ሐመረ ጽድቅ
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ሐመር
    • የማኅበሩ መልእክት
    • ትምህርተ ሃይማኖት
    • እናስተዋውቃችሁ
    • የጥያቄዎቻችሁ መልስ
    • ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት
    • ኪነ ጥበብ
    • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን
    • ከዓለም ማእዘናት
    • ዐውደ ስብከት
    • ዐቢይ ጉዳይ
  • ስምዓ ጽድቅ
    • ርእሰ አንቀጽ
    • አጫጭር ዜናዎች
    • ሪፖርታዥ
    • ቤተ አብርሃም
    • ፍሬ ከናፍር
    • የሕፃናት ዓምድ
    • ትዝብት
    • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ
  • ሙሉ ሕትመቶች
    • ሐመር በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • ሐመር በ ዓ.ም.
      • 1985
      • 1986
      • 1987
      • 1988
      • 1989
      • 1990
      • 1991
      • 1992
      • 1993
      • 1994
      • 1995
      • 1996
      • 1997
      • 1998
      • 1999
      • 2000
      • 2001
      • 2002
      • 2003
      • 2004
    • ሐመር በዓመት
      • 1ኛ ዓመት
      • 2ኛ ዓመት
      • 3ኛ ዓመት
      • 4ኛ ዓመት
      • 5ኛ ዓመት
      • 6ኛ ዓመት
      • 7ኛ ዓመት
      • 8ኛ ዓመት
      • 9ኛ ዓመት
      • 10ኛ ዓመት
      • 11ኛ ዓመት
      • 12ኛ ዓመት
      • 13ኛ ዓመት
      • 14ኛ ዓመት
      • 15ኛ ዓመት
      • 16ኛ ዓመት
      • 17ኛ ዓመት
      • 18ኛ ዓመት
      • 19ኛ ዓመት
      • 20ኛ ዓመት
    • ስምዓ ጽድቅ በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • አዳዲስ ሙሉ ሕትመቶች
      • አዲስ ሐመር
      • አዲስ ስምዐ ጽድቅ
  • ያግኙን

ስምዓ ጽድቅ

በሀገራችን እየተከሠተ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 11 January 2021
Hits: 1133
  • አጫጭር ዜናዎች
በሀገራችን እየተከሠተ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

በሀገራችን በየአቅጣጫው እየተከሠተ ያለውን አለመግባባትና ግጭት ኅብረተሰቡ በጥበብና በማስተዋል እንዲመለከተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ታኅሣሥ !፯ ቀን !)፲፫ ዓ.ም በዓለ ልደተ ክርስቶስን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥሪ አቀረቡ። 

እየተከሠቱ ያሉ አለመግባባቶች ግጭቶች ልማትን፣ ነፃነትንና፣ ሉዓላዊነትን የሚፈታተኑ በመሆናቸው ሁሉም ለሀገሩና ለሃይማኖቱ እንዲሁም ለወገኑ ተገቢ ትኩረት በመስጠት በጸሎትና በሚችለው ሁሉ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስነታቸው በመግለጫው ጠይቀዋል። 

በሀገራችን የተከሠቱት አለመግባባቶች አየተካረሩ መጥተው ወደ ግጭት እንዳያመሩ የጠቆሙት ቅዱስነታቸው በግጭቶቹ ምክንያት የሰው ሕይወት እልቂት፣ ረኀብ፣ መፈናቀልና ሌሎች መኅበራዊ ቀውሶች እየተፈጠሩ እንደሆነም ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው አያይዘውም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝንና የኤች አይ ቪ ቫይረስ በሽታዎችን ለመከላከል ከቸልተኝነት መራቅ እንደሚገባ በመግለጫቸው አስገንዝበዋል። 

በመጨረሻም የክርስቶስን ልደት ስናስብ ለእግዚአብሔር ክብር በመቆም ሰላምንም በመስጠትና በመቀበል ሊሆን ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው የታመሙና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ የተራቡትንና የተጠሙትን በማብላት በማጠጣት፣ የታረዙትንም በማልበስ፣ ለእግዚአብሔርና ለወገን ያለንን ክብርና ፍቅር በመግለጽ በዓሉን ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል። 

የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ከጥቃት ለመከላከል ያለመ ውይይት ተካሄደ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 11 January 2021
Hits: 1050
  • አጫጭር ዜናዎች

የአፍሪካ ክርስቲያኖች በአክራሪዎች የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል ዓላማው ያደረገ የበይነ መረብ ቀጥታ ውይይት መደረጉን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነብቧል። 

ውይይቱ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክና በሩሲያ የሃይማኖት ነፃነት መከላከያ ማኅበር አነሳሽነት የተጀመረ ሲሆን በአፍሪካ የሚገኙ ክርስቲያኖችንና ቅርሶችን ከአክራሪዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ለመከላከል የመፍትሔ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት እንደሆነ ዘገባው አስረድቷል። 

በቀጥታ ውይይቱ የተገኙት የሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሂላሪዮን ቮሎኮላማስሴ ‹‹በአክራሪዎች ጥቃት እየተሠቃዩ ያሉ አፍሪካውያን ክርስቲያን እኅት ወንድሞቻችንን መደገፍ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ታሪካዊ ተልእኮ ትቀበለዋለች›› ማለታቸውን ከዘገባው ለማወቅ ተችሏል። 

የሞስኮው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል እና ሁሉም ሩሲያዊ በግፍ ከሚገደሉትና ከሚሠቃዩት አፍሪካውያን ክርስቲያኖች ጎን እንደሚቆሙ ዘገባው ያስረዳ ሲሆን የአክራሪዎች ድርጊትም በተባበሩት መንግሥታቱ የሕግ ማዕቀፍ መሠረት መፍትሔ እንዲሰጠው እንደሚደረግም ዘገባው አስነብቧል። 

ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት የአፍሪካ ክርስቲያኖች ግድያና ስደት ጨምሯል ያሉት ደግሞ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ታኦድሮስ ሁለተኛ ናቸው። 

የኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ሶሳይቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ፋዘር ዶክተር ያዕቆብ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለው የብሔር ልዩነት የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለተደጋጋሚ ጥቃት እንዳጋለጣት አንሥተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መደገፍ የሁሉንም ምእመናን መብት ማስከበር እንደሆነም ተናግረዋል። 

በበይነ መረብ የቀጥታ ውይይቱ ወቅት የአፍሪካና የተለያዩ ዓለማት እምነት ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅና ፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በተወያዮቹ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት

Details
Written by: ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 11 January 2021
Hits: 1184
  • የሕፃናት ዓምድ
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት

ተወዳጅ የሆናችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከርማችኋል? በእግዚአብሔር ጥበቃ በሰላምና በጤና እንደቆያችሁን ተስፋ እናደርጋለን፤ በቤታችሁ ሆናችሁ ትምህርታችሁን በንቃት እየተከታተላችሁ ነው? በጣም ጎበዞች! በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ!

ልጆች! ዛሬ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ታሪክ ይዘልላችሁ ቀርበናልና ተከታተሉን!

አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ንጉሥ በነገሠበት ዘመን በግዛቱ ያሉ ሕዘቦቹን ለማወቅ በእስራኤል ሀገር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ይቆጠር ዘንድ አዘዘ። በትእዛዙ መሠረትም ሰው ሁሉ ሊቆጠር ወደ የትውልድ ከተማው ሄደ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በዚያን ወቅት ጌታችንን አርግዛ ስለነበር ከአረጋዊው ዮሴፍ ጋር ሆና ለመቆጠር ከናዝሬት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው  ቤተ ልሔም ሄዱ። በቤተ ልሔም ሳሉም 

እመቤታችን ማርያም የምትወልድበት ቀን ደረሰ። በዚያ ሥፍራም ብዙ ሰው ስለነበር እነ ዮሴፍ የሚያርፉበት ቦታ አላገኙም። ማደርያም ስላልነበራቸው በከብቶች በረት ውስጥ ዐርፈው ሳለ እመቤታችን የመውለጃዋ ጊዜ በመድረሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው። በጨርቅ ጠቅልላ እዛው በበረት ውስጥ አስተኛችው፤ 

በዚያ ሀገር ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ሌሊት ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ነበር፤ የእግዚአብሔር መልአክም በእረኞቹ አጠገብ ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው በራ፤ በጣምም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል። ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው። እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው። ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ፤ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ።›› (ሉቃ.፪፥፲-፲፫)

ከዚህም በኋላ እነዚህ እረኞች እርስ በርሳቸው ‹‹እስከ ቤተ ልሔም እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ›› አሉ፤ ፈጥነውም ሄዱ። ድንግል ማርያምንና ዮሴፍንም በከብቶቹ በረት አገኙአቸው። ሕፃኑንም በአዩት ጊዜ የነገሩአቸው እውን መሆኑን ስላዩ በጣም ተደነቁ። እረኞቹም እንደነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው እያመሰገኑና እያከበሩ ወደመጡበት ተመለሱ። ሰብአ ሰገልም በኮከብ ተመርተው ወደ ሕፃኑ ገብተው አምላክነቱን በመረዳት ሰገዱለት፤ ዕጣን፣ ወርቅና ከርቤንም የእጅ መንሻ አድርገው አቀረቡለት። (ሉቃ.፪፥፲፭-፲፰)

ልጆች! እነዚህ ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊያዩ የመጡ ሰዎች በደስታ የጌታችንን መወለድ አክብረዋል። ስለዚህ እናንተም በቤተ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በደስታ ልታከብሩ ይገባል።  አንድ ላይም ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን›› እያልን እንዘምር፤ እንግዲህ ለዛሬ በዚህ ይብቃን፤ ልጆች! መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ እንመኝላችኋለን!። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፤ የሰብአ ሰገሉ ረድኤት አይለያችሁ! 

 

የአዲስ አበባ ማእከል ለካህናትና መምህራነ ወንጌል ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1257
  • አጫጭር ዜናዎች
የአዲስ አበባ ማእከል ለካህናትና መምህራነ ወንጌል ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ለካህናት፣ መምህራነ ወንጌልና ለስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ከታኅሣሥ ፲፫ ቀን !)፲፫ ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሥልጠና መስጠቱን የማእከሉ ትምህርተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ አማረ ምትኩ አስታወቁ፡፡ 

በሥልጠናው እንዲሳተፉ ጥሪ ከተደረገላቸው ፪፻፵ ሠልጣኞች መካከል ፪፻፮ ያህሉ በሥልጠናው የተሳተፉ መሆናቸውን ያስታወቁት አቶ አማረ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች፣ መምህራነ ወንጌል፣ ካህናትና ክህነት የሌላቸው ነገር ግን በወንጌል አገልግሎት የተሠማሩ አገልጋዮች ተሳታፊ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ 

እንደ ኃላፊው ገለጣ ሥልጠናው ከማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማእከል ስልታዊ ዕቅድ የተቀዳ ሲሆን ሦስት ሚሊየን አዳዲስ አማንያንንና ሦስት ሚሊየን ደግሞ ወደ ሌላ እምነት የሄዱትን መመለስ የሥልታዊ ዕቅዱ አንድ አካል በመሆኑ ስልታዊ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ  ወቅቱን የጠበቀ የመምህራነ ወንጌል ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብራት አስፈላጊ ናቸው፡፡ 

ሠልጣኞቹ በሥነ ምግባር የታነፁና ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን እንዲያፈሩ ለማገዝና ክብረ ክህነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ሥልጠና እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ማእከል ከ!)፲ ዓ.ም ጀምሮ ካህናትን በተለያዩ ደረጃዎች ሲያሠለጥን መቆየቱን አያይዘው ያነሡት ኃላፊው የዛሬው ሥልጠና ደረጃ ሁለት እንደሚባልም ተናግረዋል፡፡ 

