- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1067
በዓለማችን ያሉ ብዙ ሀገራት በየአራት ወይም በየአምስት ዓመታት ልዩነት ሀገራዊ ምርጫ ያካሄዳሉ። በየሀገራቱ ያሉ ሕዝቦችም “ይበጀናል ለውጥ ያመጣልናል” ያሉትን የፖለቲካ ድርጅት በካርዳቸው አማካይነት ይመርጣሉ። የፖለቲካ ድርጅቶችም ከምርጫው ጊዜ ቀደም ብሎ “ሕዝብን ያሳምንልናል፤ እንድንመረጥ ያግዘናል” የሚሉትን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም በዐደባባይ ወጥተው ያስተዋውቃሉ። አንዳንዴ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁና በምርጫው አሸናፊ የሆነውን አካል እንኳን ደስ አለህ/ አለሽ ተባብሎ የመለያየቱ ጉዳይ ግን አሳሳቢ ይሆናል። በምርጫ ወቅት የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ ሀብት ንብረት ይወድማል፤ የሀገር ሉዓላዊነትም አደጋ ላይ ይወድቃል።
በተለይ በአፍሪካና በአንዳንድ ታዳጊ ሀገራት ሀገራዊ ምርጫ ያለስጋትና ያለፀጥታ ችግር የሚጠናቀቅባቸው ጊዜያት ውስን ይሆናሉ። በሀገራችን ባለፉት አምስት ዙር የተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች ለፀጥታ ችግር የተጋለጡ ሆነው አልፈዋል። በምርጫዎቹ ወቅት የሰው ሕይዎት ያለአግባብ የጠፋበት፤ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በአንዳንድ ዕብሪተኛ የፖለቲካ ኃይሎች ሥርዓቷ፣ቀኖናዋ፣ዶግማዋ፣ክብሯና መብቷ የተጣሰባቸው ዓመታትን አሳልፈናል። ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በሀገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ኃይል በስሑት ትርክት ተነሣሥቶ ቤተ ክርቲያንን “በጠላትነት” በመፈረጅ እውነተኛ አገልጋይ አባቶችና ምእመናን ተሸማቀው እንዲኖሩና በእምነታቸው እንዲያፍሩ ሲደርግ ቆይቷል።
በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ በሀገራችን ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ምርጫ ቦርድ መርሐ ግብር አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም በዚህ ወሳኝ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በየዐደባባዩ እየዞሩ ፖለቲካዊ አማራጭ ሐሳባቸውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንም የሀገሪቱ አካል ናቸውና በምርጫው ወቅት ሊኖራቸው ስለሚገባው ድርሻ አስመልክቶ ከጅቡቲና ድሬደዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኃላፊ ከሆኑት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዶ/ር ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።
ስምዐ ጽድቅ፡- በሀገሪቱ ሊካሄድ የታሰበው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በምን ሁኔታ ሊከናወን፣ በምርጫው ወቅትስ ምእመናን ምን ዓይነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ?
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- ሀገራዊ ምርጫ ማለት ሕዝብን ለማስተዳደርና ለመምራት የሕዝብን እውነተኛ ድምፅ ለማግኘት የሚካሄድ አንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። የሀገራዊ ምርጫ ዋናው ግብ ሕዝባዊ ይሁንታን አግኝቶ ሀገርንና ሕዝብን መምራት ነው። በሀገራዊ ምርጫ ወቅት ገዥው የፖለቲካ ድርጅትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የየራሳቸውን ሐሳብ ለኅብረተሰቡ በመግለጽ የፖለቲካ መንበርን የሚይዙበት ሂደትም ነው። ስለዚህ በሀገራችን ሊደረግ በሂደት ላይ ያለው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን እንመኛለን።
ምርጫው የኢትዮጵያዊነትን ዕሴት፣ አንድነት፣ ፍቅርንና መተሳሰብን የሚሸረሽር ሆኖ መከናወን የለበትም። የፖለቲካ ድርጅቶች አለን የሚሉትን አማራጭ ሐሳባቸውን ለኅብረተሰቡ በመግለጽ በፍትሐዊነት የመንግሥትን መንበረ ሥልጣን የሚይዙ፤ የሀገርን ሰላምና ዕድገት ለማሻሻል ጥረት የሚያደርጉ መሆን አለባቸው። ሀገራዊ ምርጫው በብሔርና በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት በኢትዮጵያውያን መካከል የተፈጠረውን ቁርሾና የኢኮኖሚ ውድቀት የሚያስወግድ ምርጫ ሊሆን ይገባል። በሕዝቦች መካከል ጠብ የሚዘሩና መለያየትን የሚሰብኩ አካላት ጭምር ሥርዓት የሚይዙበትና ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ኃያልነቷ ተመልሳ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ብቻ ሳትሆን ለሌሎች ክፍላተ አህጉር ምሳሌ የሆነ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድባትም የሁሉም ፍላጎት ሊሆን ይገባል።
የሃይማኖት ተቋማት ነፃነት ተከብሮ ሰው በፈለገው ቦታ ሆኖ ማምለክ የሚችልበት ዘመን እንዲመጣ እንመኛለን። በተለይ ከዚህ ቀደም የነበረው መንግሥታዊ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን የተበደሉበትና የተገፉበት ሥርዓት ነበር። አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በስሑት ትርክት ተነሣሥስተው ቤተ ክርስቲያንን “በጠላትነት” ከመፈረጅ ባሻገር “የጭቆና፣ የድህነትና የኋላ ቀርነት” ምሳሌ አድርገው ሲያቀርቧት ይስተዋሉ ነበር። ይህ ግን የተሳሳተ፣ ቤተ ክርስቲያን ለሀገርና ለወገን የከፈለችውን ታላቅ ዋጋ የካደ ልዕልናዋንም ያላከበረ ትርክት ነው።
በመጭው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ተወዳድረው የሚያሸንፉ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳሳቱ ትርክቶችን የሚያርሙና ቢቻል በስሑት ትርክት ምክንያት ላለፉት ፵ ዓመታት ጉዳት የደረሰባትን ቤተ ክርስቲያን የሚክሱና ይቅርታ መጠየቅ የሚችል ቅን ልቡና ያላቸው መሆን አለባቸው። በዚህ ዘመን ያለን ሕዝበ ክርስቲያንም የስሑት ትርክት ማወራረጃ መሆን እንደሌለብን ጠንቅቀን በማወቅ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያበቃንን ካርድም በመውሰድ በግብታዊነት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያናችንና ለምእመናን የሚጠቅመውን የፖለቲካ ድርጅት መምረጥ ይጠበቅብናል።
በሀገራችን ለምርጫ ውድድር የቀረቡት የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያቀርቡትን ፖለቲካዊ አማራጭ ሐሳብ ምእመናን በትክክል መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ከመምረጥ ባሻገር በምርጫው ወቅት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማገዝና ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። የዘመኑ አሰላለፍ መቀየሩን አውቀን ህልውናችንን ሊያስጠብቅልን የሚችለውን የፖለቲካ ድርጅት መምርጥ የማንችል ከሆነ ዘላለም የችግር ሁሉ ገፈት ቀማሽ፤ አቤቱታ አቅራቢና ኀዘንተኞች እንሆናለን። ለኀዘናችን ማስታገሻ ስንልም በእምነትና በምግባር ለማይመስለን መንግሥት “ተገፋን” ብለን ድምጻችን ስናሰማ ለሀገር ከምናበረክተው ድርሻ እንወጣለን።
ስምዐ ጽድቅ፡- ቤተ ክርስቲያን የተከፈተባትን ስሑት ትርክት ለማረም፤ የቤተ ክርስቲያንንና የምእመናንን ደኅንነትም ለማስጠበቅ ስለ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት እያደረገች ነው?
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- ቤተ ክርስቲያንን በስሑት ትርክት የመወንጀል ምንጩ ምዕራባውያን ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ሀገር መሆኗንና በአድዋ ድል ላይ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ስለሚያውቁ ያን መበቀል ይፈልጋሉ። ለሀገር ውስጥ ፀረ-ኦርቶዶክስ ኃይላት የገንዘብ ድጎማ በማድረግ ጭምር ቤተ ክርስቲያንን በስሑት ትርክት የመወንጀል ሥራ ይሠራሉ። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ማስተዋል አለባቸው፤ የስሑት ትርክት ምንጩ የትና እነማን መሆናቸውን በመለየት ለእርሱ የሚሆን ስልት መንደፍ አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ግንባታና አንድነት ትልቅ ሚና እንደተጫወተች ምእመናንም ሆኑ የመንግሥትን የሥልጣን መንበር የሚይዙ አካላት ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል። ሆን ተብሎ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲነዙ የነበሩ የሐሰት ትርክቶች የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት ከግምት ውስጥ ያላስገቡና የኢትዮጵያንም ሉዓላዊነትና ነፃነት ለመናድ የሚቀነቀኑ ሴራዎች ነበሩ።
የቤተ ክርስቲያን ኃያልነትና ለሀገር ያበረከታችው አስተዋፅኦ አንድ ቀን ይገለጣል፤ ዓለምም ዐይኑን ገልጦ ልቡናውንም ከፍቶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሙሉ ልቡ ይቀበላታል። ቤተ ክርስቲያን ፍትሐዊነትን ያስተማረችና ድኃ እንዳይበደል ፍትሕ እንዳይጓደል ጠንክራ የሠራች ናት። ቤተ ክርስቲያን ለሀገርና ሕዝብ ጠቃሚ የሆነችና ለአፍሪካ ጥቁር ሕዝብም የነፃነት ፋና ወጊ የሆነች እንዲሁም ለዓለም ሕዝብ ታሪክን፣ ቅርስንና ሃይማኖትን ጠብቃ ያቆየች ናት። የሀገራችን የማኅበረሰብ አንቂዎችም ሆኑ የፖለቲካና የታሪክ ምሁራንም ይንን ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ተረድተው ለእውነት መቆም አለባቸው።
ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ጊዜ የሐሰት ትርክት ሰለባ ብትሆንም ክብሯና ለሀገር የምታበረክተው ድርሻ አይቀንስም። ሰዎች ዓይናቸውን ገልጠው እስኪያዩ ድረስ እውነቱን በተገቢ መንገድ ማስረዳት የእኛ አባቶች ድርሻና የምእመናን ሊሆን ይገባል። ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያን የነበራትን ሀገራዊ ድርሻ ለማስቀጠል መጪው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሓዊና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻዋን ትወጣለች፤ ምእመናንዋም በድጋሜ ዋጋ እንዳይከፍሉ በምርጫው ወቅት በጥንቃቄ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ትመክራለች።
ስምዐ ጽድቅ፡- የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ሕልውና አስመልክቶ በሀገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተደረገ ውይይት አለ?
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- እስካሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ሕልውና አስመልክቶ በሀገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተደረገ ምንም ዓይነት ውይይት የለም። ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ድርጅቶችን ጠርታ ማነጋገሩ ጠቃሚ ነው ብላ ባለማመኗ ውይይት አላደረገችም። ነገር ግን በምርጫ ወቅት የምርጫ ሕጎችና ደምቦች እንዳይጣሱ፣ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድምና የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት የሚሸረሽሩ ጉዳዮች እንዳይከሠቱ ቤተ ክርስቲያን የመካሪነትና የአስተማሪነት ድርሻዋን በሚገባ ትወጣለች።
የፖለቲካ ድርጅቶች የሕዝብን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ መጭውን ምርጫ እንዲያካሂዱ ቤተ ክርስቲያን ትመክራለች። ለምእመናንም ያመኑበትንና መብታቸውንና ጥቅማቸውን ሊያስከብርላቸው የሚችለውን የፖለቲካ ድርጅት እንዲመርጡ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ ታስተላልፋለች፤ እንዲሁም በምርጫው ወቅት ከሁከትና ብጥብጥ እንዲቆጠቡና ከግርግር እንዲርቁ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች።
ስምዐ ጽድቅ፡- የቤተ ክርስቲያን ልጆች በሀገሪቱ የፖለቲካ ሱታፌ ውስጥ የፖለቲካ ውክልና የማያገኙት ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ተሳትፎን “በመጥፎ ስላ ስለምትመለከተው ነው” ይባላልና በዚህ ላይ ምን ሐሳብ አለዎት?
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- ይህ ሐሳብ ከእውነታው ጋር በተቃርኖ የቆመ ነው። በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ ከነበሩ መንግሥታት ጋር ትወግን ነበር ይባላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ልጆቿ የፖለቲካ ውክልና እንዳይኖራቸው ክልከላ አድርጋለች ይባላል። እውነታው ግን ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳያደርጉ አልከለከለችም፤ ከልክላም አታውቅም። የፖለቲካ ተሳትፎንም በጎ ባልሆነ ዕይታ ቃኝታ አላስተማረችም። ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎን በራሳቸው ምክንያት ሸሽተው ‹‹ቤተ ክርስቲያን ናት የከለከለችን›› ብሎ ማቅረብ ፍጹም ስሕተት ነው። ከዚህ በኋላ ሁላችንም ፖለቲካን የምናይበት ዕይታ የተስተካከለ መሆን አለበት። ፖለቲካን አስፈሪ በሆነ መንገድ መመልከት መቆም አለበት።
በአሁኑ ሰዓት መብትንና ጥቅምን ለማስከበር የግድ የፖለቲካ ተሳትፎን የሚጠይቅ ወቅት ላይ እንገኛለን። ቤተ ክርስቲያን እጅግ ሊቅ የሆኑ ልጆች አሏት፤ እነዚህ ራሳቸውን ሳይደብቁ በዐደባባይ በመውጣት በፖለቲካ ተወክለው የቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን መብትና ጥቅም ሊያስከብሩ ይገባል። ዕውቀታቸውን ለሕዝባቸው ሰላምና ልማት ሊያውሉት ያስፈልጋል። የሀርን ልማት፣ አንድነትና ሰላም የሚያስጠብቅ የፖለቲካ ርዕዮተን ዓለም ይዘው በመቅረብ ተመራጭ የፖለቲካ ሰዎች እንዲሆኑ ጠንክረው መሥራትም ይጠበቅባቸዋል።
አንዳንድ የዓለማችን ሀገራት ‹‹ክርስቲያናዊ የፖለቲካ ድርጅት›› መሥርተው የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ሁሉ የእኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችም የሀገሪቱን ሕግ መሠረት አድርገው ኦርቶዶክሳዊ የፖለቲካ ድርጅት መሥርተው እስከ መንቀሳቀስ ደረጃ መድረስ አለባቸው። በአንዳንድ የዓለማችን ሀገራት ማለትም በኖሮዊ፣ ጀርመን እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ካህናት አባቶች በምርጫ ተወዳድረው አሸንፈው የሀገር መሪ እስከመሆን ደርሰዋል። በእኛ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ካህናት በፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ባይፈቀድም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን ተሳታፊ መሆን አለባቸው። ካህናት አባቶች ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ትኩረት እንዲሰጡ ከማድረግ ውጪ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ እንዲሳተፉ አትፈቅድም። የቤተ ክርስቲያን አስታራቂነት ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ ልጆቿ ፓርላማ ውስጥ ገብተው በሀገሪቱ በሚወሰኑ ማንኛውም ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በዚህ ሁኔታ የፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆኑ ታግዛለች። ይህ ካልሆነ ግን በቤተ ክርስቲያንና በሀገር ላይ የሚወሰኑ የፖለቲካ ውሳኔዎችን እንደማንኛውም ገለልተኛ አካል በቴሌቭዥን ከማየት የዘለለ ዕድል አይኖራቸውም።
መንግሥት ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ሃይማኖት የሚወስነው ውሳኔ የሚኖር ከሆነ በፓርላማ ውስጥ ተገኝተው የሚከራከሩና ሐሳብ የሚሰጡ ተወካዮች ከሌሉ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንቱ ጉዳቷ የበለጠ በዚህ ዘመን ትጎዳለች። በራስ ድክመትና ቸልተኝነት ቤተ ክርስቲያንን መውቀስ ግን ተገቢ አይደለም። ቤተ ክርስቲያን እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ መሪዎቿን እየቀባች ስታነግሥ ኖራለች። በኋላ ላይም ርዕዮተ ዓለሙ ተቀይሮ ስትገፋ ቆይታለች።
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጫናውን መቋቋም ሲያቅታቸው ክርስትናን ሳይቀር በድብቅ ማስፈጸም መጀመራቸውን እናቀውቃለን። ከዚህ በኋላ የፖለቲካ ሥልጣን ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቤተ ክርስቲያን ስትገፋ፣ ክብሯና መብቷ ሲገፈፍ በታዛቢነት ማየት የለባቸውም። ሊሟገቱላት፣ ሊከራከሩላት ክብሯንና መብቷን ሊያስጠብቁላት ይገባል።
ቤተ ክህነቱን ባሉባልታ ከመተቸት ይልቅ የፖለቲካ ተሳታፊ የሆኑ ምእመናን የራሳቸውን ድርሻ መወጣት፤ የቤተ ክህነቱን ጉድለት ደግሞ እንዲስተካከል የተጠናና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሐሳብ አስተያየት መስጠት አለባቸው። ልጆቻችን ከአባቶች ጋር አላስፈላጊ የሆነ ንትርክ ከማድረግ ወጥተው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን በጠቅም ከሚችል የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ መግባት አለባቸው። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በዚህ ወቅት በሚኒስቴር ደረጃና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እየሠሩ ይገኛሉ። በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ጭምር በከፍተኛ ኃላፊነት እያገለገሉ ያሉ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አሉ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከፖለቲካ ውክልና እንዲርቁ አታደርግም።
በተለይ በአገልግሎት ተቋማት በኃላፊነት ላይ ያሉ ልጆቻችን እምነታቸውን በነፃነት የማምለክና የመግለጥ ድክመት አለባቸው። በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ በእምነታቸው በማፈር በመሸማቀቅ እንዲሁም ኦርቶዶክስ መሆናቸው እንዳይታወቅባቸው ሆነው ሥራን የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ኦርቶዶክሳዊነታቸውን ሳይደብቁ በኩራት አውጥተው ገልጠው የሚሠሩም በርካቶች ናቸው። ቤተ ክርስቲያንም እንደነዚህ ያሉ ልጆቿን በደንብ ታበረታታለች፤ በቅርበትም ትከታተላለች፣ ትመክራለች፣ ታስተምራለችም። በሌላ የእምነት ተቋማት ሥር ያሉ አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች በዐደባባይ ሳይፈሩ ሳይሸማቀቁ እምነታቸውን ያስተዋውቃሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ ወደጎን ትተው ለሚከተሉት እምነት ያድራሉ። የእኛ ቤተ ክርስቲያንና ልጆቻችንም ከእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ትምህርት መውሰድ አለባቸው።
ስምዐ ጽድቅ፡- በመጨረሻም ቀረ የሚሉት ነገረ ካለ?
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- ሀገራዊ ምርጫ ሲባል ሀገርን የሚወክልና የሀገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስን በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብተው የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ፣ ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቅ የፖለቲካ ድርጅት ለመምረጥ መዘጋጀት አለባቸው። ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን የፖለቲካ ድርጅት ከምርጫ በፊት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ሀገራችን መልካም ስሟና አንድነቷ ተጠብቆ እንድትዘልቅ እንፈልጋለን። ሁሉም ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን እንመኛለን። ሁሉም ዜጋ በሀገሪቱ ባሉ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ የሚሠራባትና የሃይማኖት ነፃነትን የምታከብር እንድትሆንና መጪው ምርጫ ፍትሓዊና ተአማኒ እንዲሆን መሥራት የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል።
ገዥው መንግሥትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመልካም ዕይታ እንዲያዩና ለሀገርና ለወገን ያበረከተችውን ድረሻ እንዲረዱ እናሳስባለን። የፖለቲካ ድርጅቶች ቢሆኑ ቤተ ክርስቲያን ማንንም እንዳልበደለችና እንዳልጨቆነች መረዳት ይኖርባቸዋል። ከአርባ ዓመታት ወዲህ ሆን ተብሎ የጭቆና ማዕከል ስትደረግ እንደቆየች መገንዘብ ተገቢ ነው። ቤተ ክርስቲያን በሀገራችን በኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ባልነበረበት ወቅት ፊደል አስቆጥራለች፤ ታሪክ አቆይታለች፤ ሥነ ጥበብን፣ መድኃኒት ቅመማን፣ የዘመን አቆጣጠርን አስተምራለች። በሀገራችን አራቱም አቅጣጫዎች ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አሻራዎች አሉ፤ እነዚያ ሁሉ የሀገር ሀብት ናቸው።
በሀገራችን ውስጥ እተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲካሄዱ የነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ባለመቀበል፤ ከቤተ ክርስቲያን ጎን በመቆም ለማረም ጥረት ቢያደርጉ መልካም ነው። ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስሕተቶች ድጋሜ እንዳይፈጸሙ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በምርጫው ወቅት ብጥብጥ እንዳይፈጠር ከዚህም ጋር ተያይዞ በወገኖቻችን ላይ ሃይማኖት ተኮር ጥቃት እንዳይፈጸም የፀጥታ አካላት ቀድመው ሊሠሩ ይገባል። በአንዳንድ አካባቢዎች ምርጫን ጨምሮ የፖለቲካ ለውጥ ሲካሄድ ቤተ ክርስቲያንና ኦርቶዶክሳውያን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ከዚህ ቀደም ካየናቸው ተግባራት እንገነዘባለን። በዚህ ወቅት ጥቃት የሚያደርሱ አካላት በስሑት ትርክት የተሞሉና ‹‹የእኔ›› የሚሉትን ሃይማኖት በኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ላይ ለመጫን የሚያልሙ ኃይላት ናቸው። ይህ ተግባር እንዳይፈጸም መንግሥት ከወዲሁ የሀገራችንን ችግር ስስ ብልት ለይቶ በማወቅ ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። ምርጫ ቦርድም የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል ማድረግ ያለበትን ሁሉ ሊያደርግ ይገባል።
ስምዐ ጽድቅ፡- አባታችን ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ውድ ጊዜዎትን ሠውተው ለቃለ መጠይቃችን ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍላችን ስም እናመሰግናለን።
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1226
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሰሞኑን በኦሮምያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ወለጋ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ ዴቢስ ቀበሌ በታጣቂዎች ለተገደሉ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ድጋፍ እንደምታደርግ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ማስታወቃቸውን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነበበ።
ቅዱስነታቸው ይህንን ያስታወቁት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማት በጻፉት የአጋርነትና የድጋፍ ደብዳቤ እንደሆነ ዘገባው አስረድቷል።
በንጹሓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እንዳሳዘነ የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ለሟቾች እንጸልያለን ብለዋል። በሃይማኖታቸው ብቻ ግፍና በደል ለሚደርስባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።
ሰሞኑን በኦሮምያ ክልል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ በተፈጸመ አሰቃቂ ጥቃት በርካታ ምእመናን፣ እናቶች፣ ሕፃናትና ካህናት መገደላቸውን ቅዱስነታቸው በላኩት ደብዳቤ አስታውሰው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል።
በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው አሰቃቂ ጥቃት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ ያሳሰበ ጉዳይ መሆኑን የገለጡት ቅዱሰነታቸው ቤተ ክርስቲያናቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በሀገራቸው በነፃነትና በደኅንነት እንዲኖሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ “ቃል እገባለሁ” ሲሉ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳውቀዋል።
“በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእምነታቸው ምክንያት የሚገደሉ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ፍትሕ እንደሚያገኙ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለታቸውንም ከደብዳቤው መረዳት ተችሏል። የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በእምነታቸው ምክንያት በሚሰደዱ ኢትዮጵያውያንና በሌሎች ቦታዎች የሚገኙ ክርስቲያኖችን ከጥቃት ለመከላከል ቁርጠኛና ግንባር ቀደም እንደሚሆኑ ቅዱስነታቸው የገልጠዋል።
እ.ኤ.አ በታኅሳስ 2020 ‹‹የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ከጥቃት መከላከል›› በሚል ስያሜ የተካሄደው የቪዲዮ ኮንፈረንስ የተዘጋጀው በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በሩሲያ የሃይማኖት ነፃነት አስጠባቂ ማኅበራት አነሳሽነት መሆኑ ተገልጿል። ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ፣ የፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ማኅበር የኮንፈረንሱ አጋሮች ከተሳታፊዎች መካከል እንደነበሩ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።
- Details
- Written by: እህተ ሚካኤል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1171
ልጆች! ባለፈው እትማችን ላይ ስለ ዐቢይ ጾም(ጾመ ሁዳዴ) እንዲሁም በጾመ ሁዳዴ ውስጥ የሚገኙ ሳምንታት የየራሳቸው መጠሪያ እንዳላቸው ነግረናችሁ ነበር አስታወሳችሁ? መልካም። የዐቢይ ጾም ሳምንታት ከተሰጣቸው መጠሪያዎች ውስጥ የመጀመሪያውንና የሁለተኛውን ሳምንት ስያሜ ‹‹ ዘወረደ›› እና ‹‹ ቅድስት›› እንደሚባሉ ነግረናችሁ ነበር። እነሆ በዚህ ዝግጅት ቀጥሎ ስላሉት ሁለት ሳምንታት ስለ ‹‹ምኩራብ›› እና ስለ ‹‹መጻጉዕ›› እንነግራችኋለን ተከታተሉን።
3. ምኲራብ
ልጆች! ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ምኲራብ በመባል ይጠራል። ይህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ያስተማረበት ቀን ነው።
ልጆች! የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ምኩራብን ‹‹ የአይሁድ የጸሎት ቤት ›› በማለት ይፈታዋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና በሥርዓቱ የተመሠረተ ነበር። ናቡከደነጾር ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ስፍራዎች ሁሉ ምኲራብ ሊሠሩ እንደጀመሩ ይገመታል። በእስራኤል ሀገር በየቦታው በኢየሩሳሌም ብዙ ምኲራቦች ነበሩ። ሐዋርያትም አይሁዶች በተሰበሰቡባቸው ቦታዎች ሲዘዋወሩ አስቀድመው ወደ ምኲራቦች ገብተው ወንጌልን ያስተምሩ ነበር ይላል። ማቴ ፬፥፳፫ ፤ ሐ.ሥ ፮፥፱
ልጆች በምኩራብ ውስጥ የሕግ እና የነቢያት መጻህፍት የብራና ጥራዞች በሳጥን ውስጥ ይቀመጣሉ። የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብ መጽሐፉን የሚያነበው ሰው በደንብ እንዲሰማና እንዲታይ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ቆሞ ያነብ ነበር። የክብር ወንበሮች ከዚህ ቦታ ፊት ለፊት ነበሩ ማቴ ፳፫፥፮ ። ወንዶችና ሴቶች ለየብቻቸው ይቀመጡ ነበር።
ምኲራብ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት በአይሁድ የተሰራ የጸሎት ቤት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ተመላልሶ በሚያስተምርበት ጊዜ በአይሁድ ምኲራብ ገብቶ ያስተምር ነበር።
ልጆች! የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ስለነበር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ወደ አይሁድ ምኲራብ ገባ። ጌታችን ወደ አይሁድ ምኲራብ የገባው የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተማር ነበር። ነገር ግን በቤተ መቅደሱ ብዙ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በሬ፣ ላም፣ ፍየል፣ ርግብ የመሳሰሉትን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይሸጡ ይለውጡ ነበር። ጌታችን በተከበረው የእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ብዙ ጫጫታም የማይገባ ነገርም ሲደረግ ተመለከተ። ጅራፍንም ውስዶ ሻጮቹን እየገረፈ ከቤተ መቅደሱ አስወጣ፤ የሚሸጡትንም ነገር ገለባበጠባቸው ‹‹ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል›› እያለም የእግዚአብሔርን ቃል አስተማራቸው። ዮሐ ፪፥፩— መጨረሻው።
ልጆች! ባጠቃላይ የዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት ‹‹ምኲራብ›› ተብሎ የተሰየመው ጌታችን መድኃኒታችን ወደ ምኩራብ ገብቶ ስላስተማረና በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚሸጡትን በጅራፍ ገርፎ ያስወጣበት ቀን በመሆኑ ነው።
4. መፃጉዕ
ልጆች! የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት ‹‹ መፃጉዕ›› በመባል ይታወቃል። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው መግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ‹‹ መፃጉዕ›› ማለት ‹‹ ጐባጣ›› ማለት ነው ብለው ይፈቱታል። የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት በዚህ ስያሜ መጠራቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ታሞ አልጋ ላይ የነበረውን በሽተኛ የፈወሰበት ቀን በመሆኑ ነው።
በኢየሩሳሌም ውስጥ በበጎች በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ አምስት ያህል መመላለሻ የነበረባትና በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ቤተ ሳይዳ›› የምትባል አንዲት የመጠመቂያ ቦታ ነበረች። በዚህች ቦታ ብዙ በሽተኞች እየመጡ እየተጠመቁ ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር። በዚህች ቦታ ላይ ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛ በሽተኛ ነበር።
ልጆች! የእግዚአብሔር መልአክ ወደዚህች የመጠመቂያ ቦታ መጥቶ ውሃውን ያንቀሳቅሰው ነበር። መልአኩ ውሃውን ባንቀሳቀሰው ጊዜ በመጀመሪያ የገባ ታማሚ ተፈውሶ ይወጣ ነበር። ስለዚህ መልአኩ ውሃው እንዳንቀሳቀሰ ቀድሞ ለመግባት እና ለመዳን ሽሚያ ነበረ። በዚህ ቦታ ደግሞ ለሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛ ምንም ዓይነት ዘመድ ያልነበረው አንድ ሰው ነበረ። ውሃው በመልአኩ በተንቀሳቀሰ ጊዜ የሚወስደው ሰው ባለመኖሩ ለዚያን ያህል ዓመት በዚያች የመጠመቂያ ቦታ ተኝቶ ነበረ።
በአንድ የሰንበት ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ወደዚህች የመጠመቂያ ቦታ መጣ መፃዕጉንም በአልጋው ላይ ተጣብቆ ተኝቶ አገኘው ለብዙ ዘመናት መተኛቱን ስላወቀም፦ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› አለው
መፃዕጉዕ ‹‹ጌታ ሆይ ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ፤ እኔ ወደ መጠመቂያው ልሄድ ስል ሌላው ቀድሞኝ ይገባና ተፈውሶ ይዳል›› በማለት መለሰለት።
ጌታም ‹‹ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› አለው ወዲያውም መፃጉዕ ዳነ ይተኛበት የነበረውንም አልጋ ተሸክሞ ሄደ። በሽተኛው የተፈወሰበት ቀኑ ሰንበት ነበርና አይሁድ ወደ በሽተኛው መጥተው ‹‹ በሰንበት አልጋህን መሸከም አትችልም ሰንበት ነውና›› አሉት ። መፃዕጉም ‹‹ ከበሽታዬ ያዳነኝ እሱ ነው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለኝ‹ ብሎ መለሰላችው። እይሁድም ‹‹የፈወሰህን ሰው አሳየን›› አሉት። ነገር ግን በዚያ ቦታ ብዙ ሰው ይጋፋ ነበርና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለይቶ ሊያሳያቸው አልቻለም። ዮሐ ፭፥፩፲፭ ።
ልጆች! የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት መፃጉዕ የተባለበት ምክንያት ከላይ እንደነገርናችሁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ሳይዳ ተገኝቶ መፃጉዕን ያዳነበት ቀን ስለሆነ ነው። በሚቀጥለው ዝግጅታችን ስለቀሩት የዐቢይ ጾም ሳምንታት መጠሪያና ታሪክ እንነግራችኋለን እስከዚያው ደህና ሰንብቱ!
እግዚአብሔር ቸርነት፤
የእመቤታችን ፍቅር አይለያችሁ!