ትምህርተ አበው፣ ኦርቶዶክሳዊነት እንዲሁም የተሰባክያንን ሥነ ልቡና መረዳት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለደረጃ ሁለት ሠልጣኞች ካህናት የተሰጠው ሥልጠና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና ክብረ ክህነትን ጠብቆና አስጠብቆ ለማቆየት እንደሚያግዛቸው ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ 

ሥልጠናው የአኀት አብያተ ክርስቲያናት የአገልግሎት ተሞክሮ ጭምር የዳሰሰና የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥን ያካተተ እንደሆነ ኃላፊው ገልጠው፤ የሥልጠናው ተሳታፊዎችም የሀገረ ስብከታቸውን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ተረድተው ወንጌልን እንዲሰብኩ፣ አዳዲስ አማንያንን አጥምቀው እንዲያጸኑ፣ ጉባኤ እንዲዘረጉ እንዲሁም የሊስተሮዎች፣ የወጣቶች፣ የወዛደሮች፣ የወታደሮችና የሴተኛ አዳሪዎችን ጉባኤያት እንዴት መምራት እንደሚችሉ ግንዛቤ ያስጨበጠ  ሥልጠና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም ለካህናት አገልጋዮች በተሰጡ ሥልጠናዎችና አሁን በተሰጠው ሥልጠና የቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ወቅታዊ ሁኔታ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ኃላፊው አስረዳተዋል፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት አክራሪዎች እየፈጸሙት ያለው ግፍ በዝርዝር ለተሳታፊዎች ቀርቦ የመፍትሔ ሀሳብ እንደቀርበ የስገነዘቡት ኃላፊው በሌላ በኩል ደግሞ ዓለማዊነት ምእመናንን እየወሰደ ያለው በምግባር ታንፀው ባለመያዛቸው መሆኑን አሰልጣኞቹ ለሥልጠናው ተሳታፊዎች እንዳብራሩላቸው ገልጸዋል፡፡

የደረጃ አንድ ሥልጠናዎች በቀጣይ ተጠናክረው በአጥቢያ ደርጃ እንደሚቀጥሉ ያስገነዘቡት ኃላፊው በቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልንም በብዛትና በጥራት ለማፍራት ዕቅድ መያዙን አብራርተዋል፡፡ ሥልጠናው በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያንን የሚያካትት ሲሆን ከሥልጠናው በኋላም የተለያዩ ሴሚናሮችን በማዘጋጀት የልምድ ልውውጦች እንደሚካሄዱ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡   

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በቦሌ ገርጅ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን መምህር የሆኑት መጋቤ ሐዲስ አክሊሉ አያሌው አኀት አብያተ ክርስቲያናት ያሉባቸውን ውስብስብ ችግሮች ተቋቁመው በጥንካሬ እንዴት እንደተጓዙና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም የገጠሟትን ሁለንተናዊ ችግሮች በምን መንገድ መሻገር እንዳለባት ግንዛቤ ያገኙበት ሥልጠና መሆኑን ተናግረው በቀጣይም ከሌሎች አገልጋዮች ጋር በመሆንም ለቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ይጠቅማል ያሉትን ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ 

በቃሊቲ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤልና ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን የጠቅላላ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ኪዳነ ማርያም ምንብየለት በበኩላቸው ምእመናን በክብር ተጠብቀው፣በሃይማኖታቸው ጸንተው፣በምግባራቸው ቀንተውና ይህንን ዓለም ንቀው ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርቡ ከማድርግ ጋር ተያይዞ ለሚሠሩ ሥራዎች ሥልጠናው አጋዥ እንደሚሆናቸው የተናገሩ ሲሆን አያይዘውም ምእመናንን በያሉበት ቦታ ቤት ለቤት ተዘዋውሮ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለማስተማር እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

 

ለቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ዘላቂ መፍትሔ ያሻል

Details
Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1250
  • ርዕሰ አንቀጽ

የቤተ ክርስቲያናችን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ በተለያየ ምክንያት እና በተለያዩ አካላት መወሰድ ከጀመረ ሰንብቷል።  መወሰዱ ብቻም ሳይሆን ከነበረው መንፈሳዊ አገልግሎት በተቃራኒ ለተለያዩ አገልግሎቶች መዋል ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል።  

ይህ የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን በየጊዜው የመንጠቅ ተግባርም ሥር እየሰደደ ሲሄድ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብት እያሳጣት በራሷ መብት ሌሎችን እየለመነች እንድትኖር አስገድዷታል።  ነገሩን እያረሳሳ  በሥውር  የሚካሄደው ይህ የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ይዞታን የመንጠቅ እኩይ ተግባር ሞቅ በረድ እያለ ቤተ ክርስቲያንን ለከፋ ችግር ሲዳርጋት ኖሯል።  ይዞታው በተነጠቀበት ወቅት ብዙዎች ተነሥተው የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለማስመለስ ጥረት ቢያደርጉም የአንድ ሰሞን ብቻ ጩኸት ይሆንና ነገሩ ካለፈ በኋላ በመረሳት ተዳፍኖ ይቀራል። 

በተለያየ ጊዜ እና በተለያዩ አካላት ለተለያየ ምክንያት ለተወሰዱ የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች የጃንሜዳው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ አንዱ ማሳያ ነው።  እንደሚታወቀው የጃንሜዳው በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በነበረው ጥረት ውስጥ የጥምቀት በዓልን የአከባበር ሥርዓት መንፈሳዊ ክዋኔ አስመልክቶ ናሙና የተወሰደበት ቦታም ጭምር ነበረ።  ብዙ ዓለም ዓቀፍ ጎብኚዎች የሚጎርፉበት የጥምቀት በዓል  የተቀመጠውን መሥፈርት አልፎ በዩኒስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ ቢመዘገብም ጃንሜዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ግን ለሌላ አካላት ተላልፈው ከመሰጠት አልዳኑም።  

የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎቹ በስም የቤተ ክርስቲያን ቦታ መሆናቸው ከመነገር ውጪ ቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ቦታዎች ላይ የሰነድ ማስረጃ ስለሌላት ጉዳዩን እንዲከፋ አድርጎታል።  ከዚህም ባሻገር አንዱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ሲወሰድ ጉዳዩን የአንድ ሰሞን ጩኸት ብቻ ማድረጉ ሌሎች ቦታዎች በተመሳሳይ እንዲወሰዱ እና የቤተ ክርስቲያን መብት ወደ ጎን እንዲገፋ ምክንያት ሆኗል።   

በ፳፻፲፪ ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሠተው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ከፒያሳ የተነሡ የአትክልት ነጋዴዎች ወደ ጃንሜዳ ተዘዋውረው እንዲሠሩ በከተማው መስተዳድር መሰጠቱ ይታወቃል።  በጊዜው ቦታውን በምክንያት ለሌሎች መጠቀሚያነት ይሰጥ እንጂ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ በዓልዋን ስለምታከብርበት ሁኔታ እንዲሁም ስለቦታው አጠቃቀም የታሰበበት አልነበረም።  ይህንንም ለማለት የሚያስደፍረው አሁን ላይ ቦታው ሲለቀቅ የታየው ዘርፈ ብዙ ችግር ነው። 

እስከ ችግሩም ቢሆን ቦታውን በእጅ ለማስገባት እና ዳግም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ ምእመኑ ድረስ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በግልም በማኅበርም በብዙ ታግለዋል።  የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም ይህንን ጥያቄ በቅንነት በመቀበል ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል።  ቦታውን ከማስለቀቅ ጀምሮ በማጽዳት ሥራ ተሳታፊ ሲሆኑም ታይተዋል።  ለዚህም ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።  ጉዳዩ ግን ቦታን በመመለስ ብቻ ሊቆም አይገባውም ባይ ነን።  

የጃንሜዳው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታ በተመሳሳይ ለተወሰዱ የቤተ ክርስቲያን ቦታዎች አንዱ ማሳያ ነው።  የቀሩ እና ያልተመለሱ ቦታዎችን በመመለስ ብሎም ለነዚህ ቦታዎች ሕጋዊ ሰነድ ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ከመንግሥት ይጠበቃል።  ምክንያቱም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች በተለያየ ምክንያት ተወስደው ሳይመለሱ በመቅረታቸው በየአካባቢው ያሉ ምእመናን በየአጥቢያቸው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታ በማጣት ዛሬም እየተቸገሩ ነውና።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንዱ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ ሲመለስላት በሌላ ቦታ ሌላውን እየተቀማች እስከ አሁን ድረስ  እያነከሰች ትገኛለች።  

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለ ሙሉ መብት የሆነችበትን እና ከጥንት ጀምሮ ስትጠቀምበት የነበረውን የራሷን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ይዞዎች ከሌሎች ልትጠይቅ አይገባትም።  በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁትንና በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ውስጥ የተመዘገቡ እነዚህ የዐደባባይ በዓላት (መስቀልና ጥምቀት)ማክበሪያ ቦታዎች በመንግሥት ደረጃ የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።  እነዚህ የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ለሀገሪቱ ታላላቅ  የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በመሆናቸው የሚያስገኙት ገቢም ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ እጅግ ታላቅ ነው።  ስለሆነም መንግሥት እነዚህ በዓላት በሚከበሩባቸው ቦታዎች  ላይ የቤተ ክርስቲያንን ባለቤትነት ሊያረጋግጥላት ይገባል።  

በተለይም የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን በዓላት  ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው እና ሀገርን  በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩ በዓላት  እንደመሆናቸው መጠን ለበዓላቱ ተገቢውን ክብር በመስጠት ቤተ ክርስቲያን የምትጠይቃቸውን የባለቤትነት ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ሊያስመልስላትና መብቷን ሊያስከብርላት ይገባል።  በመንግሥትም ሆነ በሌሎች ወቅት በቀል አካላት አንጡራ ሀብቷን መንጠቅ፤ የማክበሪያ ቦታ ማሳጣት ጉዳቱ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም መሆኑ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል። 

በሀገሪቱ አንዳንድ ክልሎች እና አካባቢዎች የተጀመረው የቤተ ክርስቲያንን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች የማስመለስ ጅምር ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው።  ሆኖም ከዚህ መልካም ጅምር ጎን ለጎን መንግሥት ቦታዎቹን ሕጋዊ የማድረግ ሂደቱን በማፋጠን ቤተ ክርስቲያን ለይዞታዎቿ የሰነድ ማስረጃ የምታገኝበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራም ይጠበቅበታል።  

ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ስትጠቀምባቸው በነበሩ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ  ተደርበው የተሰጡ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተነሥተው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ሊደረግ ይገባል።  ቀደም ብላ ቦታውን በማስከበር ስትጠቀምበት የነበረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናትና።  ይዞታዋን ለሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ደርቦ መስጠቱ ውሎ ሲያድር ቤተ ክርስቲያንን ተጎጂ እያደረጋት መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው።  በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ መንግሥትም ሆነ ቤተ ክህነቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል። 

ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊና  ባህላዊ ዕሴቶች የሚንጸባረቁባቸው፣ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት፣ የፍቅር እና የመቻቻል ተምሳሌት የሆኑት የመስቀል እና የጥምቀት በዓላት የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆኑ የሀገርም ሀብት ጭምር በመሆናቸው በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።   ከላይ ለመጥቀስ ከተሞከረው በተጨማሪ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር መሥሪያ ቤትም ለሚታዩት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔን ከማሰጠት አንፃር ድርሻው የጎላ መሆን አለበት።  በየጊዜው በተለያየ ስም ከቤተ ክርስቲያን ላይ የሚወሰዱ እና የሚመለሱ ቦታዎች (ተነጥቀው የቀሩት ሳይረሱ) ሕጋዊ መሥመር የሚይዙበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ቤተ ክርስቲያን የይዞታው ባለቤት እንድትሆን ማስቻል ከሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ብዙ ይጠበቃል። 

በተለያየ መንገድ የተደራጁ እና የቤተ ክርስቲያንን አጠቃላይ መብት ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ አካላት (ከግለሰብ እስከ ማኅበራት) የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎች ሕጋዊ እንዲሆኑ የጀመሩትን ጥረቶች ከዳር ሊያደርሱት ይገባል።  ቤተ ክርስቲያን ነገ እንደማንኛውም ባለይዞታ የምትታይበትን፣ ‹‹ይሄ እኮ የሷ ይዞታ ነው›› ተብላ የምትከበርበትን እንዲሁም በቦታዋ ላይ ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንድትችል የባለቤትነት ካርታ የምታገኝበት መንገድ እስከመጨረሻው ድረስ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል።  

ከዚያም ባሻገር በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ከአጥቢያ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በሙሉ ለዚህ የባለቤትነት ጥያቄ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን ሊቆሙ ይገባል።  በዓሉን ለማክበር ከውጭ ከሚገቡ ጎብኚዎች ባሻገር በበዓላቱ ወቅት ወደ ዐደባባይ የሚወጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ላሏት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ ያላትን ቦታ ልትነጠቅ ሌሎች ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታዎችም ልታገኝ ይገባል።  ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስና በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከግምት እያስገቡ በትጋት ሊሠሩ ይገባል።  

ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን እንጂ የማይገባትን አትጠይቅም

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1087
  • ሪፖርታዥ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ ታሪኳ ወስጥ ለሀገራችን ዘርፈ ብዙ የሥልጣኔ ታሪኮችን አስመዝግባለች፤ ምክንያቱም ኦቶዶክዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ናትና።  ቤተ ክርስቲያን ሀገርን ከነድንበሩ፣ነፃነትን ከነክብሩ አስረክባለች፤ብራና ዳምጣ፣ ብዕር ቀርፃና ቀለም በጥብጣም የማይምነትን ጥላ ገፋለች።  የአድባራትና የገዳማቷ ጥንታዊነትና የኪነ ሕንፃ ጥበቦቿ እንዲሁም በውስጣቸው ያሏት ዘመን ተሻጋሪ ጥንታዊ ቅርሶቿ ከሀገሬው አልፎ ለውጭ ዜጋም ቢሆን የዐይን ማረፊያ ሆነዋል።  በዚህም ሀገርን፣ ባህልንና ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ለዓለም ማስተዋወቅ ተችሏል።  ሀገራችን ኢትዮጵያ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የአብሮነት እንዲሁም የጠንካራ ዕሴት ባለቤት የመሆኗ ምሥጢር ቤተ ክርስቲያን ከሰው ሁሉ በሰላም ኑሩ፣ ጠላቶቻችሁን ውድዱ በሚሉና በመሳሰሉት አስተምህሮዎቿ ትወልድን በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ ተግባር ላይ ለዘመናት መስራቷና ሰውን ሁሉ የሚወድ መሪዎቹን የሚያከብር ለሕገ መንግሥታቸውም የሚገዛ ትውልድን ማፍራት ነው።  በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ሀገር ሆና ኖራለች።  የህንን ደግሞ መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ በዐደባባይ “ኦርቶዶክስ ሀገር ናት” በማለት መስክረውላታል።  ይሁን እንጅ ቤተ ክርስቲያን የሀገር ክብርና ርስት መሆኗ ቢታወቅም ከውጭና ከውስጥ የተፈጠሩ ጠላቶች በየጊዜው ቤተ ክርስቲያንን እየተነኮሱ መብቷን ሲጥሱ ክብሯን ሲጋፉ ቆይተዋል። 

የእምነቱ ተከታይ ምእመናንን እንደ አውሬ እያደኑ ከመግደል ባሻገር የሀገር ርስት የሆነችው ይህች ቤተ ክርስቲያን መሥዋዕት ሆና በመሠረተቻት ሀገር ርስት አልባ የማድረግ  መከራው ከተጀመረ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠጥሯል።  ከዛሬ ሦስት ዓመት ጀምሮ በሀገሪቱ መጣ በተባለው ‹‹የፖለቲካ ለውጥ›› ሳቢያ አክራሪ ሃይማኖተኞችና የስሁት ትርክት አቀንቃኝ ፖለቲከኞች በጥምረት የሚመሯቸው መንጋዎች የቤተ ክርስቲያንን መብት ሲነጥቁና ርስቷንም እንደቅርጫ ሲከፋፈሉ እንደቆዩ ማሳያው ቤተ ክርስቲያን መብቷ እንዲከበር በተደጋገሚ ያወጣቻችው መግለጫዎች ናቸው።  ርስቷ የተወረረባት ባለርስቷ ቤተ ክርስቲያንም ለእግዚአብሔር ታሰማ ከነበረው አቤቱታ በተጨማሪ ለዓለማዊው መንግሥት ዘወትር ጥያቄዋን በሕጋዊ መንገድ ስታቀርብ ቆይታለች፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት የተሻለ መፍትሔ አላገኘችም ነበር።  አልፎ አልፎም ቢሆን የላይኛው የመንግሥት አካል ቤተ ክርስቲያን የተነጠቀችውን ርስቶች እንዲመለሱላት ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም የታችኛው የመንግሥት አመራር ጫፍ በረገጠ የተሳሳተ አመለካከ ተሸፍኖ የበላዩን ትዕዛዝ ለመፈጸም ፍላጎት ሲያሳይ አልተስተዋለም ነበር።  እነዚህ የታችኛው የመንግሥት አመራሮች ሕጋዊ አሠራረን ተከትለው የቤተ ክርስቲያንን የርስት ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የተሳሳተ የትርክት መርዝ በመርጨት ‹‹ቤተ ክርስቲያን ወራሪ ናት›› የሚል ተቀጽላ ስያሜ መስጠት ጀመሩ። 

ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያን በስሁት ትርክት አቀንቃኞችና በጽንፈኛ ፖለቲከኞች አማካይነት ባልዋለችበት ሊያውሏት ቢሞክሩም፤ ክብሯንና ጥቅሟን ለማስከበር በተቻለ አቅም ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።  በመዓልትና በሌሊት ለፈጣሪዋ ይግባኝ ብላለች፤ ምድራዊ ባለሥልጣናቱንም ተማጽናለች።  ተማጽኖዋን ከምንም ያልቆጠሩ በተሳሳተ ትርክት የሰከሩ ፖለቲከኞች ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ በበደል ላይ በደል ጨምረውባታል።  በተለይ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚካሄደው የርስት ነጠቃ በደሎች በደቡብ  እና በኦሮምያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዋናነት ተስተውለዋል።  በኦሮምያ ክልል በተለይ በአርሲ ነገሌ ከዚህ ቀደም የአካባቢው ምእመናን የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ያከብሩበት የነበውረን ቦታ ሕገ ወጥ የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና አክራሪ ሃይማኖተኞች መንጠቃቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።  በወቅቱ ምእመናን ርስታቸውን ለማስከበር ሲሉ ደምተዋል፣ ቈስለዋል እንዲሁም አንብተዋል።  የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን በወቅቱ ‹‹ሌላ ምትክ ቦታ እንሰጣለን›› በሚልና የእኔ የሚሉትን ሃይማኖት ለማስደስት የወሰዱት ርምጃ እንደሆነ ምእመናን በጊዜው ያሰሙት የነበረው አቤቱታ ምስክር ነው። 

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለይ በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ተመሣሣይ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ርስት ነጠቃ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።  በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት የለሃ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለኀምሳ ሦስት ዓመታት የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን ያከብሩበት የነበረውን ቦታ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ለመንጠቅ ርምጃ በወሰዱበት ወቅት ርስታቸውን ለመከላከል ጥረት ያደረጉ ከ፳፪ በላይ ምእመናን ያለምንም ጥፋት ለእስራትና ለገንዘብ መቀጮ እንደተዳረጉና እስካሁን ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።  

በሃድያ ዞን ሆሣዕና ከተማ የሚገኘውንና በተለምዶ ‹‹ጎፈር ሜዳ›› ተብሎ የሚጠራውን የቤተ ክርስቲያን ርስትም እንዲሁም የአካባቢው የመንግሥት አመራሮች ከነጠቁ በኋላ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያህል የዐደባባይ በዓላት በቦታው ሳይከበሩ ቆይተዋል።  በወቅቱ ችግሩን ለመፍታት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ሀገረ ስብከት ከቤተ መንግሥት እስከ ዞን ድረስ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ምንም መፍትሔ ሳያገኝ እንደቀረ ይታወቃል። 

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም  የመስቀል አደባባይና የጃን ሜዳ ጉዳይ እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል።  የቤተ ክርስቲያን ርስት ጉዳይ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ጎልቶ ይታይ እንጂ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም ጭምር ችግሩ አሳሳቢ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል። 

በነዚህ ሁለት ሳምንታት ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ርስት የተመለከቱ መልካም ዜናዎች መሰማት ጀምረዋል።  ከዚህ ቀደም የከፋ ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተቀራርበው ለመሥራትና የቤተ ክርስቲያን የርስት ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎት ያሳዩ የዞንና የወረዳ እንዲሁም የከተማ አስተዳድር አመራሮች መኖራቸውን ከየሀገረ ስብከቱና ከጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መረዳት ተችሏል።  እንደ ኅብረቱ መረጃ ከሆነ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፷፭ አጥቢያዎች  የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሠርቶ ተሰጥቷቸዋል።  በሀገረ ስብከቱ እስካሁን ድረስ ፴፰ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ተሠርቶላቸዋል።  ጃንሜዳን ጨምሮ ሌሎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን የተያዙ የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች በሕጋዊ ስምምነት ቤተ ክርስቲያን የይዞታው ባለቤት መሆኗ ተረጋግጦ ውል እንዲፈጸም የውል ስምምነቱ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ኅብረቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዳስገባ አስታውቀዋል።  

ከዚህ ጋር ተያይዞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ጃንሜዳ በአትክልት ተራነት ሲያገለግል መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ኅብረቱ ባደረገው ጥረት ገበያው ተነሥቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት አመራሮች በቦታው ላይ ተገኝተው በአካባቢው የነበረውን ቆሻሻ የማጽዳት ሥራ ራሳቸው በመሥራት አስጀምረዋል።  የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ሳይቀሩ የጥምቀት በዓል መዋያ ቦታውን በማጽዳት ለመጭው የጥምቀት በዓል ዝግጁ አድርገዋል።  በደቡብ ክልል ከርስት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታት በኅብረቱ በኩል ከክልል እስከ ዞን ድረስ ባሉ መዋቅሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፤ ችግሮቹም ተለይተው ቀርበዋል።  የባለሙያዎችን ግኝት መሠረት ያደረገ ውይይትና የውሳኔ ሐሳብም ቀርቧል።  በውሳኔውና በቀረቡት ጥያቄዎች መሠረት የበዓላት ማክበሪያ ርስቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች እየተሠሩላቸው እንደሆነ ከኅብረቱ ሪፖርት ማረጋገጥ ተችሏል።  በተለይ በሃድያ ዞን ሆሣዕና ከተማ እንዲሁም በጋሞ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ከቤተ ክርስቲያን  የይዞታ መነጠቅ ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በተደረገው ውይይት በመንግሥት አካላት የተነጠቁ የቤተ ክርስቲያን የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ለቤተ ክርስቲያን ተመላሽ እንዲደረጉ ከስምምነት ላይ መደረሱን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።  በተጨማሪም በመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት ታሥረው የነበሩ ምእመናን በአጭር ጊዜ እንዲፈቱና የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ጥያቄም ተገቢ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ከስምምነት ላይ መድረሱን ኅብረቱ በሪፖርቱ አስታውቋል።  በ፴፱ኛው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ርክበ ካህናት  ወቅት የቀረበው የድሬደዋ ሀገረስብከት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከዚህ ቀደም የይዞታ ማረጋገጫ ያላገኙ አብያተ ክርስቲያናትና መካነ መቃብሮች ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ማግኘታቸው ተረጋግጧል።  በሀገረ ስብከቱ ለቤተ ክርስቲያን ማስፋፊያነት የተጠየቁ ተጨማሪ የመሬት ይዞታዎችም ተፈጻሚ ሆነዋል። 