- Details
- Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1213
ከጥቂት ዓመታት በፊት በአሜሪካና በአውሮፓ አንዳንድ በክርስትና ስም የተደራጁ አካላት ክርስትናውን በቆዳ ቀለም ለይተው የጥቁርና የነጭ ቤተ ክርስቲያን ወደሚል ፀረ ክርስትና አደረጃጀት መፍጠር እንደ ጀመሩ ይነገር ነበር። ለስሙ ምስጋና ይሁንና ‹‹ኢየሱስ›› በሚለው ስም በመጠቀምም ‹‹ጥቁሩ ኢየሱስ፣ ነጩ ኢየሱስ›› ወደሚል የጽርፈት ተግባር ውስጥ ገብተዋል።
እነዚህ ወገኖች ‹አንድ አስተምህሮ አለን› እያሉ በዘረኝነት ምክንያት ግን እምነታቸውን መክፈላቸው ያነጋግር ነበር። በአንድ ቋንቋ መሰብሰብ እየቻሉም በዘረኝነት ምክንያት ግን አንድ ስብስብ መፍጠር አለመቻላቸው ጉድ አስብሏል።
በዚህ ተገርመን ሳናበቃ በአህጉራችንና በሀገራችን ክርስትናን በጎሳና በነገድ የሚያይ ወገን ማቆጥቆጥ ጀመረ። የጥቃቱም ዒላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሆነች።
ቤተ ክርስቲያን በነበራት ታሪክ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድን አልፋ ለሰይጣን የጥፋት ዘር ሳትንበረከክ እዚህ ደርሳለች። በጎጥ ከፋፍለው ጸጋ፣ ቅባት፣ ተዋሕዶ በሚል የነበረውን መለያየት በሊቃውንቷ ጉባኤዎች መትፍሔ ሰጥታ ቤተሰቧን ሁሉ በአንድ ማኅበር አጽንታ ቆይታለች። ለቤተ ክርስቲያን የማይተኛው ሰይጣን ግን አሁን ደግሞ ‹‹የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የእገሌ ጎሳ እምነት እንጂ የእኛ አይደለም›› በሚል መንጋዋን ከቤቱ ለማስበርገግ ሲሠራ ቆይቷል። ብዙዎችም በዚህ አካሔድ ተሰናክለዋል። ኦርቶዶክሳዊ እምነትን በአስተምህሮው ሳይሆን የእነእገሌ እምነት ነው በሚል የጎሰኝት አመለካከት የተለዩት ብዙ ናቸው።
እነዚህ ወገኖች ዓለምአቀፋዊት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የአንድ ነገድ ብቻ እንደሆነ፣ ለብዙ ዘመናት የኖረችውን ቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ‹እገሌ የሚባለው ንጉሥ እምነት› በማለት ሲቀሰቀሱ ይታያል። ቢጠይቋት መልስ የማታጣ ስትሆንባቸው፣ ሊቃውንቷን ሊከፋፍሉ ሲሞክሩ ጉባኤዋን መበተን ሲሳናቸው ይህንን የሰነፍ መንገድ ለመጠቀም ተገደዋል።
የመናፍቃኑን የሰነፍ ቅሰጣ ተመልክተን ሳናበቃ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲያን በነገድና በጎሳ እንድትደራጅ፣ ከተቻለም እንድትበጣጠስ የሚደረግ ቅስቀሳ እየታየ ነው። ያለውን ፖለቲካዊ ሥርዓት የሚቀየሙና ለፖለቲካዊ ትርፍ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ አሁንም ከቤተ ክርስቲያን ራስ ላይ መውረድ ያለመቻላቸውም ማሳያ ነው። የፖለቲካ ግብግቡን በሌላ ሜዳ ማድረግ ሲሳናቸው በዘረኝት ኑፋቄያቸው ቤተ ክርስቲያንን ሊያውኳት እየሞከሩ ነው። አንዲትን ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሀገር ውስጥ ብዙ ሊያደርጓት ይፈልጋሉ። ይህ የሚያስደስተው ማንን ነው? የሚሠሩትስ ለማን ነው? ለሰይጣን አይደለምን?። ይህ ኑፋቄን ለመቀፍቀፍ የሚመች ብቻ ሳይሆን በራሱ ኑፋቄ አይደለምን?
የዘር ጥራትን፣ ቋንቋን፣ መሠረት ያደረገ ማግለል፣ እንዴት ክርስቲያናዊ መንገድ ሊሆን ይችላል? በአንድ ክርስቶስ ወንድማማች ሆነው የኖሩ፣ በአንድ የቁርባን ማዕድ የሚታደሙ ወንድማማቾች መለያየትና አንዱን ለሌላው እንግዳ ማድረግ በክርስትና እንዴት ተቀባይነት ይኖረዋል? ‹በእኛ ዘር ቄስ ብቻ፣ በእኛ ዘር ዲያቆን ብቻ ይገልገል› የሚል ጉባኤ ቢፈጠርስ ይህ የዘር ቤተ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ መልኩን እንዴት ያገኛል?
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዎች አብያተ ክርስቲያናት ሲመሠረቱ በአንድ ከተማ በአንድ አካባቢ የሚቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉንም በከተማው ወይም በአካባቢው ያሉ የእምነቱን ተከታዮች ያስተናግዳሉ፣ ያቅፋሉ እንጂ የአንድ በቁጥር የበለጠ ወይም ያነሰ ዘር ቤተ ክርስቲያን ሆነው አልተደራጁም። ስማቸው በከተማው ወይም በአካባቢው የኤፌሶን፣ የአንጾኪያ፣ የኢየሩሳሌም የትያጥሮን፣ የሰርምኔስ ወዘተ ይባላል እንጂ የአይሁድ፣ የግሪክ፣ የሮማዊ እየተባሉ አልተለያዩም። እግዚአብሔር በሚሰጠው ጸጋ ሁሉ አንድነታቸውን ይጠብቃሉ እንጂ ሰበብ እየፈለጉ አይበጣጠሱም።
የሮማው ንጉሥ ጭካኔ ሮማዊ ዜግነት ወይም ትውልድ የሌላቸውን ሁሉ እንደ እንግዳ እንዲያዩ አላደረገም። የግሪክ ሰዎች መመካት ግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ ያልሆኑትን ክርስቲያኖችን ተለይታችሁ የራሳችሁ ቤተ ክርስቲያን ፍጠሩ አላስባላቸውም። የአይሁድ ክርስቲያኖች ንቀት ሌሎች የአሕዛብ ወገን ክርስቲያኖች ለብቻቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲያቋቁሙ አላደረጋቸውም።
በኢየሩሳሌም የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በዋናነት ከአይሁድ ወገን የነበሩ ክርስቲያኖችን አብዝቶ ይቀፍ እንጂ ገና ከምሥረታው ጀምሮ ከልዩ ልዩ ሀገር/ነገድ/ የመጡ ክርስቲያኖችም አብረው ያመልኩ ነበር። የሮም ቤተ ክርስቲያን በአመዛኙ ከአሕዛብ ወገን የነበሩ ክርስያኖችን ይቀፍ እንጂ በርካታ ከአይሁድ ወገን የነበሩ ክርስቲያኖችም ነበሩበት። ታዲያ በእኛ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች የዚህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ወይም ትውልድ ነን ካልን የአሁኑን የጎሳ ቤተ ክርስቲያን ምሥረታ ከየት አመጣነው? ይህ የሰይጣን ሐሳብ የዓለማውያን መንገድ ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚጭኑ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን ያናጋልና ኑፋቄ ነው። ሊወገዝ የሚገባው የዘረኝነት ኑፋቄ እንደሆነ ታዝቤያለሁ።
እንዲህ ዓይነት ሰዎች የቅዱሳን ሐዋርያትን ማሳሰቢያ መልእክቶች ደጋግመው ማንበብ አለባቸው። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።››(፩ ቆሮ ፩፥፲) ያለው መልእክቱን ያስተውሉ እላለሁ።
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 2213
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ስሜ ገብረ ሚካኤል ይባላል የምኖረው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን በድኅረ ገጽ የሚወጡ የስምዐ ጽድቅ እና ሐመር መጽሔት ሥራዎችን እከታተላለሁ። በተለይ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ‹‹ ምሥጢሬን ላካፍላችሁ›› በሚለው ዐምድ ሥር የሚወጡ ጽሑፎችን ትኩረት ሰጥቼ እከታተላለሁ፤ ብዙ ቁም ነገሮችንም አግኝቼበታለሁ። የራሴን ጥያቄ ላቀርብ የተነሣሣሁትም መልስ ትሰጡኛላችሁ ብዬ በማመን ነው።
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! ከልጅነት ጀምሮ አብሮ አደግ የሆነ ጓደኛ አለኝ የአንድ ሰፈር ልጆች ስንሆን ከሠላሳ ዓመታት በላይ አብረን ኖረናል። ጓደኛዬን የራሴን ያህል አምነዋለሁ ቤተኛዬም ነው። በአንድ ወቅት በጣም ስለቸገረው ገንዘብ ከመንግሥት ለመበደር ፈልጎ ቤቴን አስይዤ ዋስ ሆንኩት፤ ነገር ግን ገንዘቡን ከወሰደ በኋላ ዕዳውን ለመንግሥት መመለስ ባለመቻሉ የእርሱን ዕዳ ለመክፈል ቤቴ እስከመሸጥ ደረሰ በዚያም ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋለጥኩኝ።
ይህ የልጅነት ወዳጄ ቤቴ ከመሸጡ በፊት ገንዘቡን እንዲመልስ ብዙ ጊዜ ጠየኩ አስጠየኩት ፤ነገር ግን ‹‹ቸግሮኝ ነው›› በሚል ምክንያት ዕዳውን ሳይከፍል ቀርቶ ለችግር አጋለጠኝ። በፍርድ ቤት እንዳልከሰው ‹‹ክርስቲያን ሆኜ›› የሚል ይሉኝታ ያዘኝ እንዳልተወው ከላይ እንደጠቀስኩት የከፋ ችግር ላይ ነኝ። እግዚአብሔርን በመፍራት ክሱን ብተወውም ያደረገውን ክፉ ሥራ ግን መርሳት አልቻልኩም። ከነገ ዛሬ ይመልስልኛል በሚል ተስፋ ምንም እንዳልተፈጠረ ስቄ ባናግረውም ያደረገውን ነገር በጥላቻ ከማሰብ አልቦዘንኩም። ቂም ኃጢአት እንደሆነ ባውቅም መተው ግን አልቻልኩም። ጓደኛዬን ባገኙሁትም ሆነ አጠገቤ በሌለ ሰዓት የሠራው ነገር ወደ ልቤ እየመጣ ተቸግሬአለሁ እና በእርሱ ላይ ያለኝን ቂም እንዴት ልተው? መፍትሄ ጠቁሙኝ።
ገብረ ሚካኤል ‹‹ቂሜን እንዴት ልተው?›› በማለት ቂመኛ እንድትሆን ያደረገህን ምክንያት ዘርዝረህ መፍትሔ ፍለጋ ጥያቄህን ስላቀረብክልን በቅድሚያ ምስጋና እናቀርብልሃለን። ሰው በሥጋው ሲታመም መታከም ስላለበት የትኛው ሐኪም ቤት ሄዶ የትኛውን የጤና ባለሙያ እንደሚያገኝና ታክሞም ከሕመሙ እንደሚድን በቅድሚያ እንደሚያስበው ሁሉ አንተም በክርስትና ሕይወትህ ላጋጠመህ ፈተናና የኅሊናህ ዕረፍት ለነሳህ ጉዳይ ከእናንተ መፍትሔ አገኛለሁ ብለህ ሳትደብቅ ጥያቄህን አቅርበህልናል። አበው ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም›› እንዲሉ ።
አንተው እንደገለጽክልን የምትኖረው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን ከሠላሳ ዓመታት በላይ አብረህ እንደቤተኛ ሆነህ ከምትኖረው ጓደኛህ የገጠመህ ችግር ነው። ልበ አምላክ የተባለውን ንጉሥ ዳዊት ሲያስረዳ ‹‹ከቸር ሰው ጋር ቸር ሁነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሁነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።›› መዝ.፲፯፥፳፭-፳፮ ይላል።
ገብረ ሚካኤል በቅድሚያ ከሌላ ሰው ጋር አብሮ አደጌ ነው ጓደኛዬ ነው ብለህ ሙሉ ልብህን ሰጥተህ አብረህ ከመጓዝህ በፊት ልበ አምላክ ዳዊት እንዳለው በተሰጠህ ዕውቀት ጓደኛህን በቅድሚያ መመርመር ግድ ይላል። ቸር ነው፣ ቅን ነው፣ ንጹሕ ነው፣ ጠማማ ነው ለማለት እንኳን ሠላሳ ዓመታትን ይቅርና ጥቂት ወራትም ዓመታትም በቂ ናቸውና። በመጽሐፍ ‹‹የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል?›› ኤር.፲፯፡፱ እንዲል።
መጽሐፍ ቅዱስ በገንዘብ እና በክህደት ምክንያት በቤተሰባቸው ሳይቀር የተፈተኑ ሰዎች መኖራቸውን ይገልጽልናል። ለምሳሌ የያዕቆብን ልጅ ዮሴፍን ለግብጽ ነጋዴዎች የሸጡት የአባቱ ልጆች ወንድሞቹ ናቸው (ዘፍ ፴፯፥፳፯።) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ እንኳን አብሮ አደግ ጓደኛ ይቅርና ‹‹ለሰውም ቤተሰቦቹ ጠላቶቹ ይሆኑበታል›› (ማቴ.፲፥፴፮) ብሎናል። ይህ የሚያሳየን እንኳን በሥጋ የማትዛመደው በሆነ ጊዜ ላይ ያገኘኸው ጓደኛ ይቅርና ቤተሰብ (የሥጋ ዘመድ) እንኳ ቢሆን ላይታመን ይችላል። በመሆኑም የልብ ጓደኛዬ ነው ብለህ ልብህን የጣልክበት ጓደኛህ እንዲህ ዓይነት ሥራ በመሥራቱ ብዙ ሊደንቅህ አይገባም። አንተ ግን ‹‹ለሚለምንህ ስጥ ከአንተም ይበደር ዘንድ የሚወደውን አትከልክለው›› (ማቴ.፭፥፵፪) የተባለውን አምላካዊ ቃል በመተግበርህ ዋጋህ ሰማያዊ ተግባርህ ክርስቲያናዊ መሆኑ በቅድሚያ ኅሊናህን ልታሳምነው ይገባል።
በእርግጥ ጓደኛህን ከማመንህና ከመውደድህ የተነሳ በተቸገረ ጊዜ ቤትህን አስይዘህ ዋስ እንደሆንክለትና እርሱም ገንዘቡን መክፈል ባለመቻሉ ቤትህን እስከመሸጥ እና ዕዳውን እስከመክፈል መድረስህን በዚህም ለጓደኛህ ስትል ለክፉ ችግር መጋለጥህን ጠቅሰህልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔርን ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።›› ሮሜ.፷፡፳፷ እንዲል። ጓደኛህ ባደረገህ ነገር እጅግም ሳታዝን ለበጎ ነው ብለህ መቀበል ይገባሃል። በተጨማሪ ራስህን በእርሱ ቦታ ማስቀመጥም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ማንም ሰው በራሱ ፍጹም አይደለምና።
ገብረ ሚካኤል ይህ ፈተና በጓደኛህ በኩል ላንተ መቅረቡ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑን ማወቅ ይገባሃል። ፈተናውንም በጸጋ ትቀበል ዘንድ ጽናቱን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። እንደ ኢትዮጵያዊያን ባሕል ጓደኛህን በሽማግሌ አስጠይቀው። የሽማግሌዎችን ድምፅ አልሰማም ካለም ጉዳዩን ለእግዚአብሔር ብቻ አሳውቀህ ከልብህ ተውለት። ይቅርታ ማድረግ ምሬትን፣ መብሰልሰልን ስለዚያ ክፉ ነገር በተደጋጋሚ ማሰብን ያስወግዳል። በእርግጥ ይቅርታ ማድረግ በደልን መርሳት ወይም የተሰራውን ስህተት ትክክል ነው ብሎ መቀበል አይደለም ይልቁንም ‹‹ይቅርታ ማድረግ›› በውስጥህ ያሳደረብህን መጥፎ ስሜት መቆጣጠር መቻልና መተው ነው።
በጥያቄህ ውስጥ እንደገለጽክልን ለመክሰስ አስቤ ‹‹ክርስቲያን ሆኜ›› እንዴት እከሰዋለሁ እያልኩ ከኅሊናዬ ጋር እየተሟገትኩ እገኛለሁ ብለሃል። ከላይ እንደገለጽክልን በሸማግሌዎች ጠይቀኸው እንቢ ካለ አንተ ቂም መያዝ አይገባህም። ምክንያቱም አበው ‹‹ቂም ይዞ ጸሎት›› ዋጋ እንደሌለው ይገልጻሉና። አንተም ጸሎትህ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ መሻትህን ይፈድምልህ ዘንድ ለነፍስ አባትህ ጉዳዩን አስረዳና ቀኖና ተቀበል።
ስለ ይቅርታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትልቅ ምሳሌያችን ነው። የሰው ልጆች ያለባቸው እዳ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ከፍሏልና። የአዳምን በደልና ኃጢአት ወደዚህ ምድር መምጣቱ ፣ ሥጋን መዋሃዱ ፣ በምድር ላይ ተመላልሶ ማስተማሩ የሰው ልጆች በአዳም ምክንያት ያጡትን ገነት እንዲወርሱ ነበር። ነገር ግን ጌታችን በምድር በነበረበት ጊዜ ላደገላቸው ልካም ነገር ሁሉ ክፉን መልሰውለታል። ይህም ሳይበቃቸው በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት አድርገውታል። ነገር ግን ያበላቸው፣ ከበሽታ ያዳናቸው፣ ከሰው እኩል ያደረጋቸው በአደባባይ ወጥተው ‹‹ ይሰቀል! ይሰቀል! ይሰቀል!›› ብለው ሲጮሁበት ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ›› ሉቃ ፳፫፥፴፬ በማለት ሲጸልይላቸው እናያለን። ገብረ ሚካኤል አንተ ጌታችን ድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደረሰበት በደል የበለጠ በደል፤ ከደረሰበት መከዳት የበለጠ መከዳት አልደረሰብህምና እርሱን አብነት አድርገህ ልትጽናና ይገባሃል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕዳ ስለተያዘው ባርያ እና ዕዳውን ስለሰረዘለት ጌታው በምሳሌ ባስተማረበት አንቀጹ ‹‹መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቆጣጠራቸው የወደደ ንጉሥን ትመስላለች። ሊቆጣጠራቸውም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት የሚከፍለውን አንድ ባለ ዕዳ ወደ እርሱ አመጡ። የሚከፍለውም ባጣ ጊዜ ጌታው እርሱንና ሚስቱን፣ ልጆቹም፣ ያለውም ሁሉ እንዲሸጡና ዕዳውን እንዲከፍል አዘዘ። ወዲያውም ያ አገልጋይ ወድቆ ሰገደለት፦ ‹‹ አቤቱ ታገሠኝ ሁሉን እከፍልሃለሁ እያለ ለመነው። ጌታውም ያን አገልጋይ አዘነለትና ፈታው ዕዳውንም ተወለት። . . . ›› ሉቃ ፲፰፥፳፫— ፴፭ ይለናል። ገብረ ሚካኤል አንተም እንደነገርከን ምንም እንኳ ቢቸግርህ ጓደኛህ ቸግሮት ሊከፍልህ ባለመቻሉ ይሆናል ብለህ ነገሩን በቅንነት በማየት ልትተውለት ብሎም በእርሱ ላይ ያለህን ቂም ከውስጥ አውጥተህ ልትጥል ይገባሃል።
በመጽሐፈ ሲራክ እንደተገለጸው ‹‹እንዳንተ ያለውን ሰውን ይቅር ሳትል ኃጢአትህን ያስተሠርይልህ ዘንድ እንግዲህ እንዴት ትለምነዋለህ›› ሲራ ፳፷ ፥ ፬ ብሏልና። በቅድሚያ አንተ የይቅርታ ሰው ሁነህ መገኘት ይገባሃል። ይህ ያንተ ጓደኛ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንተን በመካዱ ኃጢአት ሠርቷል። ለእርሱ የሥራውን የሚከፍለው እግዚአብሔር እንጂ አንተ ስላልሆንክ ስለተደረገብህ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ንገርለት (ጸልይለት)። መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና ለሰዎች ግን ኃጢአተኛውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።›› (ማቴ.፮፥፲፬-፲፭) ይላል።
‹‹በይቅርታ የሚገኝ ድል በጦርነት አይገኝም›› የሚል የኢትዮጵያውያን ብሂልም አለ። አንተ የበደለህን በተለይም ‹‹ የልቤ ወዳጅ›› የምትለው ሰው ያደረሰብህን በደል መተው በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ፊት የምታገኘው ይቅርታ ሲሆን ሁለተኛው ስለ ጓደኛህ የምታስበው መጥፎ ነገር በአንተ ስነ ልቦና ላይ የሚያስከትለውን ጫና ያስቀርልሃል። አንተም እንዳልከው ወደዚህ ዝግጅት ክፍል እንኳ ለመጻፍ የተገደድከው የጓደኛህ ድርጊት ሰላም ስለነሳህ ነው። ባንተ ላይ ያደረገውን ነገር ሙሉ በሙሉ ብትተውለት ደግሞ በራስህ ላይ ድልን ትጎናፀፋለህ፣ ሰላማዊ ትሆናለህ ማለት ነው። ስለዚህ አካላዊና ህሊናዊ ሰላም ለማግኘት እንዲሁም በጤንነት ለመኖር ጓደኛህን ይቅር ማለት ይገባሃል።
ስለዚህ ገብረ ሚካኤል ጓደኛህን ከልብህ ይቅር ማለት የሚገባው ፩ኛ. አንተም በማወቅም ባለማወቅም የሠራኸውን ኃጢአት ይቅር እንድትባል ነው። አለበለዚያ ይቅር አይላችሁም ተብሏሏና። ፪ኛው ለበደለህ ሰው ይቅርታ ማድረግ የውስጥህን ሰላም ይመልሳልና ነው። ይልቁንም እንደ ክርስቲያን ለጓኛህም ስመ ክርስትናውን ወደ ገዳማዊ አባቶች ላክና እንዲጸልዩለት አስደርግ። ‹‹በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ›› (ማቴ.፭፥፵፭) ተብሏልና። ጓደኛዬን ባገኘሁትም ሆነ አጠገቤ በሌለ ሰዓት ያደረገኝ ነገር ወደ ልቤ እየመጣ ተቸግሬአለሁ ስላልክ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› (ያዕ.፭፥፲፮) ተብሏልና ለራስህም ወደ ገዳማውያን አባቶች መብዓ ይዘህ በመሄድ እንዲጸልዩልህ አስደርግ።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ብለው መጸለይ እንደሚገባቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ጠይቀውት የጸሎት ሁሉ አባት የሆነውን ጸሎት አስተምሯቸዋል። ማቴ.፮፥፱-፲፫ በዚህ የጸሎት ክፍል ውስጥ ክርስቲያኖች ዘወትር ልብ ብለው ማስተዋል ከሚገባቸው ሐሳቦች ውስጥ አንዱ ‹‹የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን
ይቅር በለን።›› የሚለው ጸሎት ነው። እኛ የበደሉንን ይቅር ካላልን ይቅር አንባልምና ነው። ይቅር እንድንባል የይቅርታ ሰዎች የፍቅር ሰዎች ሆነን መገኘት ይገባናል። ‹‹ሙሉ ደመወዝ እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።›› (፪ኛዮሐ.፩፥፷) ተብለናል። በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በክርስትና ጉዞህ ከእግዚአብሔር ሙሉ ደመወዝ እንድትቀበል አንተን እየፈተነ ባለው ቂም ከልብህ ተነቅሎ እንዲጠፋ ከነፍስ አባትህ ጋር ተነጋግረህ ሱባዔ ይዘህበት ጸልይ። ቂም ይዘህ የምትጸልይ ከሆነ ግን ጸሎትህ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ለጥያቄ መልስ አያሰጥህም።
ሐዋርያው ‹‹እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን። ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል”፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይይኖር ታውቃላችሁ።›› (፩ኛ.ዮሐ.፫፥፲፬-፲፭) ብሏል። ስለዚህ ገብረ ሚካኤል አሁን ካለህበት የሞት መንገድ ወጥተህ በሕይወት መንገድ ለመጓዝ ጓደኛህን ከልብ ይቅር በለው። ያኔጊዜም እግዚአብሔር የተወሰድብህን ንብረት እንደ ጻድቁ ኢዮብ እጥፍ አድርጎ ይከፍልሃል። ይህን ካደረግህ ክርስትናውን በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ኖረህበታልና። ምድራዊውን ሀብት ብቻ ሳይሆን ሰማያዊውን ርስት እግዚአብሔር እንደሚያወርስህ እመን። ‹‹በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።›› ተብሏልና (ሉቃ.፰፥፲፭።)
ገብረ ሚካኤል ቂም እንድንይዝ የሚያደርገን መንፈስ ከጠላት ከዲያብሎስ የሚመጣ መንፈስ ነው። ስለዚህ ክርስቲያን ደግሞ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ እንጂ በጠላት ክፉ መንፈስ መኖር አይገባውም። ‹‹የጌታችን ጽዋና የአጋንንት ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፣ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።›› (፩ኛ ቆሮ.፲፥፳፩) ተብሏልና ቂም ኃጢአት መሆኑን እያወቅህ ቂም መያዝ ከአንተ አይጠበቅም። ‹‹ራቁቱን እንዳይሄድ አፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ለብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።›› (ራእ.፲፮፥፲፭) ተብሏልና ልብስ የተባለው ልጅነትህን ከቂም ርቀህ ከበቀል ወጥተህ ክርስቲያናዊ ሥርዓትና ሕግን ጠብቀህ ዋጋ እንድታገኝ አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳህ።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1042
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በወላይታ ሀገረ ስብከት የወላይታ ዞን ፕሮቴስታንት የመንግሥት አመራሮች ቤተ ክርስቲያንን ሆን ብለው ላለፉት ዐሥር ዓመታት ሲበድሉ እንደነበር የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ቀሲስ ቦኪቻ ኢንጋ ገለጡ።
የዞኑ ፕሮቴስታንት የመንግሥት አመራሮች በተለይ በገጠር ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ይዞታ ላይ ከፍተኛ በደል ይፈጽሙ እንደነበር ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትም ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ደርሶ አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም አመራሮቹ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኞች ሳይሆኑ እንደቀሩም ተናግረዋል።
ቤተ ክርስቲያን ያሏት ጥያቄዎች በሙሉ እንዲመለሱ ላለፉት ዐሥር ዓመታት ለወላይታ ዞን አመራሮች አቤቱታ ስታቀርብ ብትቆይም በአመራሮቹ በኩል ምንም ዓይነት አወንታዊ ምላሽ እንዳልተሰጠ ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።
በቅርቡም አንድ የፕሮቴስታንት ‹‹ሰባኪ ነኝ›› የሚል ግለሰብ ወላይ ሶዶ ከተማ በሚገኙ አጥቢያዎች እየዞረ በጥሩምባ በመታገዝ ‹‹የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠንቋይ ናት፤ ከዚህ ውጡ፤ ያለበለዚያ ኢየሱስን አታገኙም›› እያለ ሲረብሽ በአግባቡ ይዘን ለሕግ አካላት ብናቀርብም ሕጋዊ ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ድርጊቱን የተቃወሙ ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችን አስረዋል፣ ደብድበዋል እንዲሁም አንገላታዋቸዋል ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
“የታሠሩ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ከእስር ለማስፈታት ጥረት በምናደርግበት ወቅትም የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች በምእመንና በእኔ ላይ ተጨማሪ ወከባና ድብደባ ፈጽመዋል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ “ከፖሊስ ጋር በተደረገው እልህ አስጨራሽ ሙግት የታሠሩ ወጣቶች ወዲያውኑ ከእስር እንዲፈቱ ስናደርግ ቤተ ክርስቲያንን ሲያንቋሽሽ የነበረው ግለሰብም በድጋሚ እንደዚህ ዓይነት ተግባር እንዳይፈጽም ፖሊስ ጣቢያ ፈርሞ እንዲወጣ የፀጥታ ኃይሎችን ጠይቀናል” ብለዋል።
ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአንዳንድ የመንግሥት ማኅበራዊ ተቋማት ላይ ፕሮቴስታንት ሠራተኞች በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ እያደረሱ ያሉትን ሃይማኖታዊ ትንኮሳ እንዲያቆሙ ለዞን አስተዳዳሪው እንዳሳወቁ ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ ዞኑም ቤተ ክርስቲያን የምታነሳው ጥያቄ በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ ቃል ገብቶ ሁከት ያስነሳው ግለሰብና ድብደባና ወከባ የፈጸሙ የፖሊስ አባላት በሕግ እንዲጠየቁ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም “በዞኑ አመራሮች የተወሰኑ ውሳኔዎችንና የቤተ ክርስቲያንን ጥያቄ ሁሉ ለማስፈጸመም ዝግጁ ነን ካሉ በኋላ በግለሰቡም ሆነ ግፍ በፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ ሕጋዊ የርምት ርምጃ እንዲወስድባቸው ሰሞኑን ክስ እንመሠርታለን” ብለዋል።
የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር እንድርያስ ጌታ በበኩላቸው የወላይታ ሀገረ ስብከት ያቀረባቸውን ቅሬታዎች በሙሉ ተመልክተው ለእያንዳንዱ ቅሬታ መፍትሔ ለመሥጠት ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጠው በወላይታ ሶዶ ከተማ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ሁከትና ብጥብጥ ያስነሳው ግለሰብም ሆነ አባቶችንና ምእመናንን ያዋከቡ የፖሊስ አባላትም በሕግ እንደሚጠየቁ አስረድተዋል።
ቤተ ክርስቲያን በድለውኛል ባለቻቸው አካላት ላይ ክስ እንድትመሠርትና ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጡት አስተዳዳሪው በቀጣይም በወላይታ ዞን ባሉ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ያለውን የይዞታ ጥያቄ ዞኑ ትኩረት እንደሚሰጠውና ከሀገረ ስብከቱ ጋር ተናቦ እንደሚሠራ እንዲሁም ለተነሱት ቅሬታዎች ሁሉ አፋጣኝ መልስ ለመስጠት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስገንዝበዋል።
በተከለከሉ ቦታዎች በተለይም በመንገድ ላይ፣ በሌሎች እምነት ተቋማት አቅራቢያ እንዲሁም በገበያ ቦታ ላይ በአጠቃላይ ከራሳቸው ቤተ እምነት ውጭ አግባብ ባልሆነ መንገድ ‹‹ወንጌል እንሰብካለን›› በሚሉ አካላት ላይ ዞኑ አስተማሪ ርምጃ እንደሚወስድ የገለጡት አስተዳዳሪው “በሕክምና ተቋማትና በሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት ላይ የሚፈጸመውን ሃይማኖታዊ ትንኮሳን ጭምር ለማስቀረት ርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1106
ትውልዱ፣ቤተ ክርስቲያንና ሀገር የቅዱስ ያሬድን ትሩፋቶች በተገቢ መንገድ እንዳልተጠቀሙባቸው የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክት አቢይ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የነበሩት ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ ገለጡ።
ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ ይህንን የገለጡት በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በበየዳ ወረዳ ጥጉና ጣና ቀበሌ የሚገኘው የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክትና ዘጋቢ ፊልም የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ይፋ በሆነበት ወቅት ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ነው።
ትውልዱ የቅዱስ ያሬድን ትሩፋቶች ...
በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም እንዲሠራ የታሰበው ፕሮጀክት ትውልዱ የቅዱስ ያሬድን አሻራዎች እንዲረዳና ከትሩፋቶቹም ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል ያሉት ላእከ ሰላም ባያብል ገዳሙ ያልተበረዘ ሁሉን ዓይነት የአብነት ትምህርት የሚሰጥ ማእከል በመሆኑ የዕውቀትና ኪነ ጥበብ ምንጭ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵውያንና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘመን የማይሽረው አስተዋጽኦ ያበረከተ ሊቅ መሆኑን ላእከ ሰላም ባያብል ከጠቆሙ በኋላ “በገዳሙ ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የተለየ ድርሻ ይኖርዋል” ብለዋል።
ገዳሙ ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ በመሆኑ በተለይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች መጥተው በሚጎበኙበት ወቅት ሀገርና ገዳሙ ከውጭ ምንዛሬ ተጠቃሚ እንደሚሆን ላእከ ሰላም ባያብል ተናግረዋል። ገዳሙ ፲፻፭፻ ዓመታት ታሪክ ባለቤት በመሆኑም ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ሊጎበኝ እንደሚችልም አስረድተዋል።
የሰሜን ወሎና ከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልክና ውበት እንደሆነ ገልጠው “የእርሱን ሁለንተናዊ ሀብት ሊያሳይ የሚችል ፕሮጀክት እስከ አሁን ድረስ ያለመሠራቱ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ጉድለት ነው” ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አያይዘው ‹‹በዚህ ወቅት ቅዱስ ያሬድን የሚዘክሩ ዘጋቢ ፊልሞችና ፕሮጀክቶች መዘጋጀታቸው መልካም ጅምር ነው። ፕሮጀክቶቹ የዘገዩ ቢሆንም ከአሁን በኋላ ለሚመጣው ትውልድ አቅምና ጉልበት ይሆናሉ›› ሲሉ ተናግረዋል። ቅዱስ ያሬድ የዜማ ሊቅ ብቻ እንዳልሆነ፤ ብሉያትንና ሐዲሳትን፣ ሊቃውንትን እንዲሁም አዋልድ መጻሕፍትን ጭምር የተረጎመ፤ ያብራራና ያመሰጠረ መሆኑንም አስረድተዋል።
የጥበብ ምንጭ የሆኑትን የጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድን ትሩፋቶች ደራሲያንና የዜማ ሰዎች በደንብ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ሊተገበር የታቀደውን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በየትኛውም ዓለም ያለ ሕዝበ ክርስቲያን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የቤተ ክርስቲያን ሀብቶች የሀገር ሀብቶች መሆናቸውን በመረዳት መንግሥትም ቤተ ክርስቲያን የምታከናውነውን የልማት ሥራ ሊያግዝ ፤እንዲሁም የሚያሥፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ሊያሟላ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙሓዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው ቅዱስ ያሬድን የሚዘክሩ ሥራዎች እንዳልተሠሩ አስታውቀው ያሁኑ ትውልድ እርሱን የሚዘክሩ ሥራዎች በመሥራት ቀሪውን ደግሞ ለመጭው ትውልድ የቤት ሥራ ትቶ ማለፍ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክት የወቅቱ ዐቢይ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አለማየሁ በዕለቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳስታወቁት ጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድን በመላው ዓለም ለማስተዋወቅ የተደገው ጥረት አናሳ መሆኑን አስረድተው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሆነ አስረድተዋል።
በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በበየዳ ወረዳ በጥጉና ጣና ቀበሌ የሚገኘው የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፪ ሺህ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ የአብነት ትምህርት ቤትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚሆኑ ያስገነዘቡት ም/ሰብሳቢው ገዳሙን የልሕቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከአብነት ትምህርት ቤቱ በተጨማሪ በገዳሙ ግዙፍ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የቅዱስ ያሬድን ሥራዎችና ተጋድሎዎች የሚያሳይ ዘመናዊ ሙዚየም እንደሚሠራ ያስረዱት ሰብሳቢው ገዳሙ ከተለያየ ዓለም ለሚመጡ ጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነና የፕሮጀክቱ ሥራዎች በቅርቡ ለመጀመርም በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1291
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በላይ በችግር ላይ የወደቀችበት ሰዓት ነው። ከከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች እና በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ወቅትን ተከትሎ በመጣው ግርግር ውስጥ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል፣ በሰይፍ ተገድለዋል፤ በአንድ ጀንበር ከባለንብረትና ከባለሀብትነት ማማ ላይ ወርደው የሰውን እጅ የሚጠብቁ ተረጂዎች ሆነዋል።
የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የመጣው ይህ ‹‹ሌሎችን›› የማጥቃት ሂደት ይበርዳል ሲባል እየጋለ፤ ይቀንሳል ሲባል እየጨመረ፣ መልኩን እየቀያየረ እዚህ ደርሷል። ዛሬም ንጺሐን ዜጎች ይገደላሉ፣ ይዘረፋሉ፣ እንዲሰደዱ ይደረጋሉ። አንድ ቦታ ቀዝቀዝ ሲል ሊላው ጋር እየሞቀ መላ ሀገሪቷን ያዳረሰው ይህ ክፉ ወረርሽኝ የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ ‹‹ የነገ ተረኛ ማነው?›› የሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሷል።
እንደ አየሩ ፀባይ የሚለዋወጠው ይህ የጥቃት ዒላማ ሲያሻው ፖለቲካዊ እየሆነ ፤ሲያሻው ብሔር ላይ እያተኮረ፤ አሊያም ጉዳዩን ሃይማኖታዊ አድርጎ ‹‹ከእኔ ውጪ ነው›› ከሚለው ሃይማኖት ተከታይ ላይ የጥፋት ቃታውን እየሳበ እዚህ ደርሷል። ከኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ በተፋታ መልኩ የሞቱ በወግ ባልተቀበሩበት ቀዬ በሕይወት የተረፉቱ ለረኀብና ለእርዛት እንዲሁም ለመጠለያ እጦት ተዳርገው ይገኛሉ።
ጉዳዩን በአንድ ሰሞን ሞቅታ ውስጥ ብቻ አይተን ሰሞነኛ ሐዘን እና ርዳታ ብቻ በማድረግ ሥራ ተጠምደን ስናበቃ በወረት የምንተወው የንፁሀን ሕይወት የሚገደን መቼ ነው? ለችግረኛ የሚዘረጋው ኢትዮጵያዊ እጅ ወዴት አለ? ያስብላል። ግማሽ አካላችን ለከፋ አደጋ ተጋልጦ ባለበት በዚህ ወቅት የእግዚአብሔር ልጆች ክርስቲያኖች ወዴት ናቸው? በየጊዜው እየጨመረ የመጣው ኦርቶዶክስ ተኮር የሆነው ጥፋት ከምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየተዛመተ የ፫ ሺህ ዘመን ታሪክ ያላትን ሀገር እንደ ሰደድ እሳት እየበላ ሲጨርስ ዝም ማለት ከታሪክ ተወቃሽነት አያድንም። ሀገርን እንደባላ አቁማ የያዘች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አልባ ፣ ቅርስ አልባ እየሆነች ባለችበት በዚህ ሰዓት ምእመናንዋንም ሆነ አብያተ ክርስቲያን የሚጠብቅ፣ የሚንከባከብ እንዲሁም በፈረሰው በኩል የሚቆም ምእመን ዛሬ ያስፈልጋታል።
ከሀገሪቱ ሕዝብ ከሃምሳ ፕርሰንት በላይ ምእመን ያላት፤ የሀገሪቱ ዋንኛ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ቅዱሳት መካናት ባለቤት የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰው አልባ ፣ ምእመን አልባ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት አልባ እየሆነች እያደር እያነሰች እና ቀድሞ ከነበረችበት የልዕልና ማማ ላይ በፍጥነት እየወረደች መሆኑን በውል ተገንዝቦ ከሰሞነኛ ግርግርታ ወጥቶ በጽሞና ማሰብ ይጠይቃል። እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እየጠፉ ያሉትን የቤተ ቅዱሳት መካናት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ፣ የተጎዱ ወገኖችን በማሰብ ፤ለርዳታ እጅን መዘርጋት እና ዘላቂ መፍትሔን በማፈላለግ የድርሻን መወጣት ወቅቱም ክርስትናችንም የሚጠይቀው ነው።
በአርአያ ሥላሴ የተፈጠሩ ሰዎች በእርስ በርስ ግጭት፣ ዘርና ሃይማኖት ተኮር በሆነ ጥቃት ለስደት፣ ለመፈናቀልና ለሞት ሲዳረጉ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከጎን ሆኖ የሚያጽናና፣ አይዞአችሁ ብሎ የሚያበረታታ ያስፈልጋል። ነፍስን ለመታደግ አስፈላጊውን ሰብአዊ ርዳታ ለማድረግ እጃችንን መዘርጋት ከእኛ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል። ምክንያቱም እኛ ክርስቲያኖች የተጎዱትን ለማየት የእግዚአብሔር ዓይን፤ የተራቡትን ለማጉረስ የእግዚአብሔር እጅ፤ ለተሰደዱት ለማዘን የእግዚአብሔር ልብ ነንና ሊታሰብበት ይገባል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ስለ ዳግም ምጽአቱ በተናገረበት አንቀጽ ‹‹ተርቤ አይታችሁ አላበላችሁኝም፣ተጠምቼ አይታችሁ አላጠጣችሁኝም፣ ታርዤ አይታችሁ አላለበሳችሁኝም›› ማቴ ፳፭ በማለት የተናገረው አምላካዊ ቃል እኛን የሚመለከት የማይመስለን ብዙዎች ነን።
ትናንት ባለቤት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ይልቁንም ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ለረኀብ ለስደት፣ ለእንግልት እና ለሞት ሲዳረጉ ቢቻል የሚደረገውን ግፍና ጭቆና በመቃወም ከፊት መቆም ፤አጋር መሆንም ተገቢ ነው። ስደተኞችን በመቀበል የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን ይልቁንም ክርስቲያኖች የክርስትናው ትርጉም ሲዛባብን እንደማየት የከፋ ነገር የለም። ለዓለም የምትተርፈው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ለገዛ ምእመናንዋ (አማኞችዋ) መሆን ያቅታታል? የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች ያበዛው፤ እንደ መልካም መዓዛ ሆኖ ለብዙዎች የተዳረሰው ‹‹ ከእነርሱም አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረም፤ ቤትና መሬት ያላቸውም ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን ያመጡ ነበር። አምጥተውም በሐዋርያት እግር አጠገብ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ለእያንዳንዱ እንደፍላጎቱ ያካፍሉት ነበር።›› ሐዋ.ሥ ፬ ፥ ፴፬-፴፭ በሚለው ቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የተገለጠው ክርስትና ዛሬ በእኛ ቸልተኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነውና በእምነት ውስጥ ነን የምንል ሁሉ አጥብቀን ልናስብበት ይገባል።
ዛሬ ተደጋግፈን ያላቆምነው ወገናችንን ነገ አናገኘውምና ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ ነው። ዛሬ ያልተቆረቆርንላት ቤተ ክርስቲያን ፈርሳ እንድታልቅ ዝም ማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከታሪክ መዝገብ ለማጥፋት በሚደረገው ስውር ዘመቻ ውስጥ ተሳታፊ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም።
ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ ፈርጣማ ጡንቻዎች እና መዳፎች ስትደቆስ ‹‹ለምን?›› የማይል የቤተ ክርስቲያን ልጅ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን እንዲሁም ክርስትናው ከእርሱ የሚጠብቀውን ሥራ እየሠራ አይደለምና አጥብቆ ሁሉም ራሱን መፈተሸ ይገባዋል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ትገኛለች። ይህንን ዘርፈ ብዙ ፈተና ልጆችዋ ተረዳድተው ከላይዋ ላይ ካላነሱላት፣ ወይም እንደ ሙሴ እጆችዋን መደገፍ ካልቻሉ ነገ የኔ የሚሉት ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ምእመን ማግኘት ይቸግራልና በገዛ ሀገር ስደተኛ ከመሆን በፊት ዛሬ ላይ ቆም ብሎ መሥራት አስፈላጊ ነው።
የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬ እየተገፉ እና እየሞቱ እንዲሁም በረኃብ በእርዛት እየተሠቃዩ ባሉበት አስቸጋሪ ወቅት አለንላችሁ ማለት የክርስቲያን ዋንኛ አላማ መሆን አለበት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተራቡት እንመጸውት ዘንድ እጆቹን አውሶናል፤ ድኃውን እናይ ዘንድ ዓይኖቹን ሰጥቶናል ፤ለተበደሉት እንራራ ዘንድ አዝዞናል። የክርስቶስ አምባሳደር ሆነን በተሾምንበት ሁሉ አውቀን እንተጋ ዘንድ ዘመኑ ከኛ ከክርስቲያኖች የሚፈልገው ዐቢይ ጥያቄ ነው።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 988
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታከብራቸው የዐደባባይ በዓላት በሥርዓት እንዳይከበሩ፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይገቡ ዘርፈ ብዙ ትንኮሳዎች ሲደርስባቸው ቆይቷል። በምእመናንና በአባቶች ካህናት እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት በሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ታጅበው የሚከበሩት እነዚህ የዐደባባይ በዓላት የተጋረጠባቸው የፀጥታ ስጋት ከዓመት ዓመት ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም።
የትንኮሳውን ዓይነትና ቦታን በመቀያየር ኦርቶዶክሳውያንን የማሳቀቅ፣ ስጋት ውስጥ የመክተትና ክብረ በዓላቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ የማጨናገፍ ሴራ ከዕለት ዕለት እየጨመረ፣ ጡንቻውን እያፈረጠመ እዚህ ደርሷል። በአንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ለማክበር ቢሞከርም በተወሰኑት አካባቢዎች ደግሞ ምንም ዓይነት ከልካይና ሃይ ባይ ባለመኖሩ(ቢኖርም የይስሙላ በመሆኑ) ምእመናን በገዛ ሀገራቸው ላይ ሃይማኖታቸውን በነፃነት እንዳያካሄዱ ተገደዋል። በዚህ ዓመት ብቻ እንኳ በመስቀል እና በጥምቀት በዓላት ላይ ከመከበራቸው በፊት እየተከበሩ እና ከተከበሩ በኋላ የተፈፀሙት ፀረ ኦርቶዶክሳውያን ትንኮሳዎች በከተማውም ሆነ በገጠሩ ጥቂት የማይባሉ ነበሩ።
የመስቀልም ሆነ የጥምቀት በዓል በመጣ ቁጥር ለትንኮሳ የሚዘጋጁ ፀረ ኦርቶዶክሳውያን ኃይሎች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ተንኳሽና ዕረፍት የለሽ ፀረ ኦርቶዶክሳውያን ኃይሎች መካከል አክራሪ እስላሞች በቀዳሚነት ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ አክራሪ እስላሞች በርከት ብለው በሚገኙባቸው አንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሁሉ የዐደባባይ በዓላቱ የሚከበሩበትን ወቅት ጠብቀው በውኃ ቀጠነ በዓሉን ሊያውክ ይችላል የሚሉትን ተግባር ሁሉ ይፈጽማሉ። ሲያሻቸው “ታቦት ይዛችሁ በእኛ አካባቢ አትለፉ” ወይም ደግሞ ‹‹ሰንደቅ ዓላማ አትስቀሉ››፤ ‹‹አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለበት ልብስ አትልበሱ››ይላሉ። የዚህ ሁሉ መዳረሻው ወይም የጥቃቱ ምክንያት “ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ለምን ሆናችሁ?” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ‹‹ለምን የእኛን ሃይማኖት አልመሰላችሁም›› የሚል ፍላጎት እንዳለበትም ከድርጊታቸው መረዳት እንችላለን።