የቤተ ክርስቲያንን ክብር እና መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመው ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠበቂ ኅብረት በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ባለሥልጣናት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን በደልና የሚፈጽሙትን አድሏዊ አሠራር ለማስቆም ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቋል። የአብያተ ክርስቲያናትና የአደባባይ በዓላት መክበሪያ ቦታዎች ይዞታ እንዲከበሩ ከ፳፻፲፪ ዓ.ም. ጀምሮ ሰነዶችን በማዘጋጀት ወደ ተለያዩ ክልሎች በአካል በመጓዝ ለክልሎቹ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥያቄዎችን አቅርቦ ጉዳዩን ሲከታተል መቆየቱን ገልጦ፤ ከክልል መስተዳድሮችና ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር  በተከታታይ ከተደረጉ ውይይቶች በኋላ ተጨባጭ ውጤቶችን መስመዝገቡን አስታውቋል። 

በተለይ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ኅብረቱ ላቀረበላቸው የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ጥያቄዎች በጎ ምላሽ በመስጠት ቀዳሚ ተጠቃሾች እንደሆኑ አስታውቋል። ለሐረሪ ክልል ባለሥልጣናት ከቀረበላቸው “ይዞታ ይከበርልን” ጥያቄዎች መካከል ክልሉ ቃል በገባው መሠረት የተወሰኑት ምላሽ አግኝተዋል። በሐረር ከተማ የሚገኙ አምስት አብያተ ክርስቲያናት እና የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ተሰጥቷል። ኅብርቱም ለሐረሪ ክልል ባለሥልጣናት በጎ ምላሽ ምስጋናውን አቅርቧል።  በቀጣም ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ቦታዎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ የይዞታ ማርጋገጫ ሰነድ ተሠርቶ እንደሚሠጣቸው የኅብረቱ ሰብሳቢ ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ በሪፖርታቸው አስረድተዋል።  በተጨማሪም በጋሞ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ እና በሆሳዕና ከተማ አስተዳድር የተፈጠረውን የቤተ ክርስቲያን  የይዞታ ችግር ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል። ችግሩ እልባት እንዲያገኝ የተሔደበትን መንገድ እና  የተገኘውን ውጤትም በቅርቡ እንደሚገለጽ ከኅብረቱ ሪፖርት ለማውቅ ተችሏል። 

ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን እንጂ የማይገባትን አልፋ አትጠይቅምና መንግሥት የሚገባትን ያህል ርስት /ይዞታ/ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሊሰጣት ይገባል።  በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን የሀገሪቱ የመሬት አስተዳደር ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ተፈጻሚ ማድረግ ለመንግሥትም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን አዋጭ ነው።  ቤተ ክርስቲያን ካላት የምእመናን ብዛት አንጻር የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ማስፋፊያ የመካነ መቃብር ቦታዎችን ጨምሮ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ይዞታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።  በሕጋዊ ቦታዎች የሚከበሩ የዐደባባይ በዓላት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በመስህብነት የሚያገለግሉ በመሆናቸው ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ እንደምትሆን ሳይዘነጋ መንግሥት የሃይማኖትና የመንግሥትን ግንኙነት የወሰነውን ሕገ መንግሥታዊ አሠራር ተከትሎ የቤተ ክርስቲያንን የባለቤትነትን መብትና ጥቅም ሊያከብር ይገባዋል።  እግዚአብሔር ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቅልን። 

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከ፲፱፻፵፪ - ፳፻፲፫ ዓ.ም

Details
Written by: በጋዜጣው ሪፖርተር
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1453
  • ቤተ አብርሃም
ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ  ከ፲፱፻፵፪ - ፳፻፲፫ ዓ.ም

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከልጅነት እስከ ዕለተ እረፍታቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነት አገልግለዋል።  ከአዲ አባት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የፊደል ትምህርት የሚጀምረው የልጅነት ሕይወታቸው መንፈሳዊውን የቤተ ክርስቲያን እውቀት ለመቅሰም ከተለያዩ ሊቃውንት ዘንድ ደርሰዋል፤ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረዋል።  ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪው ዓለም ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሰማራቻቸው ቦታዎች ሁሉ በመሄድ ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋል።  ብዙ መጻሕፍትን በመጻፍ ለምእመናን እንዲደርሱ አድርገዋል፤ የሰንበት ት/ቤት፤ የስብከተ ወንጌል እና የአብነት ትምህርት ቤት አገልግሎት እንዲስፋፋ በሕይወት ዘመናቸው ብዙ ሰርተዋል።  

ብፁዕነታቸው ከተወለዱበት ሚያዚያ ፭ ቀን ፲፱፻፵፪ ዓ.ም እስካረፉበት ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም መንፈሳዊ እድገታቸውንና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውን፤ባጠቃላይ የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል መልካም ንባብ፦

የብፁዕነታቸው የልጅነት ሕይወት

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በቀድሞ በትግራይ ክፍለ ሀገር በሽሬ አውራጃ ፀለምት ወረዳ ውስጥ ልዩ ስሙ አዲ አባት ኪዳነ ምሕረት ደብር ከአባታቸው ከባላምባራስ አሳየኸኝ ነጋ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ሕይወት ረታ ሚያዚያ ፭ ቀን ፲፱፻፵፪ ዓ.ም ተወለዱ።  ፈሪሃ እግዚአብሔር ካደረባቸው፤ በጉልበታቸው እና በገንዘባቸው ቤተ ክርስቲያንን ያገለግሉ ከነበሩት ወላጆቻቸው በስዕለት የተገኙት ብፁዕነታቸው የያኔው አምኃ ሥላሴ ገና የአምስት ዓመት ሕፃን ሳሉ ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥተዋል።  

ሕፃኑ አምኃ ሥላሴ በጣም የሚወዷቸውና ሲንከባከቧቸው የነበሩ ወላጅ አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ኀዘናቸው በጣም የመረረ እንደነበር ይነገራል።  ሆኖም 

ለቤተ ክርቲያን የተሰጡ የስዕለት ልጅ ናቸውና በዚያ የጨቅላነት ዕድሜያቸው በሕልማቸውም ሆነ በእውናቸው የሚታሰባቸው የአበው መነኰሳት ሕይወት ነበረ፤ እንደነሱ ለመሆንም እጅግ ይመኙ ነበረ።  

የብፁዕነታቸው የትምህርት ቤት ሕይወት

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ  የ፮ እና የ፯ ዓመት ልጅ እያሉ በዋልድባ አበረንታንት ገዳም ዙሪያ ከ፴‐፺ ኪሎ ሜትር እየተዘዋወሩ በርካታ መንፈሳዊ ትምህርት ተምረዋል።  በአቅራቢያቸው በምትገኘው ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ከፊደል እስከ ንባብ ያለውን የልጅነት ትምህርት ከመምህር ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ተምረው አጠናቀዋል።   

በ፲፱፻፶፱ ዓ.ም ጎንደር ድረስ በመሄድ ከብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የዲቁና ማዕረግ ተቀብለዋል።  ደብረ አባይ ገዳም በመግባትም የአብነት መምህር ከሆኑት ከየኔታ የኋላሸት ዘንድ ለአንድ ዓመት ተኩል መዝገበ ቅዳሴን ተምረው በ፲፱፻፷ ዓ.ም ከገዳሙ የእውቅና ሰርተፊኬት ተቀብለዋል።  ለዓመታት የዋልድባ የገዳም ቆይታቸው ሥርዓተ ምንኰስናውን እያጠኑ በረድዕነት ገዳሙንና ማህበሩን በከፍተኛ ደረጃ ሲረዱ ቆይተዋል።  ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም በተወለዱ በ፳፫ ዓመታቸው ከታወቁት ባለ አስኬማ ከባሕታዊ አባ ገብረ አረጋዊ ወልደ ገሪማ ማዕረገ ምንኩስናን ተቀብለዋል።  ኅዳር ፳፫ ቀን ፲፱፻፷፬ ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  እጅ በአክሱም ርእሰ አድባራት ወገዳማት የቅስና ማዕረግ ተቀብለዋል።  

ቅስናን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ቀድሞ ገዳማቸው አበረንታንት በመመለስ በልዑክነት፣ በቄሰ ገበዝነት አበውንና ገዳሙን እያገለገሉ ከታላቁ መምህር የኔታ ገ/ኪዳን ወ/ሥላሴ ባህረ-ሐሳብ ተምረዋል።  ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እስከ ፲፱፻፸ ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የሥራ መስኮች እያገለገሉ ጎንደር ከምትገኘው ጥንታዊቷ ደብር ግምጃ ቤት ማርያም ከሚገኙት ከመምህር ወልደ ሰንበት መጽሐፈ መነኰሳትን ተምረዋል። 

ከጎንደር ግምጃ ቤት ማርያም መጽሐፈ መነኰሳትን ከተከታተሉ በኋላ ወደ ገዳማቸው ዋልድባ ተመልሰው በልዩ ልዩ የሥራ መስክ ገዳሙንና አበው መነኮሳትን አገልግለዋል።  ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም በመመለስም ከሊቀ ሊቃውንት መንክር ሐዲስ ኪዳንን ተምረዋል።  ሲመለሱም በአበው መነኰሳት ተመርጠው አዲስ አበባ ድረስ እየመጡ የገዳሙን ተግባር እያከናወኑ በአጠቃላይ በተማሪነት፣ በረድዕነት በመጋቢነት፣ በቄሰ ገበዝነትና በልዑክነት ለ፲፱ ዓመታት ዋልድባ አበረታንትን አገልግለዋል።  

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በ፲፱፻፸፱ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከገዳሙና ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያካበቱትን እውቀት ለማዳበር ወደ ኢሉባቡር በመሄድ በኢሉባቡር ሀገረ ስብከተ ከሚገኘው መቱ የካህናት ማሠልጠኛ ት/ቤት ገብተው የስብከት ዘዴ በዘመናዊ መልክ  ሲከታተሉ ቆይተው አብረዋቸው ሲማሩ ከነበሩት ፷ ካህናት መካከል አንደኛ በመውጣት በወቅቱ ከነበሩት ሊቀ ጳጳስ እጅ ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ተቀብለው  ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። 

የብፁዕነታቸው የሥራና የአገልግሎት ሕይወት

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በዋልድባ አበረንታንት ገዳም  በረድዕነት በመጋቢነት፣ በቄሰ ገበዝነትና በልዑክነት ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተሰጠውን የአስተዳዳሪነት ፈተና ጥያቄ ከሰባት መነኰሳት መካከል ሁለተኛ በመውጣታቸው በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በፈንታሌ ወረዳ በሚገኘው የመተሐራ አንቀጸ ሰላም መድኃኔ ዓለም ገዳም በአስተዳዳሪነት ተሹመው አገልግለዋል።      

በመተሐራ አንቀጸ ሰላም መድኃኔ ዓለም ገዳም በሦስት ዓመት የአገልግሎት ዘመናቸው ባሳዩት የሥራ ፍቅር ከጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፹፭ ዓ.ም ጀምሮ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን/ገዳም/ አስተዳዳሪ በመሆን ተሹመው አገልገለዋል።  በመቀጠልም ወደ ምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በመዛወር ከየካቲት ፲፱፻፹፭ እስከ የካቲት ፲፱፻፹፮ ዓ.ም በዋና ሥራ አስኪያጅነት ለ፩ ዓመት አገልግለዋል።  ከየካቲት ፲፱፻፹፮ ዓ.ም ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተዛውረው የመንሳዊ ኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ሞግዚት ሆነው የገዳማዊ ዕውቀት ግብረ ገብነትና ትህትናን አስተምረዋል።  