ዐይን ያወጣውን የአክራሪዎች የወንጀል ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስተካክል የፀጥታ ኃይል ባለመኖሩም ጥቃቱ በማን አለብኝነት በተደጋጋሚ ይፈጸማል። የፀጥታ ኃይሎች በየአካባቢው ቢኖሩም ለሚከተሉት ሃይማኖት ያደሉ ወይም ለእውነት ያልቆሙ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት አይሞክሩም፤ ለክርስቲያኖች በደልና እንግልትም አይጨነቁም። ዘንድሮ ማለትም ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም የተከበረው የጥምቀት በዓል እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ ማለፉ አልቀረም። በተለይም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሀላባ ዞን ሀላባ ቁሊቶ ከተማ በጥምቀትና በቃና ዘገሊላ ዕለት የአካባቢው አክራሪ እስላሞች በበዓሉ ተሳታፊ ምእመናንና አገልጋዮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ፈጽመዋል። በዚህ ጥቃትም ምእመናንና አገልጋዮች መለስተኛና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እኛም በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢው የሃይማኖት አባቶችንና የመንግሥት አካላትን በስልክ አነጋግረናል።
የከምባታ፣ ጠንባሮና ሀላባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ ሚካኤል ታደሰ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ በሰጡት መረጃ “የእመቤታችንና የገብርኤል ታቦታት ከባህረ ጥምቀት ቦታቸው ተነሥተው ወደ መንበራቸው ሲመለሱ መስጅድ ውስጥ የነበሩ በርካታ አክራሪ ሙስሊሞች በምእመናንና በታቦታቱ ላይ በድንጋይ ጥቃት ፈጽመዋል ብለዋል። በወቅቱ በዓሉን በማክበር ላይ የነበሩ ምእመናን ችግር ይኖራል ብለው ባለመጠርጠራቸው መለስተኛና ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የአካባቢው አክራሪ እስላሞች ‹‹ታቦታቱን በአካባቢያችን አናሳልፍም›› ከማለታቸው ባሻገር በታቦታቱና በምእመናን ላይ ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ ናዳ በማውረድ ጉዳት አድርሰዋል። ወደ ፌዴራልና ክልል መንግሥታት ስልክ ተደውሎ የፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያና የክልሉ ልዩ ኃይል ደርሰው ካረጋጉ በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑ በከፍተኛ ቁጭት፣ ለቅሶና ኀዘን ሆነው ታቦታቱን ወደ መንበረ ክብራቸው እንደሸኙ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል። በወቅቱ በአካባቢው የነበሩት የፀጥታ አካላት ቁጥራቸው አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር መሣሪያ ሳይሆን ዱላ ብቻ የያዙ በመሆናቸው ሕዝበ ክርስቲያኑን ከጥቃት የመከላከልምና የመጠበቅ አቅምም ሆነ ፍላጎት አልነበራቸውም ብለዋል። ይባስ ብለው አብዛኛዎቹ የፀጥታ አካላት በምእመናንና በታቦታቱ ላይ ይደርስ የነበረውን ጥቃት በታዛቢነት ይመለከቱ ነበር።
እነዚህ የፀጥታ አካላት አልፎ አልፎ ይህን እኩይ ተግባር ይፈጽሙ ከነበሩት አካላት ጋር በመወገን በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ጥቃት ይፈጽሙ እንደነበርም ተናግረዋል። አንዳንድ የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ደግሞ ጥቃቱን እንዲያስቆሙ ሲጠየቁ ‹‹ትእዛዝ አልተሰጠንም›› የሚል መሠረተ ቢስ ምክንያት ያቀርቡ እንደነበር የገለጹ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቀትና የመስቀል በዓላትን በዐደባባይ እንደምታከብር እየታወቀ ልዩ ጥበቃ አለመደረጉ ለፀረ ኦርቶዶክሳውያን ኃይሎች ጥቃት ተጋላጭ አድርጎናል ብለዋል።
ሥራ አስኪያጁ አክለውም የአካባቢው አክራሪ እስላሞች ከዚህ ቀደም ማለትም በ፳፻፬ ዓ.ም በተመሳሳይ ወቅትና ቦታ በታቦታትና በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ከፍተኛ ጥቃት የፈጸሙ ቢሆንም የዘንድሮው ግን ከዚያ የተለየና የባሰ መሆኑን ገልጸዋል። አክራሪ እስላሞች ከዚህ ቀደም በተለያየ ወቅት አብያተ ክርስቲያናትን ለማቃጠል ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ባደረጉት ተጋድሎ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የዘንድሮው ጥቃት የሚለየው ቁጥራቸው ከሦስት መቶ እስከ አራት መቶ የሚሆኑ አክራሪ እስላሞች ከገጠር ተሰባስበው በመምጣት ‹‹መስጅድ ተቃጠለ›› በሚል ሰበብ በሕዝበ ክርስቲያኑና በታቦታት ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ነው ብለዋል። ካደረሱት የድንጋይ ጥቃት በተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናትን ለማቃጠልና የባሕረ ጥምቀቱን የግንብ አጥር ለማፍረስ ጥረት ሲያደርጉም ቆይተዋል ብለዋል።
የአካባቢው የፀጥታ ኃይልም መስጅድ ውስጥ ሆነው በሕዝበ ክርስቲያኑና በታቦታቱ ላይ በድንጋይ ጥቃት ሲፈጽሙ የዋሉትን ትተው በቦታው ያልነበሩና በሁከቱ ያልተሳተፉ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ለእስር እንደዳረጓቸው ሥራ አስኪያጁ አስረድተው ቤተ ክርስቲያን ወጣቶቹ ለምን እንደታሠሩባት ስትጠይቅም ‹‹አጣርተን እንለቃቸዋለን›› የሚል መልስ መስጠታቸውን ገልጸዋል ። በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ያሉ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ለሚከተሉት እምነት ያደሩ መሆናቸውን በመግለጽ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በክልሉ መንግሥት በኩል ውሳኔ እንዲያገኝ ሀገረ ስብከቱ ጠይቋል ብለዋል።
በሀላባ ቁሊቶ ከተማ የሦስቱ አድባራት ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል በበኩላቸው ጥር ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በሚገኝ ዐደባባይ አቅራቢያ ባለ መስጂድ ውስጥ የነበሩ በርካታ አክራሪ እስላሞች በምእመናንና በታቦታቱ ላይ ጥቃት እንደፈጸሙ ተናግረዋል። በወቅቱ በድንገት በተፈጠረው ችግር ምእመናንና አባቶች እንደተደናገጡ ያስረዱት አስተዳዳሪው በዕለቱ ከፍተኛ የሆነ የመሣሪያ ድምፅ ስለነበረ የቅዱስ ገብርኤልን ጽላት ይዘን በቅርብ ትገኝ ወደነበረችው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን አስገብተናል ብለዋል። አክራሪ እስላሞች በፈጸሙት በዚህ ጥቃትም አራት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን የተጎዱ ሲሆን የአንደኛው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለተሻለ ሕክምና ወደ ሐዋሳ ሆስፒታል እንደተላከ አስተዳዳሪው አስረድተዋል። የጥምቀትና የቃና ዘገሊለ በዓላት ካለፉ በኋላ የአካባቢው የፀጥታ ኃይላት ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችን እያደኑ ያለምንም ጥፋታቸው አስረዋል። ወጣቶቹ በበዓለ ጥምቀትም ሆነ በቃና ዘገሊላ ዕለት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርጉ ነበር ያሉት አስተዳዳሪው መስጅድ ውስጥ ሆነው በሕዝበ ክርስቲያኑና በታቦታቱ ላይ የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱ የነበሩ አክራሪ እስላሞች ግን አንዳቸው እንኳን አለመታሰራቸውን ገልጸዋል።
አክራሪዎቹ ይፈጽሙት ለነበረው ጥቃት የአጸፋ ርምጃ ባልወሰዱ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ላይ ፍትሐዊ ያልሆነ የእስር ርምጃ መውሰድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሆነ አስተዳዳሪው ተናግረው አንድ የሰበካ ጉባኤ አባልን ጨምሮ አስራ ሰባት ኦርቶዶክሳውያን ያለምንም ወንጀል በእስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል። እነዚህ የታሰሩ ወጣቶች በተለይ ቤተ ክርስቲያንን መኪና ከማቅረብ ጀምሮ በሁሉም ነገር እገዛ ሲያደርጉ የነበሩና ሌሎችም በበዓለ ጥምቀት ወቅት በቦታው ያልነበሩ እንደሆነ አስተዳዳሪው አስረድተዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስም ወጣቶቹ በታሰሩባቸው አካባቢዎች ተገኝተው ያጽናኑ ሲሆን ከመንግሥት አካላት ጋርም በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን፤ ጉዳያቸው እየተጣራ ከእስር እንደሚፈቱ የመንግሥት አካላቱ እንዳሳወቋቸው ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው በራሳቸው ዋስትናም ወጣቶቹ ከእስር እንዲፈቱ የአካባቢውን የመንግሥት አካላት መጠየቃቸውን እንዲሁም መንግሥት በሚፈልጋቸው ጊዜም ለማቅረብ ዝግጁ እንደሆኑ መናገራቸውን አስተዳዳሪው አክለዋል። ይሁን እንጂ ወጣቶቹ እስካሁን ድረስ ከእስር እንዳልተፈቱ አስታውቀዋል። ቤተ ክርስቲያን ወጣቶቹ ከእስር እንዲፈቱ ተግታ እንደምትሠራና ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ ወጣቶች ተደራጅተው ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል። በበዓለ ጥምቀት ወቅት አክራሪ እስላሞች የፈጸሙትን ጥቃት የአካባቢው የፀጥታ አካላት ድርጊቱን እንዳወገዙና እስልምናን የማይወክል ነገር ግን የአክራሪዎች ተግባር እንደሆነ መናገራቸውን አስተዳዳሪው አንሥተዋል።
የሀላባ ቁሊቶ ከተማ የሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤ ም/ሰብሳቢ አቶ አድነው ወልዴ እንደተናገሩት ደግሞ በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ትንኮሳ አሁን የተጀመረ እንዳልሆነ ገልጠው ከዚህ ቀደምም ብዙ ሃይማኖት ተኮር ትንኮሳዎች እንደነበሩ አስረድተዋል። ለዐደባባይ በዓላት ማክበሪያነት እንዲውል ፴፯ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በሕጋዊ መንገድ ከተሰጠን በኋላ ቦታውን ማልማት ስንጀምር ለሚከተሉት ሃይማኖት ያደሩ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹አታለሙም አቁሙ›› ብለው ከልክለውናል ሲሉ በአካባቢው እየተፈጸመ ያለውን በደል በማሳያነት አንሥተዋል።
የጥምቀት በዓል ከመድረሱ በፊት የፀጥታ ሥጋት እንዳለብን ለሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳዳር ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግልን በደብዳቤ ያሳወቅን ቢሆንም ጥያቄያችን ችላ በመባሉ አክራሪ እስላሞች መስጅድ ውስጥ ሆነው ጥቃት ፈጽመውብናል ብለዋል። አንዳንድ የአካባቢው የመንግሥት አካላት ለአክራሪዎች እኩይ ተግባር የተገዙ በመሆናቸው ጥቃት ሲፈጸምብን በቸልታ ከማየት ባሻገር ቤተ ክርስቲያን መብቷን ስትጠይቅ እንዳይፈጸምላት የሚሠሩ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ለሀላባ ዞን ፖሊስ መምሪያ (ኢ/ር ታረቀኝ ጉራች)፣ ለሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ (ዶ/ር መሐመድ ኑርዬ)፣ ለሀላባ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ (አቶ ሱሌይመን ሀሰን)፣ ለሀላባ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ (አቶ አብዱቃልድር ሎላሽ) እንዲሁም ለሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ (አቶ ሀሩና አህመድ) ስልክ ደውለን መረጃ ለመጠየቅ ጥረት ብናደርግም የተወሰኑት የመንግሥት አካላት ስልክ አንሥተው መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን የገለጡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ስልክ ሊያነሱልን ባለመቻላቸው ምላሻቸውን በዚህ ጽሑፍ ማካተት አለተቻለም።
- Details
- Written by: መጽሐፈ ሲራክ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1259
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ናዝሬት ቅድስት ማርያም በመጽሐፍ መምህርነት ተመድቤ ብሔድም የስብከተ ወንጌል ኃላፊነቱንም ደርበው ስለሰጡኝ ሁለቱም የሥራ መደብ ላይ አገለግል ነበር። ሠርክ ጉባኤ ከእሑድ እስከ እሑድ አስተምር ነበር፤ ከጉባኤው በኋላ ማታ ማታ ልጆች ሰብስቤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ሥርዓተ ቅዳሴ አስተምራለሁ፤ በእርግጥ ብዙ ዲያቆናትም ወጥተዋል። እዚያ ካስማርሁዋቸው ውስጥ ውጪም ሄደው የሚያገለግሉ አሉ። ያኔ ብዙውን ሥራ ካለ አንድ ረዳት የምሠራው እኔ ነበርኩ። መምህር ዘላለም ወንድሙ ከወር አንድ ቀን ቅዳሜ ወይም እሑድ እየመጣ በስብከተ ወንጌል ትምህርት ያግዘኝ ነበር እንጂ ሌላ የሚያግዘኝ ሰው አልነበረም። በዚያ የሥራ ብዛት ዕረፍት ስላልነበረኝ ሰውነቴ እጅግ ተጎድቶ ነበር። ለአራት አመታት በዚያ ካገለገልኩ በኋላ በ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ዝውውር ጠይቄ በመጽሐፍ መምህርነት ወደ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል መጣሁ። እንግዲህ ከ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እዚህ ነው ያለሁት።
ስምዐ ጽድቅ፦ አሁን እዚህ ከመጡ በኋላ በመጽሐፍ መምህርነት ቀጠሉ ማለት ነው? የምን ያህል ተማሪዎች አሉዎት?
አባ አእምሮ ፦ ወደ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ተዛውሬ ስመጣ በመጽሐፍ መምህርነት ቢሆንም ብዙ ተማሪ ግን አልነበረም። እንደመጣሁ አካባቢ መጽሐፍ መምህርነት ጀምሬ ነበረ ፤አንድ አራት ልጆች መጥተው መማር እንደጀመሩ የሚበላ የለም፣ የማስተማሪያ
ቤት የለም ማንም ዞር ብሎ የሚያያቸውና የሚረዳቸው በማጣታቸው ተማሪዎቹ ጥለውት ሄዱ። እነዚህን ልጆች
ቤተ ክርስቲያን መጠለያ እንኳ ብትሰጣቸው ለምግባቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ ደግ ነው ለምነው ይማሩ ነበር፤ ሆኖም የሚያስተባብር በመጥፋቱ ትምህርቱን አቋርጠው ጥለውት ሄደዋል። ከዚያ ወዲህ ምንም ተማሪ የለም። የመጽሐፍ መምህርነቱ በዚህ ምክንያት ከመቆሙ ውጪ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለይ በስብከተ ወንጌል ሳገለግል ነው የቆየሁት አሁንም እያገለገልኩ ነው።
ሌላው ወደ ደብረ መዊዕ እንደመጣሁ በቦታው ላይ ፊደል የሚያስቆጥር መምህር አልነበረም፤ እኔም ዝም ብዬ ከምቀመጥ ለምን ልጆችን ፊደል አላስቆጥርም? ብዬ በራሴ ፍላጎት እና መነሣሣት ማስማስተማር ስጀምር ብዙ የአካባቢው ልጆች መጡ። ግእዙን፣ ውዳሴ ማርያሙን፣ ንባቡን፣ ዳዊቱን ሁሉ አስተምራለሁ። ማታ ማታ መጠለያው እና አዳራሹን ሞልተው ነው ሕፃናቱ የሚማሩት። አሁን ዓለማዊው ትምህርት በፈረቃ ስለሚሰጥ ትምህርት በሌላቸው ቀን እየመጡ ጥዋት እስከ ስድስት ሰዓት እና ማታ ከአስራ ሁለት ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት ይማራሉ፤ ሆኖም ብቻዬን ነው የማስተምራቸው አጋዥም የለኝም።
ከማስተምራቸው ውስጥ ከፊደል ጀምረው፣ ዳዊት ዘልቀው ውዳሴ ማርያም፣ መልካ መልኩን ሁሉ የጨረሱ አሉ። መጀመሪያ መልእክተ ዮሐንስን ግእዝና ወርድ ንባቡን አስነብባቸዋለሁ እሱን ካነበቡ በኋላ ወንጌለ ዮሐንስን ቀጥሎ ዳዊትን አስነብባቸዋለሁ። ከዚህ በፊት ግን በስመ አብ ብለው ጀምረው ውዳሴ ማርያም አንቀጸ ብርሃን፣ መልካ መልኮቹን እነዚህን ጨርሰው ነው ወደ ምንባብ የማመጣቸው።
ሂደቱ እንደዚህ ነው በዚህ መካከል ይህን ሁሉ ጨርሰው ዳዊት የሚማሩ ጎበዝ ሴቶች ልጆች አሉ፤ ዳዊቱን ጨርሰውም አጠናቀው የሄዱ አሉ። አሁንም በጣም ጎበዝ የሆኑ ሴቶች ልጆች አሉ። የወንጌሉን ንባብ ጨርሰው ወደ ዳዊት የሚገቡ ማለት ነው። ወንጌል ከጨረሱ በኋላ ዜማ የሚፈልግ ካለ ወደ ዜማ ቤት፣ ቅዳሴ የሚፈልግ ወደ ቅዳሴ ቤት ይሄዳሉ። ቅዳሴ ቤት የገቡ ብዙዎች ናቸው ቅዳሴውን ጨርሰው አሁን ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ብዙ ልጆች ናቸው። እስከዛሬ እየተማሩ የሄዱ በቁጥር ይህን ያህል ናቸው ብዬ መናገር ባልችልም ብዙ ዲያቆናት እየተማሩ ዲቁና እየተቀበሉ ሄደዋል። እዚህም በተራ እየገቡ የሚቀድሱ ዲያቆናት ብዙ ናቸው። ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያም ንባብ የሚማሩ አሁንም ሞልተዋል።
ስምዐ ጽድቅ ፦ እርስዎ ያፈሩዋቸው ተማሪዎች ምን ያህል አሉ ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያናችን የተለያዩ መዋቅሮች ላይ ካሉ ቢነግሩን?
አባ አእምሮ፦ በእርግጥ ካስተማርኩዋቸው ተማሪዎች እልቅና ላይ የደረሰ ሰው የለም፤ ናዝሬት እያለሁ ካስተማርኩዋቸው ውስጥ አሁን በቤተ ክርስቲያን በአገልግሎት ላይ የሚገኙ አሉ። ቅድም እንደነገርኩሽ እዚህ ከመጣሁም መጽሐፍ የሚማር ተማሪ ባለመኖሩ ንባቡን ዳዊቱን ይህንን መልካ መልኩን እሱን እሱን ነው የማስተምር እነዚህ ብዙ ናቸው። በደሞዝም የተቀጠሩ በአብዛኛው በዲቁናና በቅስና አገልግሎት ላይ ነው ያሉት።
ስምዐ ጽድቅ፦ በዚሁ በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በስብከተ ወንጌል፣ የኮሌጅ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፣ የተለያዩ ማኅበራትን እና ምእመናን ያስተምሩ እንደነበር ይነገራል እስኪ ስለዚያ ይንገሩኝ?