 ከኅዳር ፳ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ.ም እስከ ሰኔ ፳ ፲፱፻፹፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ፣ በሊቀ ሥልጣናት ማዕረግ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ፣ከመጋቢት ፩ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም  እስከ  ኅዳር ፲ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም  ዋና አስተዳዳሪ ፣ ከኅዳር ፲ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም እስከ የካቲት ፲፩ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም የደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ፣ በሀገር ውስጥ ያለው ኀላፊነታቸው እንዳለ ሆኖ  ከሰኔ ፳ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም እስከ የካቲት ፲፱፻፺፩ ዓ.ም በጅቡቲ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በመሾም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት አገልግለዋል።  ከጅቡቲ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ከየካቲት ፩ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ጀምሮ ምዕረገ ጵጵስናን እስከተቀበሉበት ሐምሌ ወር ድረስ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል።

ማዕረገ ጵጵስና

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከረጅም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን የትጋት አገልግሎት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም በኤጲስ ቆጶስነት መርጧቸው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ አባ ኤጲፋንዮስ በሚል ስያሜ ማዕረገ ጵጵስናን ተቀብለዋል።  

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ማዕረገ ጵጵስናን ከተቀበሉ በኋላ በሀገር ውስጥ በሸካ ቤንች ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ እንዲሁም በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም በደቡብና ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን አገልግለዋል።  ብፁዕነታቸው ከሀገር ውስጥ አገልግሎት በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን በውጪው ዓለም ካቋቋመቻቸው አህጉረ ስብከት ውስጥ በየመን ሰንአ፣ በሊባኖስ ቤይሩት፣ በጣልያን ሮም፣ በኢየሩሳሌም፣ በደቡብ አፍሪካና በግብፅ ካይሮ እየተላኩ ምእመናንን አጽናንተዋል፤ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። 

የብፁዕነታቸው የኅትመት ሥራዎች

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከታላቁ ዋልድባ አብረንታንት ገዳም ከመግባታቸው በፊት በትውልድ ቀያቸው በምትገኘው አዲ አባት ኪዳነ ምሕረት የተለማመዱትን የመንፈሳዊ ሕይወት ወደ ደብረ አባይ ሄደው በርካታ መንፈሳዊ ትምህርት አካብተዋል።  ይህንኑ የተማሩትን ትምህርት ለሌላው ለማካፈልና ለማስተማር በነበራቸው ትጋትና ጥረት ጥቂት የማይባሉ መጻሕፍትን በመጻፍና በማሳተም ለቤተ ክርስቲያናችንና ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው አበርክተዋል።   

ፍኖተ ሃይማኖትና ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤ 

ክህነትና አገልግሎቱ፤

ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የሃይማኖተ አበው አስተዋጽኦ፤

ፍሬ ጸሎት ወንስሐ

መጽሐፈ መነኮሳት የተሰኙ መጻሕፍት ጥቂቶቹ ናቸው። 

ብፁዕነታቸው በልማት ሥራዎች

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በነበሩበት የሕይወት ዘመን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም፣ ምእመናንን የሚያንጽ መንፈሳዊ አገልግሎትን የሚያሰፋ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን ማከናወናቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።  በተለይ የነበራቸው የጸሎት ሕይወት፣ የመንፈሳዊ አባትነትና ትሕትናቸው በብዙዎች ዘንድ የመወደድ ፀጋን አላብሷቸዋል።  ለሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት መሳካት ምሥጢሩም  ፍጹማዊ ሕይወታቸው አንዱ ሲሆን ሌላው የተለያዩ የውጭ ሀገር ኤምባሲዎችን፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን እና በሀገር ቤት የሚገኙ ባለሀብቶች የገንዘብና የሙያ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው የማስተባበር ፀጋ እንዳላቸው ይነገርላቸዋል። 

ብፁዕነታቸው በተመደቡበት አህጉረ ስብከትና አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከፍተኛ የልማት ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።  በደቡብ ምዕራብ ሸዋና በምዕራብ ሸዋ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ የካህናት ማሰልጠኛ አዳሪ ት/ቤቶች፣ የሕፃናት መርጃ (ዕጓለ-ማውታ)፣ ክሊኒክና ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማሳነጽ በዚህ አጭር ጊዜ መግለጽ የማይቻል የልማት ሥራ አከናውነዋል።  በተለይ  በሰሜን ምዕራብ ወረዳ በፀለምት የእምባ ድኩላ አቡነ አረጋዊ እና የአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቤተ ክርስቲያንን በግል ገንዘባቸው አሳንጸው ለምእመናን እና ምእመናት እንዲገለገሉበት በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ኀላፊነታቸውን የተወጡ ታላቅ አባት ነበሩ።   

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የሥራ ክቡርነትን የተረዱ፤ ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን ፍፁም ፍቅር የነበራቸው፤ ከምንም በላይ መንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ የጸሎት ሰው መሆናቸው፣ ግብረ-ገብነታቸው፣ ለሌላው ያላቸው የመልካም ምሳሌነት፣ ሰውን ሁሉ መውደድና ካላቸው ሁሉ ማካፈል የሚወዱ መሆናቸው፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ያላቸው ምሳሌነት ከቤተ ክርስቲያን እና ከምእመናን ልብ የማይጠፋ ሕያው ታሪክ ያላቸው አባት እንዳደረጋቸው ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ይቻላል። 

ብፁዕነታቸው መንፈሳዊ ሕይወትን በተግባር የኖሩ፤ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን የበረከት ዕድሜ በሙሉ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ያዋሉ ጠንካራ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ነበሩ፤ ‹‹ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ሰው ማነው?›› መዝ ፹፰፥፵፰ እንዳለ ዳዊት በመዝሙሩ በነበራቸው የሕይወት ዘመን ቤተ ክርስቲያንን በብዙ መልኩ አገልግለው እና ከቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ልብ የማይጠፋ ታላቅ ሥራ ሠርተው ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በተወለዱ በ፸፪ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።  የብፁዕነታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፍ ለቤተ ክርስቲያን እና ለምእመናን ጥልቅ ሐዘን ቢሆንም ያከናወኗቸው በጎ ተግባራት ህያው ናቸውና በዚህ እንጽናናለን።  

 በረከታቸው ይደርብን!

 

“ጦርነቱ ምእመናንን በሞት፣ በአካል ጉዳትና በስደት እየነጠቀን ይገኛል”

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1096
  • ፍሬ ከናፍር
“ጦርነቱ ምእመናንን በሞት፣ በአካል ጉዳትና በስደት እየነጠቀን ይገኛል”

በዚህ ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ  ጦርነት መቀስቀሱን ሰምተናል፤ በሚዲያም አይተናል።  በጦርነቱም በሁለቱ ወገን  የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ሀብት ንብረት ወድሟል።  ይህ ድንገተኛ ጦርነት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ የጎላ ጉዳት እንደሚያመጣ ይታወቃል።  ጦርነቱ በቤተ ክርስቲያንና  በምእመናን  ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ም/ኃላፊ  ከሆኑት ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ ጋር አጭር  አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።  መልካም ንባብ።  

ስምዐ ጽድቅ፡- በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ምን ዓይነት ተፅእኖ ይኖረዋል ይላሉ?

ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡-  የትም ቢሆን ጦርነት አስከፊ እንጂ መልካም ገጽታ የለውም።  ሁሉም ሰው እንደመረዳት አቅሙ የጦርነትን አውዳሚ ገጽታ ይረደዋል።  ሰሞኑን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በጣም አሳሳቢ ነው።  ጦርነት ሰዎች በራሳቸው ፍላጎት የሚያመጡት ሰው ሰራሽና ሰው ጨራሽ ድርጊት ነው።   ጦርነት የሰውን ልጅና ዓለምን ያወድማሉ ከሚባሉ ክፉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።  አስከፊና አሳዛኝም ክስተት ነው።  ጦርነት ሞትን ብቻ የሚጠራ ሳይሆን ሳንሞትም እንደሞትን እንድናስብ አድርጎ የሚያኖረን አውዳሚ ተግባር ነው።  ትልቅ ጠባሳን ጥሎም የሚያልፍ ነው።  

ጦርነት በሥጋ ብቻ ሳይሆን በነፍስም ይጎዳል፤ ምክንያቱ በጦርነት ጊዜ አንዱ አንዱን ይገድላልና።  ሀገራችን ኢትዮጵያ የእርቅና የሽምግልና ጥሩ እሴት ባለቤት ሀገር ብትሆንም በየጊዜው እሴቶቻችንን ወደጎን በማለት ሀገሪቱ በጦርነት እንድትታመስ እየተደረገ ይገኛል።  ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ የተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ ከሽምግልናና ከእርቅ የዘለሉ አልነበሩም።  አሁን በዚህ ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክልል እየካሄደ ያለው ጦርነትም ነገሩ በሽምግልና ማለቅ የነበረበት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ሄዶ ወደ ለየለት ጦርነት ተለውጧል።  ይህ ጦርነት ከመንጋው መካከል ያሉ ምእመናንን በሞት፣ በአካል ጉዳትና በስደት እየነጠቀን ይገኛል።  ጦርነቱ መንጋውን ከመንጠቁ በተጨማሪ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትባቸው እንዲሁም የምእመናን ተስፋ የሆኑ አብያተ ክርስቲያት ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል፤ አንዳንድ ሀገራዊና ታሪካዊ ቅርሶች ደግሞ በሥጋት ውስጥ ይገኛሉ።  ይህ የጦርነት ክፉ ገጽታው ነው።  በጦርነት ጊዜ ምእመናን መሞታቸው አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ መቃጠላቸው አይቀሬ ነው።  

በሁለቱም ክፍል በጦርነቱ እየተሳተፉ ካሉት አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ናቸው።  ገዳዮችም ሟቾችም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።  ከሚጠፋው ሕይወት በተጨማሪ የሕዝበ ክርስቲያኑ ሀብትና ንብረት በአንድ ጀንበር እየወደመ ነው።  ይህ ጦርነት ነገ የማንተካቸው በአባቶቻችን የረቀቀ ጥበብ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናትን ጭምር ያጠፋል።  በጦርነቱ መሀል የጦርነቱ አካል የሆኑ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኗን መደበቂያ ሊያደርጓት ይችላሉ።  በዚህን ወቅት የመንግሥት ኃይል የተደበቁ ዓመፅያንን ለማጥፋት ሲሞክር ቤተ ክርስቲያንም ትጎዳለች።  በሌላ ሁኔታም ቤተ ክርስቲያን የወንበዴና የአጥፊዎች መሸሸጊያ ሆናለች የሚል ወቅቱን ያላገናዘበ ስያሜ ሊያሰጣት ይችላል።  የጦር መሣሪያ መከማቻ ሆናለች ልትባልም ትችላለች።  ነገር ግን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የገባ ኃይል መሣሪያውን አስረክቦ ከነፍሰ ገዳይነት ርቆ መጀመሪያ እጁን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ንስሐ ቢገባ ምልካም ነው።  ቤተ ክርስቲያንም የሽፍቶች፣ የነፍሰ ገዳዮች፣ የአማፅያንና የአረመኔዎች መደበቂያ መሆን የለባትም፤ ምእመናንም ቤተ ክርስቲያናቸውን መጠበቅ አለባቸው።  

ስምዐ ጽድቅ፡- በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናን ለመርዳትና ለማጽናናት ምን ታስቧል?

ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- የተፈናቀሉና ጉዳት የደሰባቸውን ምእመናን ማቋቋምና ማጽናናት ቤተ ክርስቲያኗ ቅድሚያ ሰጥታ የምትሠራው ሥራ ይሆናል።  ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ምእመናን አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ማድርጓ ይታወቃል።  ይህ ድንገተኛ ጦርነት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲፈጸምባት የነበረው በደል አድጎ ነው ወደለየለት ጦርነት የተቀየረው።  ምንጊዜም ጦርነት በመጣ ቍጥር በዋናነት ቤተ ክርስቲያንና ልጆቿን ነው የሚጎዳው።  በዚህ ጦርነትም በርካታ ምእመናን ተገድለዋል፤ ታርደዋልም።  ይህ ጦርነት እንዳይመጣ ቤተ ክርስቲያን አስቀድማ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ስታውጅና ስትጸልይ ቆይታለች፤ ወድፊትም ትጸልያለች።  የማስታረቅ ሥራም ለመሥራት ሞክራ ነበር።  ነገር ግን በሁለቱም ወገን ወደ ዕርቅ ለመምጣት ፈቃደኞች አልሆኑም።  ፈቃደኞች ባለመሆናቸውም ምክንያት ጦርነቱ ተከሰተ።  በዚህም ምእመናን ተፈናቀሉ፤ ሞቱም።  ምእመናን በሃይማኖትና በቋንቋ ወደ ማይመስሏቸው ሀገራት በመሰደድ በእንግልት የታጀበን ኑሮ መምራት ጀምረዋል።  የተሰደዱ ምእመናን መመለስና ማቋቋም የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው።  ምእመናንን በመመለሱና በማቋቋሙ ሂደት ላይ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት አካላት ጋር በጋራ ትሠራለች።  

ስመዐ ጽድቅ፡- አሁን እየተካሄደ ባለው ጦርነት አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ቤተ ክርስቲያን ምን እየሠራች ነው? 

ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- ሁሉም ሃይማኖታዊ ቅርሶች የቤተ ክርስቲያናችን ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥትና የሀገር ሀብቶች ናቸው።  ቅርሶችን ጠብቆ ማቆየትና ከጉዳት መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ነው።  ዓማፅያን ቤተ ክርስቲያንን መደበቂያ ሊያደርጓት ይችላሉ።  በዚህን ወቅት መንግሥት ተፈላጊ የሆኑ አማፅያንን ለመያዝ በሚያደርገው ጥረት አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሶች ጉዳት በማይደርስባቸው ሂደት ሊሆን ይገባል።  

መንግሥትም አስቦ ወይም በቸልተኝነት በቅርሶች ላይ ጉዳት እንዲደርሰባቸው ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም።  ነገር ግን ቅርሶች በድንገት ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችልም ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው።  የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል።  ስለዚህ ሀገር ከቅርሶቹ የምታገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ መንግሥት የቻለውን ያህል ቅድመ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።  ምእመናንም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን በቅርሶች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።  መንግሥት በበኩሉ የሕግ ማስከበር ሂደቱን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እያከናወነ እንደሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሲሰጥ ተስተውሏል።  እስካሁን ድረስም በግልጽ የታወቀ በቅርሶች ላይ የደረሰ ጉዳት ያለመኖሩን ተረድተናል።  

ጥንታዊ ገዳማትና አድባራትን ከመጠበቅ በተጨማሪ ንጹሐን ዜጎች የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ጭምር መንግሥትን የማሳሰብ ሥራ እየተሠራ ነው።  መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት ሸሽተው ወደ አጎራባች ሀገራት የሄዱ ኢትዮጵያውያንም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ወደአካባቢያቸው ተመልስው የቀደመ ኑሯቸውን እንዲመሩ እንዲያደርግ መልእክቶች ተላልፈዋል።   እስኪመለሱ ድረስም በያሉበት አካባቢ አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ተጠይቋል። መንግሥትም የተጠየቀውን ተቀብሎ ወደተግባር በመለወጥ ዜጎቹ ዘላቂ ሰላም እንዲያገኙ እየሠራ እንደሆነ ገልጧል። ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ሂደቱን የሚከታተል ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ ከመንግሥት ጋር በጋራ የተቻላትን ሁሉ ታደርጋለች።  

ስመዐ ጽድቅ፡- ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ አድባራትና ገዳማት በመንግሥት ቀጥተኛ ትእዛዝ እንዲዘጉ እየተደረገ ነው።  ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ? 

ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- አብያተ ክርስቲያናቱና ገዳማቱ እንዲዘጉ የተደረገው መንግሥት የፀጥታ ሥጋት አለ በማለቱ ነው።  ቤተ ክርስቲያን በዚህ ደረጃ የፀጥታ ሥጋት ምንጭ ትሆናለች ተብሎ አይታሰብም።  ነገር ግን አንዳንድ ሰርጎ ገቦች ወቅቱን ምክንያት አድርገው የቤተ ክርስቲያን ክብር እንዲነካ የጥፋት ተልዕኮ ይዘው በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ።  የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የፀጥታ ሥጋት መፍጠር ሳይሆን ዓለም የፀጥታና የሰላም ምንጭ እንድትሆን ማድረግ ነው።  ከዚህ ውጭ የሆነ ዓላማ ሁሉ ሰይጣናዊ እሳቤ ያላቸው ግለሰቦች እንጂ ሰማያዊት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን አይደለም።  

ሰዎች ከቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ ውጭ የሆነ ተግባርን በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።  ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ዓለማዊ እንዳልሆነችና ከዕኩይ ተግባር የራቀች መሆኗን ለመንግሥትም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስረዳት አለበት።  ጉዳዩ የተከሰተው በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ባሉ አጥቢያዎች በመሆኑ ሀገረ ስብከት ጉዳዩን እየተከታተለ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ሊሠራ ይገባል።  የሕዝብ ግንኙነት መምሪያውም ክትትል በማድረጉ ሂደት የራሱን ድርሻ የሚወጣ ይሆናል።  

ስምዐ ጽድቅ፡- በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?

ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- ሀገራዊ እሴቶቻችንን ተጠቅመን በፍቅርና በሰላም መሥራት አለብን።  ጦርነት አውዳሚ እንጂ ጠቃሚ አይደለም።  በሀገራችን ፍቅር እንዲኖር ካስቀየምነው ፈጣሪ ጋር እርቅ መፈጸም አለብን።  ክርስቲያን ተስፋ አይቈርጥምና ዛሬ የጨለመውን ነገ እንደሚነጋ አስበን መኖር አለብን።  መንግሥት የዜጎቹንና የቅርሶቹን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ምእመኑም በጸሎት እየተጋ ይህ አስከፊ ጦርነት እንዲቆም እግዚያአብሔርን መለመን አለበት።  ቤተ ክርስቲያን በሀገር ላይ ሰላም እንዲመጣ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም።  ይህንንም ለዘመናት ስታከናውነው ነበረች፤ለወደፊትም የአስታራቂነት ድርሻዋን ትወጣለች።  መንግሥትም የአባቶችን ምክርና ተግሣፅ መስማትና መተግበር ይጠበቅበታል።  እግዚአብሔር በኢትዮጵያና በልጆቿ የሚጨክን አምላክ ባለመሆኑ በሀገራችንና በሕዝባችን መካከል ሰላምና ፍቅርን ያመጣልን ዘንድ እንማጸናለን።   እግዚአብሔር ሀገራችንን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቅልን።     

የአውቶብስ ላይ ማዕጠንት

Details
Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1167
  • ትዝብት

በአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ ሲጓዙ ብዙ የሚያስገርም፣ የሚያሳዝን፣ የሚያስፈግግ፣ የሚያስቆጣም ክሥተቶች ያጋጥማሉ። በተለይም ደግሞ ረዘም ያለ ርቀት ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚጓዝ ሰው ከሚኖረው ብዙ የጉዞ ቆይታ አንጻር እንዲህ ዓይነት ክሥተቶች ሊፈራረቁበት ይችላሉ።

እኔም በአንድ አጋጣሚ ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ ሀገር ስጓዝ ያጋጠመኝን እና በጅጉ አዝኜ የታዘብኩትን ላውጋችሁ። አውቶብሱ ሞልቶ የተወሰኑ ቆመው የሚሄዱ ሰዎችንም ጭኗል። ሁሉም አፍና አፍንጫውን በመሸፈኛ ጋርዶ ግማሹ በወንበር ላይ ተክዞ፣ ግማሹ አጠገቡ ካለው የጉዞ ጓዱ ጋር እያወጋ፣ የቆሙት ደግሞ የመኪናውን ወራጅና ቋሚ ብረቶች በእጆቻቸው ይዘው፣ በመኪናው ግፊት ወደ ኋላ ወደ ፊት እየተወዛወዙ ይጓዛሉ። ፌርማታዎች ላይ ሲደረስ ከነበሩት ገሚሶቹ ሲወርዱ አዲስ ተሳፋሪዎች ደግሞ በጉዞው ይስተናገዳሉ። 

በዕለቱ በጉዞው በጉልህ መጀመሪያ ላይ ያጋጠመኝ  ተሳፋሪ ሆኖ ትኬት ቆርጦ ከገቡት ተጓዦች መካከል አንዱ ተሳፋሪው የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋለት ጮክ ብሎ መጠየቅ ጀመረ። ከተሳፋሪው የተወሰነው ሰውዬው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ በመግባቱ ያጉረመርማል። የተወሰኑ አጠገቡ ያሉ ወጣቶች ደግሞ የህክምና ማስረጃ ብሎ የያዘውን ወረቀት ቀረብ ብለው በማየት ‹‹ማኅተሙ ደብዝዟል፣ የተጭበረበረ ነው›› እያሉ ይሳሳቃሉ። የተወሰነው ሰው ደግሞ ‹‹ካልቸገረው ሰው ፊት አይቆምም፤ መርዳት ነው›› እያለ የሚችለውን እየተቀባበለ ያደርስለታል። ሰውዬው የቻለውን ያህል ለምኖ ፌርማታ ጠብቆ ወረደ። 

ትንሽ እንደተጓዝን ከከተማው ወጥተን ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ሳለ በፌርማታ አቅራቢያ አንድ የቤተ ክርስቲያን ልብሰ ተክህኖ ለብሶ፣ መስቀል ጨብጦ፣ ማዕጠንት የያዘ ካህን ይታየኛል። እንደደረስን አውቶብሱ ቆሞ የመሐል በር ተከፈተ። ተሳፋሪው በአብዛኛው በመጨረሻው ፌርማታ የሚወርድ በመሆኑ የወረደ ሰው የለም ከውጪም ከቆመው ባለማዕጠንት ካህን በስተቀር ሌላ ሰው አይታይም። 

መኪናው ቆሞ በሩ እንደተከፈተ ማዕጠንት የያዘው ካህን በእጁ የያዘውን ዕጣን በማዕጠንቱ ባለው ፍም ላይ ጨምሮ ጭሱ ደምቆ መውጣት እንደጀመረ ወደ አውቶብሱ ገባ። ካህኑ በተሳፋሪው መካከል ወደ ፊት ወደ ኋላ እየተጓዘ አውቶብሱን አጠኑ። የልብሰ ተክህኖውን ዘርፍ መስቀሉን በያዘበት በግራ እጁ ዘርግቶ ይዞ በቀኝ እጁ ማዕጠንቱን ያወዛውዛል።

በአውቶብሱ ውስጥ ካለው ተሳፋሪ ብዙዎች ብር እያወጡ ካህኑ በግራ እጁ ዘርግቶ በያዘው የልብሰ ተክህኖው ዘርፍ ላይ ይጥላሉ። አንዳንዱ ጠጋ እያለ በግራ እጅ ወደተያዘው መስቀል ቀረብ ብሎ ይሳለማል። አንዳንዱ ደግሞ መስኮት ከፍቶ የእጣኑን ጢስ ለማስወጣት ይውተረተራል። አንዳንዱ ዓይኑን ቁልጭ ቁልጭ እያደረገ ወደፊት ወደኋላ ያያል። አንዳንዱ በአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛው ውስጥ ሆኖ ያጉረመርማል። ሹፌሩም ካህኑ የሚያደርገውን ፈጽሞ እስከሚወርድ ይጠብቃል።

እኔ አጠገቤ ያለውን ሰው ሁኔታ በጣም እየተከታተልኩ ነበር። በካህኑ ተግባር በጣም ተደስቷል። ለካህኑም ብር ሰጥቷል። ‹‹እሰይ፣ እሰይ እንዲህ ሲያደርጉ ግሸን የምጓዝ ያህል ነው የተሰማኝ›› አለ።  እኔም መለስ ብዬ ‹‹ሁሌም እንደዚህ እየገቡ ያጥናሉ እንዴ›› አልኩት። ‹‹እኔ አልፎ አልፎ ስመጣ እንደዚህ ሲያደርጉ አጋጥሞኛል፤ የአውቶብስ ሾፌሮቹም ይተባበሯቸዋል፤ በጣም ደስ ይላል›› አለኝ። የምለው ጠፍቶኝ በዝምታ ተዋጥኩ። 

ካህኑ ወረደ። አውቶብሱ መጓዝ ጀመረ። እኔ ከተቀመጥኩበት ወንበር ጀርባ ግን አንድ የሚያጉረመርም ሰው ድምፅ ሰማሁ ‹‹ጥፋተኛው ሾፌሩ ነው፤ ይህ እኮ! የሕዝብ ሁሉ መገልገያ አውቶብስ ነው። ዕጣን መታጠን የማይፈልግ ሰው ቢኖርስ! ለምን እንደዚህ ይሆናል። እኔ እኮ ወንጌላዊ አማኝ ነኝ …እያለ አብሮት ላለው የጉዞ ጓዱ ያወራል። ‹‹እነርሱ  ለአገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው…›› ክርክሩ ቀጠለ፤ ‹‹ታዲያ እዚህ ሳይገባ በመስኮት መቀበል ይችላልኮ…› ክርክሩ ቀጥሏል።

የእኔም ትልቁ ትዝብት በመንግስት አውቶብሶች ውስጥ ገብቶ ማዕጠንት ይዞ አውቶብሱን እያጠኑ ገንዘብ መሰብሰብ መቼ ነው የተጀመረው? ለመሆኑ ቤተ ክህነትስ ጉዳዩን ያውቀው ይሆን? ይህንን በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀማለች ወይስ ትጎዳለች? 

በእኔ ትዝብት ግን ተግባሩ በሕግ የሚያስጠይቅ ከመሆን አልፎ ከፍተኛ ግጭት የሚቀሰቅስ ተግባር ነው። እኔ ባየሁት አጋጣሚ የታየው የሙስሊምና ፕሮቴስታንቶች ማጉረምረም፣ የኦርቶዶክሱ ወገን ደስታ ውጤቱ መልካም እንደማይሆን ነው።  

በአውቶብስ ውስጥ ማዕጠንት ይዞ ወጣ ገባ ማለቱስ ከሃይማኖታችን  ሥርዓት አንጻር ምን ያህል ተቀባነት አለው። ሁሉም አማኝ ባልሆነበት፣ ፈቃዱ ባልተጠየቀበት፣ በማን አለብኝነት የሚፈጸም ሥርዓት ውጤቱ የማረ ይሆናል ብዬ አላስብም። ምእመናን የማዕጠንት ሥርዓት በሚፈጸምበት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው በመሳተፍ ከአገልግሎቱ ሊጠቀሙ ሲገባ ወደማይገባ ስፍራ አገልግሎቱን በመውሰድ የንትርክ አጀንዳ መፍጠር አግባብ አይደለም። 

ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳዮች ኖረውት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በወቅቱና በጊዜው ተግባሩን ለመፈጸም እየተጣደፈ ላለ ተሳፋሪ ለአምስትም ይሁን ለዐሥር ደቂቃ ቆሞ ባላቀደው አጋጣሚ ውስጥ መቆየት ላይዋጥለት ይችላል። ቤተ ክርስቲያንን በማክበርና በመውደድ ተባባሪ የሆኑ አውቶቡስ ሾፌሮችም ለሕግ ተጠያቂነት መጋለጥ የለባቸውም።

ስለዚህ ምእመናን የምንወዳቸው እና የምንፈልጋቸው አገልግሎቶች ከጊዜና ከቦታቸው ሲወጡ ለምን ማለት ይገባናል እንጂ ግፋ በለው በማለት ለሀገራችን ሰላም እጦት ምክንያት መሆን የለብንም። የሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርም በየአካባቢዎቹ ያሉ ለፈተና ሊዳርጉን የሚችሉ የካህናት እንቅስቃሴዎችን በምክር ሊያስተካከል ይገባል።

በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን የሚመስሉ (በትክክል ልመናው ለቤተ ክርስቲያን ቢሆን እንኳ) ነገር ግን በብዙ መንገድ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያፈነገጡ እና የሚያስተቹ ድርጊቶች ናቸው። በመሆኑም ሁሉም የሚመለከተው አካል  እንዲህ ዓይነት በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደረጉ ከሥርዓት የወጡ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ሲያይ በቸልታ ሊያልፈው አይገባም እላለሁ።

 

ብቸኝነት እየጎዳኝ ነው ክፍል ሁለት

Details
Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1304
  • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ

፪. ጓደኛ የማጣት የብቸኝነት ፈተናን በተመለከተ በርግጥ ነው ሰው ያለሰው መኖር አይችልም።  ግን ምን አይነት ሰው፣ ከየት ማግኘት ይቻላል? ለሚለው መድኃኔ ዓለም አባታችን በወንጌል “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ወይን፥ ከአሜኬላም በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬ ያፈራል” (ማቴ.፯፥፲፮-፲፱) በማለት ክፉ ሰዎችን እና መልካም ሰዎችን በክፉ ዛፍና በመልካም ዛፍ መስሎ እንዳስተማረ ልንቀርባቸውና ጓደኛ ልናደርጋቸው የሚገባን መልካሞቹን እንደሆነ እንረዳለን።  እነዚህን የምናገኘው ደግሞ ዘወትር ወደ ቤተ እግዚአብሔር ለጸሎትና ለአገልግሎት ከሚገሠግሡት መካከል ነው።  ከእነዚህ ውስጥ መልካሞቹ የሚታወቁት ደግሞ በበጎ ሥራቸው ነው።  ወለተ መድኅን ወደ መድኃኔ ዓለም፣ ወደ እናቱ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወደ ቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ሰማዕታት በጸሎት ደጅ በመጥናት፤ መንፈሳዊ ጓደኞችን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይገባሻል።  በጽሑፍሽ ስለ መንፈሳዊ ሕይወትሽ የገለጥሽው ነገር ባይኖርም ከሥራ ውጪ  ባለሽ ትርፍ ጊዜ ጠዋት እና ማታ ቅዳሜና እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገሠገሥ በመንፈሳውያን ማኅበራት አባል ሆኖ ማገልገል፣ ወደ ገዳማት መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ መንፈሳውያን ጓደኞችን ለማግኘት ይጠቅምሻል። 

፫.በሥራና በግል ሕይወትሽ፤ ስሜትን የሚጎዱ አስተያየት በመስጠትና በመዝለፍ የሚፈትኑሽን በተመለከተም፦ ጠቢቡ ሰሎሞን “ተግሣጽን የሚወድ ዕውቀትን ይወዳል፤ተግሣጽን የሚጠላ ግን ሰነፍ ነው።  የተሻለ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል።  ዐመፀኛ ሰው ግን ቸል ይባላል።  ከዐመፃ የማይርቅ ሰው ይጠፋል፤የጻድቃን ሥር ግን አይነቀልም።” (ምሳ. ፲፪፥፩ )እንዳለ በዚህች ምደር ላይ ሁለት ዓይነት ሰዎች ማለትም ጽድቅን የሚከተሉና ክፋትን የሚፈጽሙ እንዳሉ በሚከተሉት እና በሚፈጽሙት አንፃር የሚገጥማቸውን ያብራራል።  

እኛ ምንም ነገር ቢገጥመን ተግሣጽን ከሚወዱት ወገን ልንሆን ይገባል።  የሚጠሉሽና የሚዘልፉሽ ስለ ሃይማኖትሽ እና ስለ በጎ ሥነ ምግባርሽ ከሆነ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  “ሰዎች ስለሰው ልጅ ቢጠሉአችሁ፥ ከሰው ለይተው ቢአሳድዱአችሁ ቢሰድቡአችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአወጡላችሁ ብፁዓን ናችሁ።” (ሉቃ. ፮፥ ፳፪) በማለት እንደተናገረው ክብር ታገኚበታለሽ እንጂ ስለማትጎጂበት ደስ ሊልሽ ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለክፋትና ስለክፉዎች፤ 

“ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ከክፉ ራቁ፤ በጎውንም ያዙ፤ ለጽድቅ አድሉ፤ እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፤ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።  . . .  የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ . . . ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ።  ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ. . . ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው።” (ሮሜ ፲፪፥፲፬-፳፩) እያለ የመከረንን በሕይወታችን ከተጠቀምንበት የክፉ ሰዎች ባሕርይ አይፈትነንም፤ በትዕግሥት እናሳልፈዋለን።  ትዕግሥት ደግሞ በፈተና ወቅት ለመሸጋገሪያ ዋና መሣሪያ ናት።  ጻድቁ ኢዮብ የታገሠው ደዌውን ብቻ አይደለም፤ ጓደኞቹ በእርሱ ላይ የተናገሩትን ነቀፌታም ጭምር ነው።  በዚህ ምክንያት ልዑል እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ክፉ የተናገሩትን ተቆጥቶ ጻድቁ ኢዮብ ካልጸለየላቸው ምሕረት እንደማያገኙ በነገራቸው መሠረት  በቅዱሱ ጸሎት ይቅርታ ተደርጎላቸዋል።  የእኛን ሕይወት ለመጉዳት ፈተና የሚያመጡብንን ሁሉ በትዕግሥት ካሳለፍናቸው፣ ከጸለይንላቸው ለጊዜው ፈተናቸው ሊያስጨንቀን ቢችልም፤ በኋላ ጸጋና ክብር የምናገኝበት ይሆናል። (ያዕ. ፭፥፲፩፤ኢዮ. ፵፪፥፯-፲) 

፬. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራና የግል ሕይወት የሚያሰናክሉ ድርጊቶች ከመፈጸም አልፎ፤ የትዳር ሕይወትሽን እስከማበላሸት በመድረሳቸው ትዳር መመሥረት መቸገርሽን በተመለከተ፦ የፈጸሙብሽ ድርጊቶች ምን እንደሆኑ፤ ጾታዊ ግንኙነት ማበላሸት ማለት ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ ያለ ፈቃድ ወይም በማታለል የተፈጸመ መሆኑ ስላልተገለጸ፤ በቂ ምክር ለመስጠት ቢያስቸግርም፤ 

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራና የግል ሕይወትን የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶች ያጋጠሙሽ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በድላችሁ የመጣባችሁን ብትታገሡ፥ ምስጋናችሁ ምንድነው? ነገር ግን መልካም እየሠራችሁ፥ የደረሰባችሁን ግፍ ብትታገሡ፥ በእዚአብሔር ዘንድ የምታስመሰግን ይህቺ ናት። ” (፩ኛጴጥ. ፪፥፳) እንዳለው በዚህ ሁኔታ የሚያገኝሽ መከራ ዋጋ የሚያሰጥሽ ስለሆነ፤ ተስፋ ልትቆርጭ አይገባም።  ጾታዊ ግንኙነትን በተመለከተ ያለ ፈቃድ ወይም በመታለል የተፈጸመ ከሆነ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፤  ወደ መምህረ ንስሓሽ ቀርበሽ፤ በሚሰጡሽ ምክርና መመሪያ መሠረት ላንቺ የሚሆንሽን እስክታገኚ፤ በንጽሕና፣ በጾም፣ በጸሎት ተጠብቀሽ፤ የሚስማማሽ፣ የምትስማሚው የትዳር አጋር ስታገኚ፤ በጸሎተ መዓስባን በሥጋ ወደሙ ለማግባት እድሉ ስላለ፤ ተስፋ መቁረጥ የለብሽም።  

በሥራሽ ጣልቃ የሚገቡ ሰዎች ቢኖሩም አንቺ ግን በተፈጠረው ጣልቃ ገብነት ሳትደናገጪ እና ሳትረበሺ በሥራ ቦታሽ ላይ ሥራሽ ካንቺ የሚፈልገውን አቅም ሁሉ በመጠቀም የሰዎችን ባሕርይ መቀየር ትችያለሽ።  በዙሪያሽ ባሉ ሰዎች እና በቅርብ አለቃሽ ዘንድ መልካም የሆነውን ነገር በማድረግ፣ ሥራሽን በቅልጥፍና በመሥራት ማንነትሽንና በሥራሽ አካባቢ ለሁሉም ሰው ቀና አመለካከት በማሳየት ከሌሎች ጋር የሚኖርሽን ግኑኝነት ከበፊቱ የበለጠ ማጠናከር ትችያለሽ። 

፭. በመጨረሻም ብቸኝነቱ የጎዳሽ በመሆኑ፤ ሰው የግድ እንደሚያስፈልግሽ፤ ለዚህም ምክር እንድንለግስሽ ጠይቀሻል።  በእርግጥ ሰዎች ሁሉ አንድ አይደሉም እንደ መልካቸው ሁሉ ባሕሪያቸው ሊለያይ ይችላል።  አንቺም ከአንድ ወይም ከሁለት ሰው ጋር በነበረሽ ግኙኝነት ሁሉም ሰው እንደዚያ ዓይነት ባሕርይ ይኖረዋል ብለሽ መገመት የለብሽም።  ከጥቂት ሰዎች ጋር በነበረሽ ግኑኝነት ሁሉም ሰው እንደዚያ ዓይነት ነው ብለሽ መገመትሽ ሰዎችን ሁሉ እንድትርቂ እና ብቸኛ እንድትሆኚ አድርጎሻል።  ይህ ደግሞ እየዋለ ሲያድር በራስሽ ላይ ያመጣውን ተጽዕኖ ከሐሳብሽ ተረድተናል።  ከሰዎች ጋር መቀራረብ ብትጀምሪ ብዙ መልካም ሰዎች በምድር ላይ እንዳሉ ታያለሽና።  በተጨማሪም ከብቸኝነት ለመዳን ግዴታ መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን በማኅበራት፣ በሰንበቴ፣ በዕድር፣ በሰንበት ት/ቤት፣ በሠፈር ወ.ዘ.ተ. ጓደኛ ማፍራት ይቻላል።  እኅታችን አንችም በነዚህ ማኅበራዊ ተቋማት በመሳተፍ ማኅበራዊ ሕይወትሽን ማጠናከር ትችያለሽ። 

ጋብቻን በተመለከተ ምንም እንኳን ቀጥተኛ ጥያቄ ባይሆንም ጠቢቡ ሰሎሞን “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል።  አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ያነሣዋልና፥ አንድ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት።  ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ አንድ ብቻውን ግን  እንዴት ይሞቀዋል? አንዱም ሌላውን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፤ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም። ” (መክ. ፬፥፱-፲፪) በማለት እንደገለጸው አንቺም በተግባር በማየትሽ ጓደኛ እንዴት ማግኘት እችላለሁ በማለት ላቀረብሽው ጥያቄ ከላይ በቁጥር ፪ ከሰጠነው ምክር በተጨማሪ ጓደኛ ወይም ወዳጅ ስንይዝ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊሆን ይገባዋል።  ከጠላቶቻችን ይልቅ ወዳጅ መስለው የሚመጡብን ጠላቶች ስላሉ መጠንቀቅ ተገቢ እንደሆነ ጠቢቡ ሰለሞን “ ከጠላቶችህ ራቅ፤ ወዳጆችህንም ተጠባበቃቸው።  . . .የታመነ ወዳጅ የሕይወት መድኃኒት ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚፈሩ ያገኙታል” (ሲራ.፮፥፲፫-፲፮ ) በማለት ምክር ተሰጥቶናል።  ስለዚህ ሕጉን ትእዛዙን በማክበር ለእርሱ በመገዛት በጸሎት ደጅ በመጥናት እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት ይቻላል።  ተጨማሪ ምክር የሚያስፈልግሽ ከሆነ በዝግጅት ክፍላችን ስልክ ቁጥር ብትደውዪ ከመምህራን ጋር ልናገናኝሽ እንችላለን።  

ውድ እኅታችን ወለተ መድኅን እነዚህን ምክሮች ተጠቅመሽ ከገጠመሽ ፈተና ነፃ ለመውጣት፤ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳሽ፤ የወላዲተ አምላክ አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን የሰማዕታት ቃል ኪዳን አይለይሽ። 

የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሕንፃ እድሳት ተጠናቆ ተመረቀ

Details
Written by: በጋዜጣው ሪፖርተር
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1251
  • አጫጭር ዜናዎች
የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሕንፃ  እድሳት ተጠናቆ ተመረቀ

የአጤ ምኒሊክ መታሰቢያ የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እድሳት ከተጠናቀቀ በኋላ በቅዱስነታቸው ተባርኮ ታቦተ ሕጉ ቅዳሜ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም   ወደ መንበረ ክብሩ ተመለሰ፡፡ በዕለቱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች ፣ የአድባራት እና የገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ካህናት እና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡  

የገዳሙ ሕንፃ እድሳት ፵ ሚሊዮን ብር ያህል መፍጀቱን የሕንፃው አሠሪ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ በሀገር ውስጥ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውጪ በሰሜን አሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ ከሚገኙ የቀድሞ የገዳሟ ካህናት አገልጋዮች እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ያካተተ ንዑሳን ኮሚቴን በማዋቀር በርካታ የገቢ ማባሰብ ሥራዎች መሥራት መቻሉ 

ተጠቅሷል፡፡  በአንድ ዓመት ተኩል ሊጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የገዳሙ ሕንፃ እድሳት የኮቪድ-፲፱ ወረርሺኝ ባስከተለው ተፅዕኖ ምክንያት ሁለት ዓመታት ያህል መፍጀቱን ከሕንፃው አሠሪ ኮሚቴ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙና እንዲጎበኙ ከተመረጡ ዐሥር ቦታዎች ውስጥ አንዷ የሆነቸው የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ለዳግማዊ አጤ ምኒልክ መታሰቢያነት በልጃቸው በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ነው የተሠራቸው፡፡ በገዳሟ ሙዚየም ውስጥ አባቶቻችን አድዋ ይዘውት የዘመቱት መስቀል፣ ከውጪ ነገሥታት ለአጤ ምኒሊክ የተበረከቱ ስጦታዎች እንዲሁም የተለያዩ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ከ፻ ዓመት በኋላ እድሳት የተደረገላት የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የአጤ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱ፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲሁም የመጀመሪያው ግብፃዊ ጳጳስ የአቡነ ማቴዎስ አፅም እንደሚገኝባት ይታወቃል፡፡

የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም በ፲፱፻፲ ዓ.ም ቦታውን የመጥረግ ሥራ በመጀመር የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ የግንባታው ሥራ ዐሥር ዓመታት የፈጀ ሲሆን በ፲፱፻፳ ዓ.ም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠናቆ ጽላቷን ከጎንደር በማስመጣት ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፳ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ መከበሩን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ 

ጾም

Details
Written by: ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 26 December 2020
Hits: 1264
  • የሕፃናት ዓምድ

የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁ? መልካም፤ እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን።  ባላችሁበት ሆናችሁ ትምህርታችሁን  በጥሞና ተከታተሉ! 

ልጆች! ለዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ትምህርት ስለ ጾም ነው።  በመጀመሪያ ጾም ምን ማለት እንደሆነ እና እናንተ ሕፃናት ከሰባት ዓመት ዕድሜያችሁ ጀምሮ እንዴት መጾም እንዳለባችሁ እናስተምራችኋለን።  

ልጆች! ጾም ማለት ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ ለተወሰነ ጊዜና ሰዓት ከእህል ከውኃ ተከልክሎ መቆየት ማለት ሲሆን ከሥጋ፣ ከቅቤና፣ ከእንቁላል ደግሞ እንድንጾምባቸው የተወሰኑ የአጽዋማት ሳምንታት እስኪጠናቀቁ የምንከለከልበት ወቅት ማለት ነው።  (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭)

ከዚያም በተጨማሪ ጾም ዓይን ክፉ ከማየት ጆሮ ክፉ ከመስማት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ እጅ ክፉ ከመሥራት በአጠቃላይ ሰውነት የኀጢአት ሥራ ከመሥራት የሚገታበት፣ የሚከለከልበት ሁኔታ ማለት ነው።  

ጾም የአዋጅ እና የፈቃድ ተብሎ በሁለት ይከፈላል።  

ሀ. የዐዋጅ ጾም

የዐዋጅ አጽዋማት በቤተ ክርስቲያን ለምእመናን ሁሉ አውቀውት በአንድነት የሚጾም ጾም ነው።  ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው።  ‹‹በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ ጉባኤውንም ዐውጁ›› (ኢዩ. ፪፥፲፭)

የዐዋጅ ጾሞች ሰባት ናቸው።  እነርሱም፤ የነቢያት ጾም፣ የገሃድ ጾም፣ የነነዌ ጾም፣ ዐቢይ ጾም፣ የሐዋርያት ጾም፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ)፣ ጾመ ፍልሰታ ናቸው።  

 ለ. የፈቃድ ጾም

የፈቃድ ጾም  ደግሞ ራሳችን አስበንና ፈልገን የምንጾመው ጾም ነው።  የፈቃድ ጾም ሁለት ናቸው፤ የጽጌ ጾም እና ጾመ ዮዲት ተብለውም ይጠራሉ።  ይህም ጥፋት ወይንም ኀጢአት ስንሠራ ለንስሓ (ይቅርታን ለማግኘት) ስለሚረዳን እንጾመዋለን።   

ልጆች! እያንዳንዱን ጾም የምንጾምበት ምክንያት አለን።  ለምሳሌ አሁን ያለንበት ወቅት የነቢያት ጾም የሚጾምበት ነው፤ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፰ ድረስም ይጾማል።  

ይህን ጾም ነቢያት የአምላክን መወለድ በተስፋ በመጠበቅ ስለጾሙት እኛም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ተወልዶ እንዳዳነን በማመን እስከ የልደት በዓል ዋዜማ ታኅሣሥ ፳፰ ድረስ እንጾመዋለን።  

ልጆች! ወደፊት ስለተቀሩት የዐዋጅ እና የፈቃድ አጽዋማት ወቅታቸውን እየጠበቅን በተናጠል እናስተምራችኋለን።  ለዛሬ ግን በዚህ ይብቃን፤ በሚቀጥለው ትምህርታችን እስክንገናኝ በጸሎትና ጾም እንድትበረቱ እንመክራችኋለን፤ በደኅናም ሰንብቱ!

የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነትና የእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለያችሁ።  

Page 12 of 19

  • 7
  • 8
  • 9
  • 10
  • 11
  • 12
  • 13
  • 14
  • 15
  • 16

የቅጅ መብት © ማኅበረ ቅዱሳን 2012 ዓ.ም.

ዋናው ማዕከል | Afaan Oromoo | English |አሜሪካ ማዕከል | አውሮፓ ማዕከል | ካናዳ ማዕከል | ትሩፋት
MK Facebook MK Telegram MK Youtube
አጫጭር ዜናዎች የሕፃናት ዓምድ ትዝብት ሪፖርታዥ ቤተ አብርሃም ፍሬ ከናፍር ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ርዕሰ አንቀጽ Oct ኪነ ጥበብ June ዐውደ ስብከት sept እናስተዋውቃችሁ ትምህርተ ሃይማኖት Nov Mar Apr ዐቢይ ጉዳይ ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት የነገዋ ቤተ ክርስቲያን የጥያቄያዎቻችሁ መልስ July የማኅበሩ መልእክት Jan Aug May 1997 13 ከዓለም ማእዘናት