አባ አእምሮ፦ እውነት ነው በስብከተ ወንጌል፣ በአካባቢው ላይ ያሉ የኮሌጅ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞችንና የተለያዩ ማኅበራትን ሰብስቤ ስብአስተምራለሁ። ለምሳሌ ማኅበረ ቅዱሳን ሰብስቧቸው በዚህ ግቢ የሚማሩ የቅዱስ ጳውሎስ የጤና ተማሪዎች ነበሩ። ከነዚህ ተማሪዎች ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ በጣም ነው የሚስደስተኝ። ጉባኤውን በጸሎት ማስጀመርና ሲያልቅ በጸሎት በመዝጋት እንዲሁም መምህር በሚቀርበት ጊዜ ሸፍኜ በማስተማር ማኅበሩን አግዝ ነበር። ታላላቆቹ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ለማስተማር ይመጡ ነበር።
በየዓመቱ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ እናስመርቃቸው ነበር ፊት የመጣው ይመረቃል ከኋላ የመጣው ደግሞ ይቀጥላል። በኋላ ላይም የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ተከፍቶ ስለነበር እነሱንም በዚሁ ግቢ ውስጥ ሰብስቤ ስብከተ ወንጌል አስተምር ነበር። ብዙ ተማሪዎች ከዚህ ቦታ መንፈሳዊ ትምህርት ቀስመው ሄደዋል። ያን ጊዜ አዳራሹ ስለሚጠበን ውጭ ላይ ድምጽ ማጉያ በመጠቀም ነበር የምናስተምራቸው። ይህ ጉባኤ እስካሁን ድረስ አለ እሱን ጉባኤ እኔው ነኝ የምከታተለው።
ከነዚህ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በተጨማሪ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሚካኤል፣ ቤተ ጊዮርጊስ፣ ማኅበረ አዳም ወሔዋን የሚባሉ አራት ማኅበራትን በዚሁ ግቢ ውስጥ ሰብስቤ ስብከተ ወንጌል የማስተምራቸው እኔ ነበርኩ። እነዚህ ማኅበራት ከጉራጌ ማኅበረሰብ የመጡ ነበሩ፤ ከሚማሩት መንፈሳዊ ትምህርት ባሻገር የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳድሳሉ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳንጻሉ። ገጠሩ ላይ ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው ምእመናን አስከሬን የሚቀብሩበት አጥተው ቤተ ክርስቲያን እና መቃብር ፍለጋ የስድስት ሰዓት መንገድ የሚጓዙበት ጊዜም ነበረ፤ እነዚህ ማኅበራት እንዲህ ዓይነት ችግር ባሉባቸው ቦታዎች በመሄድ አብያተ ክርስቲያናትን በቅርባቸው አሳንጸውላቸዋል። ይህን ሁሉ ያደረጉት እዚህ መጥተው ወንጌል በመማራቸው ነው። የእነርሱ ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው ማለት ይቻላል።
ሌላው ማኅበረ ቅዱሳን ወደዚህ ካቴድራል በመምጣት እና ፈቃድ በመውሰድ በአካባቢው ላሉ የመንግስት ሰራተኞች መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጥ ነበር። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ የፓስተር ኢንስቲዩት፣ የጤና ጣቢያ፣ የመድኃኒት ፋብሪካ፣ የመናኸሪያ ሰራተኞችን ዓርብ ዓርብ አስተምር ነበር። ለነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ደብዳቤ ሰጥቶኝ ነው እያገለገልኩ ያለሁት። ብዙ ሰራተኞች እየመጡ ይማሩ ነበር፤ አዳራሹ እየሞላ ውጭ ቆመው የሚማሩ ነበሩ።
ስምዐ ጽድቅ፦ አሁን ጉባኤው እንዴት እየሄደ ነው?
አባ አእምሮ፦ አሁን እንኳ በኮረና ምክንያት አገልግሎቱ ቆሞ ነበር በዚህ ሰሞን ጀምረናል አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው። እዚህ ጤና ጣቢያው ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ልጆች አሉ እነሱ ሌሎች ሰራተኞችን እየቀሰቀሱ ጉባኤው እንደበፊቱ ተጀምሯል።
ስምዐ ጽድቅ፦ እንደ እርስዎ ያሉ መምህራን እንዲበዙ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለባት ይላሉ?
አባ አእምሮ፦ ቤተ ክርስቲያን ተተኪ መምህር እንዲበዛ ተግታ መሥራት አለባት እላለሁ፤ አሁን ግን ያ እየሆነ አይደለም። ይልቁንም ማኅበረ ቅዱሳን ገጠሩ ድረስ ዘልቆ እየሠራ ነው። ቤተ ክህነት፤ ባለ ሀብት የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ መንግሥት ለዚህ ስራ በኅብረት ቢሰለፉ ጥሩ ነው እላለሁ። በተለይ ቤተ ክህነት አጥብቆ ሊያስብበት ይገባል። የአብነት መምህራኑ የታሉ ተብለው ተፈልገው ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል። ያኔ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተተኪ ትውልድን ያፈራሉ። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ይተባበር ነው የምለው። ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል እላለሁ።
እኔም እኮ አሁን ቁጭ ብዬ የማስተምረው ዳቦ ስላገኘሁ ነው። እኛ ስንማር ደረቅ ባቄላ፣ ለምለም እንጀራ በልተን ነው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እዚህ የደረስነው። የአብነት መምህራኑን እንደዚህ የሚያስቀጥል ሁኔታ አይደለም ዛሬ ያለው። ለዚህ ነው የአብነት መምህራኑ በደንብ ሊያዙ ይገባል የምለው። አሁን ማኅበሩ ብቻ ነው እየሠራ ያለው ለምሳሌ ጎንደር መንበረ መንግሥት አራቱ ጉባኤ ቤት ማለት ነው ተማሪው በጀት ወጥቶለት ሰርከ ኅብስት ተሰጥቶት ያው ያቺን እየበላ እየተማረ ነው። እንደ አገባባቸው የጊዜ ገደብም ተሰጥቶአቸው የተማረው ቦታ እየለቀቀ ያልተማረው እየገባ ነው ያለው፤ እንዲህ ቢሆን ብዙ ነገር ይሠራል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ዕድል አንድና ሁለት ቦታ ነው ያለው ሌላ ቦታ የለም።
እንዲህም ሆኖ በገጠሩ ዓለም የእግዚአብሔር ሥራ ይገርማል። በደመወዝ ሳይሆን በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቀው የሚያስተምሩ አባቶች ሞልተዋል።
ስምዐ ጽድቅ፦ ትምህርት ቤት እያሉ የመገልበጥ ሥራ ከሠሩባቸው መጻሕፍት ውጪ የጻፏቸው መጻሕፍት አሉ?
አባ አእምሮ፦ በዓይኔ ምክንያት መጽሐፍ ማዘጋጀት አልቻልኩም። እንኳን መጽሐፍ ልጽፍ የማነበውን እንኳ እየተቸገርኩ ነው ያለሁት። በጣም የሚገርመው እስከ እድሜ ልኬ ትምህርት አቆማለሁ የሚል እምነት አልነበረኝም። መሀከል ላይ ዓይኔ ታመመ አሁን አምስት ደቂቃ ሳነብ እንባዬ ነው የሚፈሰው። ተመርምሬው ነበር ዶክተሩ ዓይህ ስለተጎዳ ጥበቃ አድርግለት በማለት አሳስቦኛል። እንግዲህ በዓይኔ ምክንያት ምንም ነገር መሥራት አልቻልኩም ማለት ነው። በልጅነቴ ዓይኔ በመጎዳቱ አሁን ላይ ምንም መስራት አልቻልኩም። እንደውም ትምህርት ለመማር በጣም ተነሳስቼ ነበር ነገር ግን ዓይኔን እንዴት ላድርገው አልቻልኩም ትምህርቱን አቆምኩኝ።
ስምዐ ጽድቅ፦ በአገልግሎት ዘመንዎ ደስ የሚልዎት ወይም ያዘኑበት አጋጣሚ ካለ ገጠመኝዎትን ይግለጹልን?
አባ አእምሮ፦ በሕይወት ዘመን ጥሩም መጥፎም ነገር ይገጥማል። እኔ በሕይወቴ የተደሰትኩበት አጋጣሚ እስቴ መካነ ኢየሱስ እያለሁ አራቱን ወንጌላውያን ትርጓሜ በእጄ መገልበጤ ነው። ቀለም በጥብጬ ብዕር ቀርጬ ደብተር አስምሬ በመጻፌ ትዝ የሚለኝና የሚያስደስተኝ ትልቁ ሥራ እሱ ነው። ሌላው እዚህ ደብረ መዊዕ ከመጣሁ በኋላ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማስተማር ያሣለፍኩት ጊዜ ነው የሚያስደስተኝ፤ በእርግጥ አሁንም በዚሁ አገልግሎት ውስጥ ነው ያለሁት።
ሌላው በሕይወት ዘመኔ ክፉ አጋጣሚ ነው ብዬ የማነሳው የአብነት ት/ቤት የገጠመኝን ነው። በአብነት ት/ቤት ብዙ ፈተናዎችን አልፌአለሁ ማጣት፣መራብ፣መታረዝ ስንቱ ይዘረዘራል? በተለይ እስቴ መካነ የሱስ ብዙ አሳልፌያለሁ በእርግጥ ትልቅ እውቀት ይዤ ወጥቻለሁ እሱ ነው ትልቁ ትርፌ የምለው። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ያ ይመስለኛል ዛሬ ከሰው ፊት ያደረሰኝ። እንደዚያ የምንለብሰው፣ የምንበላው ሳይኖረን ቤተ ክርስቲያን እናገለግል ነበር። ሰዓታት፣ ማኅሌት እንቆም ነበር በፈቃዳችን ነው እንጂ ምንም አይከፈለንም። ከዚያ ህይወት የሚያስደስተው ያን ጊዜ የተሰጠን ጥንካሬና ብርታት ብቻ ነው። እንዴት ነው ሰው ምግብ ሳይበላ ውሃ ሳይጠጣ ቃለ እግዚአብሔርን እያገለገለ መኖር የሚችለው? ይህ የመላእክት ሥራ ነው እያልኩ አሁን ሳስበው ይገርመኛል።
ትምህርት ቤት ሳለን አንዲት ቁምጣና አንሶላ ነበረ ልብሳችን ሌላ የለም፤ ያችኑ ቀን ለብሰን እንውላለን ሌሊት ለብሰናት እናድራለን። ይህችው ቁምጣ ከመቀመጫዬ ላይ አለቀችብኝ ምን ላድርግ? ገንዘብ የለኝ አልገዛ፤ በቅርብ ዘመድ የለኝ አልብሱኝ አልል። አስታውሳለሁ አንድ ቀን ወደ ማታ ላይ ቁራሽ ልመና ወደ መንደር ስሄድ ከአንዱ ቤት ጓሮ ወይም ኮሲ ላይ ትልቅ ቡትቶ ተጥሏል ከዚያ ላይ ትልቅ ካኪ ተጥፎበት አየሁኝ። ያንን ቡትቶ ሰው እንዳያየኝ ይዤው ጫካ ገባሁና ካኪውን ከውስጡ አውጥቼ ከወንዝ ወስጄ በማጠብ ያንን ጥፌ የተወሰነ ጊዜ ተጠቀምኩበት። አሁን ሳስበው ይገርመኛል፤ እንባዬ ሁሉ ይመጣል። ‹‹ድህነት ከሰማይ ይርቃል የሚባለው ለካ እውነት ነው›› እላለሁ። ወይ እግዚአብሔር! ደሀውን ሀብታም፤ሀብታሙን ደሀ የምታደርገው ብዬ የነቢዩ ዳዊትን መዝሙር እያስታወስኩ አመሰግነዋለሁ። እንግዲህ ከዚያ ተነስቼ ነው ወደ ጎንደር ፤ከጎንደር ወደ ናዝሬት፤ ከናዝሬት እዚህ የደረስኩት። እዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ እንደሚታወቀው ነው ባልታሰበው ነገር ይመጣል ልብሱ፣ ጋቢው፣ ካባው ወደ ፲፩ ካባ ነው ለሰው የሰጠሁት። ይሄ ራሱ ታሪክ ነው። ለወደፊት የሚመጣውን አላውቅም እግዚአብሔር እስከዚህ ድረስ አድርሶኛል።
ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ስለሰጡን ቃለ መጠይቅ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለን?
አባ አእምሮ፦ እኔም ፈልጋችሁ መጥታችሁ ካለኝ ጥቂት እንዳካፍል እንግዳ ስላደረጋችሁኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1093
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ስምዐ ጽድቅ፡- የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ጥፋት ሲያደርሱ እንደቆዩ ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያን ጥፋቱ ከደረሰ በኋላ ጊዜያዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት ላይ ጫና ማሳደር እንዴት አልቻለችም?
ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- በመንግሥትም ሆነ በሌላ አካል ላይ ጫና አሳድሮ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ በፊት የሚቀድመውን ማስቀደም መልካም ነው። ይኸውም መጀመሪያ በጽንፈኞች ጥቃት ችግር ላይ የወደቁ ምእመናን በተቻለን አቅም መረዳት፣ ከጎናቸው መሆናችንን ማሳየትና ሥነ ልቡናቸውን ማደስ ያስፈልጋል። ይህንን ካደረግን በኋላ ደግሞ ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበትንና ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች እንደማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮላቸው እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን ሥራ ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ መሥራት ያስፈልጋል።
ሰላምን ከሌላ አካል ከመጠበቅ ደግሞ እኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ተናበንና ተግባብተን መሥራት መቻል አለብን። መናበባችን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያና ምእመናን ድረስ የሚደርስ መሆን አለበት። ቤተ ክርስቲያን ከሠራችው ያልሠራችው ይበልጣልና የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የልጆቿን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው። እንዴት ማስጠበቅ አለባት ለሚለው የመጀመሪያው አምላኳን በጸሎት በመጠየቅና ከመንግሥትና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ሊሆን ይገባል። በዚህ ዘመን በመንግሥት ላይም ሆነ በሚመለከተው አካል ላይ ጫና ተፈጥሮ ችግሮችን ማስተካከል ይቻላል ማለት ትንሽ ይከብዳል። ለአብነት በመተከል ዞን በንጹሓን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማስተካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በቦታው ተገኝተው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገው ነበር። ዳሩ ግን እርሳቸው ከተመለሱ በኋላ በርካታ ንጹሓን ወዲያው ተገድለዋል። ስለዚህ መንግሥትን የማይሰማ እንዲሁም እግዚአብሔርን የማይፈራ ትውልድ ምንም ጫና ብትፈጥር ከጥፋት ድርጊቱ አይመለስም።
እንደ ኦሪቱ ዘመን ያጠፋህን አጥፋው፣ የገደለህን ግደለው የሚሆን ከሆነ አያዛልቀንም፤ለሀገር አንድነትና ሰላምም የሚጠቅም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ሁሌም ሰላምን፣ አንድነትንና ፍቅርን ነው የምትሰብከው፤ ታጠቅ የገደለህን ግደል፤ ዝረፍ የሚል አስተምህሮም የላትም። ቤተ ክርስቲያን የትዕግሥት ቤት ናት፤ ትናትናም ክብሯን ጠብቃ ኖራለች፤ ዛሬም እየኖረች ነው፤ ነገም ለሀገር ጠቃሚና አሳቢ ሆና ትቆያለች። በሰዎች ላይ ጥፋት ስለሚያደርሱ ሰዎች ሁሉ ፈጣሪዋን ትለምናለች። ለጥፋት የተሰማሩ ኃይሎች ከጥፋታቸው እንዲመለሱና ለሰው አሳቢና የቀና ሕይወት እንዲመሩ ቤተ ክርስቲያን ሁሌም ትጸልያለች።
የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ እየተበላሸ መጥቷል። ለሀገርና ለወገን የማይጨነቁና የማያስቡ ፖለቲከኞች ተፈጥረው እየተመለከትን ነው። በሰው ሞት፣ ስደት፣ ስቃይና ችግር ሀብት ለማካበትና ሥልጣን ለመቆናጠጥ የሚያልሙ የፖለቲካ ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። ለወገን ደራሽ የመሆን ስሜት ያላቸው ሳይሆኑ አንዱን ጥሎ የማለፍ ሥሜት ያላቸው ሰው መሰል ግን አውሬ የሆኑ ፖለቲከኞች በየአካባቢው ተፈጥረዋል። በተለይ ለራሳቸው ዘውግና ሃይማኖት ብቻ የሚሠሩ በርካቶች ናቸው። ስለሆነም በሌላው ዘውግና ሃይማኖት ላይ ጫናና ጥቃት እንዲደርስ ሆነ ብለው እየሠሩ ያሉ በርካታ ፖለቲከኞች እንዳሉ የትላንቱና የዛሬው የሀገሪቱ ታሪክና ሁኔታ ማሳያዎች ናቸው።
ከዛሬ ፖለቲከኞች የወገንን ቁስል የሚጠግን ንግግር ሳይሆን የሚወጣው የሐሰት ትርክትና ድል አድራጊነት እንዲሁም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ሀሳብ ነው። የራሳቸውን ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ የሌላውን ኑሮ ደግሞ የሚያጨልሙ በርካቶች ናቸው። ትንኮሳውንና ብጥብጡን ሲፈልጉ የሃይማኖት እያደረጉ ካልሆነ ደግሞ የብሔር መልክ እያላበሱ ይኖራሉ። እነዚህን እግዚአብሔር ወደ ኅሊናቸው እንዲመልሳቸውና ወገናዊ ፍቅር እንዲኖራቸው እንጸልያለን።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ያለውን የፀጥታ ችግር ለማስተካከል የክልል የፀጥታ ኃይልን ጨምሮ መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በቦታው ቢሰማሩም አሁንም ድረስ በአካባቢው በየቀኑ ሞትና መርዶ አለ። ሰዎች በግፍ ተፈናቅለዋል፤ በአካባቢያቸው ለዘመናት ያፈሩት ሀብት ንብረት ወድሞባቸዋል። ይህ ተግባር እንዲቆም ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት “ከታሪክ እንማር፣ ከክፉ ነገር እንመለስ እንዲሁም ለሀገር ሰላምና አንድነት እንቁም “ እያለች ያለምንም ልዩነት ጥሪ እያቀረበች ነው።
ስምዐ ጽድቅ፡- የምእመናንና የቤተ ክርስቲያንን ደኅንነት ለመጠበቅ በሀገረ ስብከትዎ ያለው የወጣቶች አደረጃጀት ምን ይመስላል?
ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- ወጣቶች የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገረ ስብከታችን ጌጦች ናቸው። ወጣቶቻችን የእኛ አባቶች እጣፈንታዎች ናቸው። በወጣቶቻችን ደግሞ መሥራት ያለብንን ሁሉ እንሠራለን። ቤተ ክርስቲያን እንጠብቅበታለን፤ ሕዝቡን እናንጽበታለን፤ ማንኛውንም ተልእኮ እናከናውንበታለን። ወጣቱን ትውልድ በሃይማኖትና በምግባር አቅንቶ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠቀም ዘመኑ የሚጠይቀው ተግባር ነው። ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች የራቀና የተለየ አገልግሎት የላትም። ቤተ ክርስቲያን ወጣቶቿን በአብነት ትምህርት ቤትና በሰንበት ትምህርት ቤት አቅፋ ስታስተምር ቆይታለች። አሁን የምናያቸው ዲያቆናት፣ ካህናትና ጳጳሳት ከአብነት ትምህርት ቤቶች የወጡ ናቸው። እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑና በሥነ ምግባር የታነጹ ወጣቶች ደግሞ ከሰንበት ት/ቤት የወጡ ናቸው።
ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች የተለየ አገልግሎት ኖሯት አያውቅም። በሀገራችን በየአካባቢው ምእመናን ተገደሉ፣ ተፈናቀሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ተዘረፉና ተቃጠሉ የሚሉ ዜናዎችን መስማት እየተለመደ የመጣ ተግባር በመሆኑ እነዚህ እኩይ ተግባራት ወደ ሀገረ ስብከታችን ከመምጣታቸው በፊት ቅድመ ዝግጅት አድርገናል። ዘመኑ መለወጡንና አሰላለፉ መቀየሩን በመረዳታችን ወጣቶችን ማደራጀትና ማሰባሰብ ጀምረናል። ይህ ወጣት ሀገሩን ወገኑን እንዲወድና በሃይማኖቱ የቀና በሥነ ምግባር የታነፀ እንዲሆን እየሠራን ነው። ከዚህ ባሻገር ወጣቱ ትወልድ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናንን ድኅነትን ተደራጅቶ እንዲጠብቅ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ወደፊትም በትኩረት ይሠራሉ። ወጣቶችን ለማሰባሰብ ሲታሰብ መጀመሪያ የተወሰደው ርምጃ የጽዋ ማኅበራትን ወደ አንድ ማሰሳበብ ነው። ስልታዊ እቅድ ነድፈን ከቀን ሠራተኛ እስከ መንግሥት ሠራተኛ ድረስ ሕግና መመሪያን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት የተከተለ አደረጃጀት ፈጥረናል። ለወደፊቱ ከተደራጁ ወጣቶች መካከል ቋሚ የሥራ እድል ያልተፈጠረላቸውን ወጣቶችን በመለየት የሥራ እድል የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ቢቻልም መልካም ነው።
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሥር የተደራጁ ወጣቶች ‹‹የባሕር ዳር የወጣቶች ኅብረት›› የሚባል ሲሆን በማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡ እነዚህ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ሲደርሱ የነበሩ ችግሮችን የቀረፉና ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ አካላትንም ወደ ሕግ ሲያቀርቡ የቆዩ ናቸው። ወጣቶች አንድነታቸውን ባጠናከሩ ቁጥር ኃይል እንዳላቸውና ቤተ ክርስቲያናቸውን ከክፉ ነገር መጠበቅ እንደቻሉ አሳይተዋል። ለወደፊቱም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁሉ ወጣቱን ያቀፈ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን የማትሻገረው ፈተና አይኖርም ብዬ አምናለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፡- ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?
ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- በእኛ ሀገረ ስብከት ያሉ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የቤተ ክርስቲያንን ትልቅነትና ኃያልነት የተረዱ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን በምታዛቸው ጊዜ ሁሉ ታዛዥ ናቸው። ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ነገር ግን ሁሉም ለቤተ ክርስቲያን ቀና የሆነ አመለካከትና የታዛዥነት መንፈስ አላቸው። ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ባውለታ መሆኗን በደንብ የተገነዘቡ በመሆናቸው እኛ ወደ እነርሱ ሳንሄድ እነርሱ ወደ እኛ መጥተው አስፈላጊውን ማኅበራዊ አገልግሎት ይሰጡናል።
በዚህም ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት አካላቱ እውቅና ትሰጣለች። ከባሕር ዳር የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ያሉት ልምድ ሊወስዱና ሊማሩ ይገባል። ቤተ ክርስቲያንን በወራሪና በጠላትነት ፈርጀው በርሷ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ በተለይ የታችኛው የመንግሥት አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው የመልካም ሥራዎች ተምሳሌት የሆኑ አካባቢዎች ላይ ልምድ ቢወስዱ መልካም ነው።
- Details
- Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1046
በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በጸሎት በትጋት ይመሩ በነበረበት ዘመን በ፲፱፻፸፱ ዓ.ም አንድ የወጣ ሕግ ነበር። በጊዜው በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች መነኮሳት ከገዳም ወጥተው በከተሞች የመመላለስ በዚያም የመቆየት ልማድ እየተንሰራፋ በመምጣቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የሲኖዶስ ውሳኔ እና የአባቶች ምክር መነሻ በማድረግ አንድ ሕግ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር።
መነኮሳት የፈቃድ ወረቀት ሳይዙ በከተማ ወይም ከገዳም ውጪ በሆነ ስፍራ እንዳይገኙ ተክከሏል። ከገዳም ከወጡ የፈቃድ ወረቀት መያዝ አለባቸው። ያለፈቃድ የሚገኙ በሕግ አካላትም እንዲጠየቁ መመሪያ ተላልፏል። ቀሳውስትም ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደ ሌላው ሄደው ሀገረ ስብከት ዝውውር ለማድረግ ቢፈልጉ ከነበሩበት ሊቀ ጳጳስ የፈቃድ ወረቀት ማጻፍ አለባቸው። ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስያን በ፲፱፻፵፮ ዓ.ም እና በ፲፱፻፶ ዓ.ም ባወጣችው በሁለተኛው ሲኖዶስ በ፲፩ኛው፣ በ፲፫ኛው፣ በ፲፬ኛው አንቀጽ እንዲሁም በሦስተኛው ሲኖዶስ በ፬ኛው ክፍል የተወሰነውን ውሳኔ መሠረት ያደረገ ነበር ተብሏል።
ይሁን እንጂ ይሄ ሕግና መመሪያ ከወጣበት ጊዜ አነሥቶ ላለፉት ሦስት ዐሠርት ዓመታት በአግባቡ ሳይተገበር እንደውም ከጊዜ ጊዜ በባሰ ሁኔታ የመነኮሳት ፍልሰትና አግባብ ያልሆነ የከተሞች ቆይታ መስተዋሉን ቀጥሏል። ይህ ሁኔታ መልኩን እየቀየረም በገዳማት በሱባኤና በትጋት በሚቆይባቸው የጾም ወራትም ተከብሮ አለመገኘቱ ደግሞ የበለጠ ያሳስባል።
መነኮሳት ወደ ከተማ እንዳይመጡ ፈጽሞ የተከለከለ ባይሆንም ለገዳሙ በመላላክ፣ ወይም የእነሱን ወደ ከተማ መምጣት የሚያስፈልግባቸው የጋራና የግል ጉዳዮች ሲኖሩ የፈቃድ ወረቀት ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ይፈቀዳል። ይሁን እንጂ ምክንያቱ በማይታወቅ፣ ጥንቃቄ በጎደለው፣ ድፍረትም በተሞላባት፣ አሰናካይ በሆነ ሁኔታ በአዲስ አበባና በሀገራችን አንቱ በተባሉ ከተሞች በቁጥር በዛ ያሉ መነኮሳትን ማየት እየተለመደ ነው። እነዚህ መነኮሳት በከተሞች የሚያደርጓቸው መመላለሶች ብቻ ሳይሆን በሚፈጽሟቸው ተግባራትም ለምእመናን ሰላም በማይሰጡ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በማይመጥኑ፣ ለገዳማዊ ሥርዓቱ ክብር በነፈጉ ተግባራት ውስጥም ይታያሉ። መነኮሳት ከገዳማት ሲመጡ የሚያርፉባቸው ገዳማት ሊኖሯቸው ሲገባ በየመንደሩ፣ በየሆቴሎች የሚቆዩ መኖራቸው፣ በሆቴሎችና በአደባባዮች ሲመገቡ የሚወሰድባቸው ትዝብቶች፣ አብረዋቸው በሚውሉና በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ምክንያት የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽእኖ . . . ወዘተ በቤተ ክርስቲያኒቱ እየፈጠረ ያለው ማሰናካያ ግምቱ እየከበደ ነው።
በከተሞች ያለፈቃድ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ መነኮሳት ቆቡን አስተካክለው፣ መስቀላቸውን ይዘው፣ ቀሚሳቸውን አሳምረው፣ ፈረጅያቸውን ነስንሰው፣ ምንኩስናቸውን የበለጠ በሚገልጽ አለባባስ ስለሚታዩ መነኮሳት መሆናቸውን ማንም በግልጽ የሚረዳው ሆኖ ይታያሉ። ነገር ግን አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች በአውቶብሶች ላይ ባለው ግፊያ ውስጥ የሚደርስባቸው መንገላታት፣ ክብር ማጣት፣ ከዚያም አልፎ ለቁጣና ለክርክር የሚዳርግ ሁኔታ ለምእመናን ትልቅ ቁጭት የሚፈጥር ነው። በታክሲዎች ውስጥ በተሳፋሪ ክብር ማጣት፣ በረዳቶች ማመናጨቅና ከንቱ ክርክሮች ውስጥ መታየት ለሥርኣተ ምንኩስናው የሚሰጠውን ክብር ያቀለዋል።
ከዚያ አልፈው በየመጠጥ ቤቶች አካባቢ፣ በየሥጋ ቤቶች ደጃፍ ተቀምጠው አገልግሎት ለማግኘት ሲውተረተሩ መታየቱም ለቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ሰላም የሚሰጥ አይሆንም። በስመ መነኲሴ የሚነግዱ ፤መነኲሴ ሳይሆኑ በተከበረው ልብስ ውስጥ ተደብቀው ‹‹ ወደ ገዳም ልሄድ ነውና ብር አምጡ›› እያሉ የዋሁን ምእመን ኪስ የሚያራቁቱ ብዙዎችን በየመንገዱ ማየት የተለመደ ከመሆኑም ባሻገር የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የእውነተኞቹን መነኲሳት ክብር የሚነካ ነው።
በስንት ተጋድሎ የሚገኘውን የክብር ልብስ በቀላሉ ከመርካቶ በመግዛት ተጎናጽፈው በቤት የክብር ወንበር፤ በአደባባይ የክብር ስፍራ ለማግኘት የሚሯሯጡ ‹‹የቀበሮ ባህታውያን›› በከተማው እንደ አሸን ፈልተው ሲታይ ደህነኛውን ለመለየት እጅግ አስቸጋሪ የሆነበት ዘመን ነው። ዛሬ ዛሬ ምንኩስና የእነ አባ እንጦንስን ፈለግ በመከተል ይህን ዓለም ንቆ ለእግዚአብሔር ማደሪያ መሆኑ ቀርቶ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለመሄድ ፓስፖርት ማግኛ መንገድም እየሆነ ነው።
ያለፈቃድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ መነኮሳት ሌላም ቀዳዳ እየከፈቱ ነው። መነኲሴ ሳይሆኑ መነኲሴ መስለው ለሚንቀሳቀሱ መናፍቃን በአርአያ ምንኩስናው የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ በማበላሸትና የተሳሳተ ትምህርት በመስጠት ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ያልገቡትን ደግሞ በዚያው ሳይገቡ እንዲቀሩ በማድረግ ወጥመድ ለዘረጉ ክፉዎች በር ከፍተዋል።
የቤተ ክህነቱ አስተዳዳርም ከዚህ በፊት እንደዚህ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለማስተካከል ያወጣው ሕግ እንዳለ እያወቀ ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት ጋር በመተባባርም ድርጊቱን ማስቆም አልቻለም። መነኮሳት ከገዳም የሚወጡበትንም ሁኔታ በትክክል ለማስተግበር የሚስችል ግልጽ አሠራር ከገዳማት ጋር በመተባባር አላዳበረም። ስለዚህ ተግባሩ የሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያን ሐዘን ሆኖ ቀጥሏል።
አጅግ አስገራሚው ነገር ደግሞ ምእመናን ካሉባቸው ብዙ ጭንቀቶች የተነሣ ዕረፍት ይሰጡናል ወደሚሏቸው ገዳማት በስፋት እየተመሙ፣ በጾም በሱባኤ ለመቆየት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ባሉበት በዚህ ዘመን የመነኮሳት ከገዳም ወጥቶ በከተሞች መሰንበት ነገሩን እንዴት በተቃራኒ እየተጓዘ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር ከዚህ በፊት ያወጣቻቸውን ሕጎች/መመሪያዎች አሁንም ለማንቃት ቢሞክር መልካም ይሆናል። ገዳማትም እየተጎዳ ያለው ሥርዐተ ምንኩስናው የገዳማዊ ሕይወት ክብር መሆኑንን በውል ተረድተው የውስጥ አስተዳዳር ሥርዐቱን ማርቀቅ ይገባቸዋል። ያሏቸውን ሴትና ወንድ መነኮሳት ቁጥር ማወቅ ማንነታቸውን መለየት ሕጋዊ መታወቂያ መስጠት፣ በገዳሙ ሥርዐት መሠረት የመነኮሳትን እንቅስቃሴ ምን መምሰል እንዳለበት ሥርዐታቸውን በየጊዜው ማጥበቅ ይገባቸዋል።
ምእመናንንም አጓጉል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ መነኮሳት መደበቂያ ዋሻ ከለላና ጠበቃ በመሆን የቤተ ክርስቲያንን ሥርዐታዊ አሠራር ከማወክ ሊቆጠቡ ይገባል። ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት በዚህ ረገድ ያለውን ጥፋት ከግምት ያስገባ እርምጃ መውሰድም ያስፈልጋቸዋል።
ይህ ካልሆነ ገዳማዊ ሥርዐት የማይወደድ የማይፈለግ፣ ከዓለማዊ አኗኗር ያልተለየ እንዲመስል ያደርገዋል። የዋህና ትሑት አባቶች በፈቃድ ሲንቀሳቀሱ የሚገባቸውን ክብርና ነጻነት እንዳያገኙ ወጥመድ ይፈጥራል። ለመናፍቃን እንቅስቃሴ አመቺ መንገድ ይከፈታል። የቤተ ክህነት አስተዳደር አቅምም ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ብሂል ማሰብ ይገባል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር