- Details
- Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1225
በኢትዮጵያ ‹‹መልካም ንጉሥ ይነግሣል›› የሚል ትንቢት እንዳለ በትውፊት ሲወራረድ የመጣ ንግር አለ።ከዚያ በመነሣትም ከመካከለኛው የኢትዮጵያ የታሪክ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ ጭንቅ በከበባት ቁጥር የትንቢቱ ፍጻሜ ይናፈቃል።እንዲህ ያለው ልማድ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ ቆይቷል።በኢትዮጵያ የረጅሙ ዘመን በተለይ በዘመነ መሳፍንት የዚህ ንግር ፍጻሜ ናፋቂዎች በርክተው ስለነበር መሳፍንቱን አሸንፈው የነገሡት ራስ ካሣ ኃይሉ ዐጼ ቴዎድሮስ ተብለው እንዲነግሡ ምክንያት እንደሆነ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ “Literary Origins of Ethiopian Millenarianism” በሚለው ጥናታቸው ይጠቅሳሉ።በዚህም ሳያበቃ ውጣ ውረድ በመጣ ቁጥር ይሄንኑ ፈታሒ ንጉሥ የመናፈቅ ጉዳይ በክርስቲያኑ የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ ሲንጸባረቅ ቆይቷል።በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ በርካቶች ራሳቸውን ‹‹ቴዎድሮስ›› አድርገው በማሰብ፣ በመቃዠት ከትውልድ ትውልድ ተፈራርቀዋል።በርካቶች ለአእምሮ መታወክ ተዳርገዋል።ዛሬም ድረስ ይሄው ልማድ ይንጸባረቃል።በብዙኃን መገናኛዎች ጭምር እኔ ንጉሥ ነኝ የሚሉ ወጣቶች ታይተዋል።ያልጨበጡትን እንደጨበጡ፣ ይልሆኑትን እንደሆኑ የሚሰማቸው ተጎጂ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ነው።
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 2333
የተወደደዳችሁ አንባብያ የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል።ቀጣዩንና ሁለተኛውን ክፍል ደግሞ እነሆ፦
ውድ እኅታችን እኅተ ገብርኤል! ሴቶች በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን የማይገቡበት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት አንዱ ከሆነው ከቅዱስ ቁርባን ክብር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄደው ለማስቀደስና የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለመቀበል ነው። ከቅዱስ ቁርባኑ የሚቀበል ሰው ደግሞ መንፈሳዊና አካላዊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ከአካላዊ ዝግጅት መካከልም ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ (ሕልመ ሌሊት፣ ደመ ጽጌ፣ የቁስል ፈሳሽ፣ የአፍንጫ ፈሳሽና የመሳሰሉት) ሊኖረው አይገባም የሚለው አንዱ ነው። ይህም የሚሆነው ለቅዱስ ቁርባን ከሚሰጠው ልዩ ክብር የተነሣ ነው። በዚህም መሠረት ሴቶች በወር አበባ ወቅት፣ ወንዶችም ሕልመ ሌሊት ከታያቸው፣ ባለትዳሮችም ለሦስት ቀናት ራሳቸውን ከሩካቤ ካልከለከሉ ከቅዱስ ቁርባኑ አይቀበሉም (ዘሌ ፮:፲፱-፳፩)። በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፮ ላይም “ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ወገን አንዱስ እንኳ አደፋፍሮ ከግዳጅዋ (ከደሟ) ያልነጻችውን ሴት ቤተ ክርስቲያን ያስገባ በደሟም ወራት ሥጋውንና ደሙን ያቀበላት ቢኖር ከሹመቱ ይሻር። ምንም ከነገሥታት ሴቶች ወገን ብትሆን፡፡” በማለት ሥርዓቱ ተቀምጧል። ከዚህ ውጭ ግን ከማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሳተፉ የሚከለክላቸው ነገር የለም።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1054
ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪዎች ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በዝግጀት ላይ መሆናቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በአክራሪ ሙስሊሞች ሊደረስባቸው የሚችለውን ጥቃት በማሰብ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጸሎት እንዲያስባቸው ጥሪ ማቅረባቸውን የቪዥን ክርስቲያን ሬዲዮን ዘገባ ጠቅሶ አዓም አቀፍ ክርስቲያን ኮንሰርን ዘገበ፡፡
በአፍጋኒስታን የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከሀገሪቱ መውጣት ለታሊባን እስላማዊ የሽብር ቡድን የጭቆና አገዛዝ መመለስ እና ለክርስቲያኖች ስደት በር እንደሚከፍት ገልጸዋል ሲል ዘገባው አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ እና የኔቶ ሰላም አስከባሪ አባል ሀገራት እስከ ነሃሴ ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ ከአፍጋኒስታን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ዘገባው የገለጸ ሲሆን በታሊባን እና አሁን ባለው የአፍጋኒስታን መንግሥት መካከል የሰላም ስምምነት ባለመኖሩ ታሊባን ሀገሪቱን መልሶ እንዲቆጣጠር ያደርገዋል ተብሏል፡፡
Read more: ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪዎች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸውን ተከትሎ የአፍጋኒስታን ክርስቲያኖች ዓለም በጸሎት እንዲያስባቸው ጠየቁ
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1376
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥ ካሏት ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት በተጨማሪ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ከስድስት በላይ ገዳማት ያሏት ሲሆን ይህም በኢየሩሳሌም የራሳቸው የገዳም ይዞታ ካሏቸው ጥቂት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ያደርጋታል። በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የግሪክ፣የአርመን፣የኢትዮጵያ እንዲሁም የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው የገዳም ይዞታ አሏቸው። ይሁን እንጂ በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ሥር ያሉ ገዳማዊ ይዞታዎች ከአወዛጋቢነታቸው በተጨማሪ በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል የቁርሾና የብጥብጥ መነሻ ሲሆኑ ይስተዋላል። ይህ የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ለዓለም ሕዝብ የታሪክ ማእከል ነው። ክርስቲያኑም እስላሙም፣ ካቶሊኩም፣ ፕሮቴስታንቱም በኢየሩሳሌም ይዞታ እንዲኖረው ይፈልጋል። ይህ የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም። ዓለምን የለወጠ፣ ጨለማን ያሰወገደ፣ ለዘለዓለማዊ ሕይወት መሠረት የሆነ ተአምር ተፈጽሞበታልና ነው። ብዙዎቹ በእምነቱ ባይገኙም ቦታውን መያዝን እንደ ትልቅ ጀብድ ቈጥረውትና የጽድቅ ማረጋገጫ አድርገውት ይታያሉ።
በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያሉ ጥንታዊ ገዳማት የብዙ አካላት ዐይን ያረፈባቸው በመሆናቸው አንዱ የሌላውን ይዞታ ለመንጠቅ የሚያደረገው ጥረት ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በዚህ ምክንያት በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል ከትብብርና መከባበር ይልቅ መገፋፋት ይስተዋላል። በሃይማኖታዊ ወንድማማችነት መንፈስ ከመተያየት ይልቅ እንደባላንጣ በመተያየት የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን ቅድስና የማይመጥኑ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል፤ እየተፈጸሙም ይገኛሉ።
Read more: “በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያሉ ጥንታዊ ገዳሞቻችን አስቸኳይ ጥበቃና ክብካቤ ይፈልጋሉ! ክፍል አንድ
- Details
- Written by: እህተ ሚካኤል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1808
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከረማችሁ? ደኅና ናችሁ? የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን!!
ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ቅዱስ ሚካኤል ለባሕራን ስላደረገው ተአምራት ነው፤መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!
ሰኔ ፲፪ ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል በዓል የሚከበርበት ልዩ ቀን ነው። ልጆች! ‹‹ሚካኤል›› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ሚ›› -- መኑ ‹‹ካ ›› -- ከመ ‹‹ኤል›› -- አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ ‹‹ መኑ ከመ አምላክ›› (እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው) ማለት ነው። ‹‹ሚካኤል›› ማለት አንድም የቸርነትና የርኅራኄ መገኛ መዝገብ ማለት ነው።
ቅዱስ ሚካኤል ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ›› ራእይ ፰፥፪ ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ የሾመው ነው።
ልጆች! ንግሥት ክሌዎፓትራ ‹‹ ሳተርን›› የሚባለው ጣዖት ቤተ ጣኦት በእስክንድርያ አሠርታ ነበር። ይህ ቤተ ጣኦት እስከ እስክንድርያው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ ዘመን ድረስ ነበር። እለ እስክንድሮስም ይህን ቤተ ጣኦት ሊያጠፋው ሲነሳ የሀገሩ ሕዝብ ያመልክት ነበርና ‹‹እስከዛሬ የነበሩ ዐሥራ ስምንት ፓትርያርኮች ያልነኩትን ቤተ ጣዖት አንተ ለምን ታፈርስብናለህ? ብለው ተቃወሙት።
- Details
- Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1727
ቤተ ክርስቲያን በስመ እግዚአብሔር ወይም እርሱን በሚወዱና በሚያከብሩ ቅዱሳን ስም ተሠይማ በየአካባቢው ትሠራለች። በዚያም ምእመናን ተሰብስበው መንፈሳዊ አገልግሎት ያገኙባታል። የእግዚአብሔር አገልጋይ ካህናት የእግዚአብሔርን መንጋ ሰብስበው ያገለግሉባታል። ሁሉም በጋራ ይጸልዩባታል። ስለዚህም የጸሎት ቦታ ነች። የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫና ማደሪያ የሆነው የቃል ኪዳኑ ታቦትም ማደሪያ ናት። ሌሊትና ቀን ስመ እግዚአብሔር በዝማሬ ይከብርባታል። ስለዚህም የተወደደች የምስጋና ቦታ ነች። እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሁሉ በትሕና ተገኝተው ይሰግዱባታል። ለፈጣሪያቸው ያላቸውን ታማኝነት ይገልጡባታል፤ ስለዚህም የተከበረች የአምልኮ ቦታ ነች። እንደ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ካህናት ሆነው በኅብረት እግዚአብሔርን የሚያክብሩባት፣ ምሥጢራትን ሁሉ የሚፈጽሙባት፣ ሰውን ከፈጣሪው ጋር የሚያገናኙባት የአንድነት/የፍቅር/ ቦታ ነች።
በዚህ ደረጃ የምትገለጽ ቤተ ክርስቲያን በሚገባት ክብር መጠን ልትጠበቅ ይገባል። ምእመናን በመንፈሳዊ ሕይወት የሚታነጹት መንፈሳዊ ስፍራ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሥፍራ የሚፈጸሙ ተግባራት ሁሉ ዓላማቸው መንፈሳዊ ብቻ ሊሆን ይገባል። በዝክር፣ በተዝካር፣ በሰንበቴ፣ በጽዋ ማኅበር ስም ሊበላባቸው፣ ሊጠጣባቸው ይችላል። መንፈሳዊ በዓላትን ለማክበር አስበን ነጭ ልብስ ልንለብስባቸው እንችል ይሆናል። ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ የግብርና ሥራዎችን ልንሠራባቸው እንችል ይሆናል። ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ጧፍ ዕጣን፣ ጥላ፣ ጽዕሓ፣ ልብሰ ተክህኖ ወዘተ ንዋየ ቅድሳትን ልንሸጥባቸው እንችል ይሆናል። ከዚህ ባለፈ ግን ለአንድ ሰው ወይም ለሆነ ቡድን/ማኅበር/ ለግሉ ጥቅም የሚውል ተግባር ማከናወን የማይገባ ነው።
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 2920
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነኝ። ስሜ እኅተ ገብርኤል ይባላል የ፳፬ ዓመት ወጣት ስሆን የምኖረው ወሊሶ ከተማ ነው። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች በሕይወቴ ውስጥ ጥያቄ ሆኖ የቆውን ጉዳይ ለእናንተ ላካፍል ወደድኩ። የወር አበባ በማይበት ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እፈራለሁ ሕጉንም ስለማላውቅ ምናልባት ኃጢአት ይሆንብኝ ይሆናል በሚል የወር አበባ ላይ በምሆንበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑን ቅጥሩን እንኳ መንካት እፈራለሁ።
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1134
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። በሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት ታሪክ ውስጥ ቅድምና ያላት እንዲሁም በአገልግሎት ተደራሽነቷ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሰፊው አገልግሎቷ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲፈራረቁበት ቆይታለች። ራሱን የቻለ ሀገር በሆነው አገልግሎቷ ውስጥ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮችን እያሳለፈች ዛሬ ላይ ደርሳለች።
በሀገር ውስጥ ትልቁን የባለቤትነት ድርሻ ይዛ የነበረችው ታላቋና ስመ ገናናዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ሂደት ውስጥ ከዚህ ትልቅ ክብር ስትገፋና እንድትርቅ ስትደረግ ቆይታለች። የነበራት መልካም ስምና ዝና ሆን ተብሎ በተለያዩ ምክንያቶች እንዲጠለሽ ሲደርግ ቆይቷል። ሀገር ናት የተባለላት ደግሞም በእውነት ሀገር የሆነች ቤተ ክርስቲያን በክልል ብሎም በመንደር እንድትወሰን ተደርጋለች። ቀስ በቀስ ሥር እየሰደደ የመጣው የጎሰኝነት በሽታ ደግሞ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ ዛሬ እየደረሰባት ላለው ችግር ዳርጓት ይገኛል።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1250
በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እየተከሠቱ ላሉት ችግሮች ዋና መንሥኤዎች ጥንታዊው መንፈሳዊ ሕይወትና ቀኖናዊ ሥርዓት በቤተ ክርስቲያኒቱ የዕለት ተዕለት የአስተዳደር ሕይወት ውስጥ መጥፋቱ ነው። በተጨማሪም አስተዳደራዊ ሥርዓቷ ጥንታዊ መሠረቱን ጠብቆ የዘመኑን ፈተና ባገናዘበ መልኩ ባለመቃኘቱ በኹለቱም አቅጣጫ ጽኑ የሥነ ምግባርና የአስተዋይነት ድርቅ የመታው ኾኖ መታየቱ ነው። ይኽም የሚያስገነዝበን በአኹኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ከምን ጊዜውም በላይ ጥንታዊ ትውፊቷን አጽንታና አጠናክራ እርሱንም መሠረት አድርጋ ሕጓንና ሥርዓቷን ዘመኑን በዋጀ ኹኔታ ልትቃኝና ልትገነባ የሚያስፈልግበት አስገዳጅ ወቅት ላይ የምትገኝ መሆኗን ነው። ለአንድ አፍታም ቢኾን ልንዘነጋው የማይገባ፣ ከኹሉም ነገር በለይ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚያስፈልግ ከትናንት ያደረ የቤት ሥራችን መኾኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ይህም አሠራር ከጥንት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ሕይወት ውስጥ ያለ እንጂ ዛሬ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ኾኖ የመጣ አይደለም። አበው ቀኖናን ሲደነግጉ ከእነሱ በኋላ የሚመጣውን ዘመንና ትውልድ በማሰብ “ከቀኖናት ውስጥ የተነገረው ኹሉ ሌላውን ለውጦት ሲገኝ የሚበዙት ያሸንፉታል። ከጊዜው ጋር የሚስማሙና ለልቡና የሚመጥኑ የሀገር ልማዶችም ያሸንፉታል በማለት እንደተናገሩት ይህ ድንጋጌ ቤተ ክርስቲያን አሁን ላይ ያሉትን የአስተዳደር መርሆዎቿን ጥንታዊ መሠረታቸውን ሳይለቁ ከጊዜው ጋር የሚጣጣሙ ለልቡና የሚመጥኑ ልታደርግ እንደሚገባት የሚያስተምር ምክረ ሊቃውንት ፍኖተ አበው ነው።
- Details
- Written by: መጽሐፈ ሲራክ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1182
ብዙዎች የበረሃው ምንጭ ይሏቸዋል። ቤተ ክርስቲያንን ማሳነጽ፣ የፈረሱትን ማሳደስ ምእመናንም አስተባብሮ ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት ጸጋቸው ነው። በዚህ ዕድሜያቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በየገጠሩ፣በየበረሃው ተዘዋውረው ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን አደራ ለመወጣት ዛሬም ይተጋሉ። በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁልጊዜ ከፊት ናቸው፤መጠየቅ ያለባቸውን ይጠይቃሉ፣መገሠፅ ያለባቸውን ይገሥፃሉ። ሲያስተምሩም እንደዚያው የዛሬው እንግዳችን ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሙሉ ታሪካቸውን ከራሳቸው አንደበት እንስማ መልካም ንባብ
ስምዐ ጽድቅ፦ ብፁዕ አባታችን ሙሉ ስምዎን ከነ መዓርግዎ ቢነግሩን
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ አባ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነኝ።
ስምዐ ጽድቅ፦ እስቲ ስለ ልጅነት ሕይወትዎ ይንገሩን የት ተወለዱ? የት አደጉ? እናትና አባትዎ ስማቸው ማን ይባላል? ሞያቸውስ?
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ የተወለድኩት በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ልዩ ስሙ የትኖራ ሚካኤል የሚባል ቀበሌ ሰኔ ፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ነው። አባቴ ስማቸው መምሬ ኃይለ ማርያም ድብቁ ይባላሉ እናቴ ደግሞ ወ/ሮ ስናፍቅ ወልደ ማርያም ይባላሉ የቄስ ልጅ ናቸው። አባቴ ጥሩ የተማሩ ካህን ነበሩ፤ በሙያቸውም ሙሉ ሰው ነበሩ። ቅኔውን፣ ድጓውም፣አቋቋምን ፣ ቅዳሴውንም ሁሉ አጠናቀው የያዙ ነበሩ። በዚያ ላይ የሀገር አባት ነበሩ። ወንድሞች እና እኅቶች አሉኝ ከኔ በላይ ብዙ ልጆች ነበሩ ሞት ወስዶአቸዋል። ከኔ በታችም አሉ።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1165
ማኅበረ ቅዱሳን ለገቢ ማስገኛ እንዲውል የገዛውን የጋራ መኖሪያ ቤት ለዋልድባ ዳልሻ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ ደናግል የእናቶች እንድነት ገዳም ተወካይ ካርታውን ማስረከቡን የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርትቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ ዲ/ን አንድነት ተፈራ አስታወቁ።
የጋራ መኖሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ችሎት በተባለው አካባቢ እንደተገዛ የገለጡት ም/ኃላፊው አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሥልሳ ሥድስት ሽህ ሥድስት መቶ ሰማንያ ሥድስት ብር ወጪ እንደተደረገበት ተናግረዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቱ በገዳሙ የሚኖሩ እናቶች አቅመ ደካሞች በመሆናቸው ሠርተው መኖር ባለመቻላቸው ዘላቂ የሆነ የገቢ ማስገኛ እንዲሆናቸው ታስቦ የተገዛ ነው። ከአሜሪካ ሀገር ዳላስና ሀገር ውስጥ ከሚኖሩ ምእመናን በተሰበሰበ ገንዘብ ማኅበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቱን መግዛቱንም ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ገዳሙ የተገዛለትን የጋራ ምኖሪያ ቤት አስፋፍቶ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሊሆን በሚችል መንገድ መሥራት እንዳለበት የጠቆሙት ም/ኃላፊው ማኅበሩም ለገዳሙ አስፍላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። የጋራ መኖሪያቤቱ ሲገዛ ከፍተኛ እገዛ ያደረጉ ምእመናንም ለወደፊቱም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አያይዘውም ገዳሙ ያሉበትን የውኃና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ማኅበሩ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቅሰው የጋራ መኖሪያ ቤት ግዥው እውን እንዲሆን እገዛ ያደረጉትን የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስንና የወረዳ ማእከል አባላቱን አመስግነዋል።
የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሤ መብራቱ በበኩላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቱ እንዲገዛ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ድጋፍ ላደረጉ ምእመናን ምስጋናቸውን አቅርበው ገዳሙ የበለጠ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የተለመደ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቱን ካርታ የተረከቡት የገዳሙ ተወካይ እማሆይ አስካለ ማርያም ማኅበሩ ላደረገላቸው ድጋፋ አመስግነው ለወደፊቱም የማኅበሩም ሆነ የምእመናን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዳይለያቸው አሳስበዋል።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1088
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎቿን በሕግ አግባብ የማስከበርና የማልማት ውስንነቶች እንዳሉባት የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት መምሪያ ኃላፊ አፈ መምህር ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ ገለጡ።
ኃላፊው ይህንን የገለጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋዮች በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ገለጻ ነው።
በርካታ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች በግለሰቦችና በመንግሥት እጅ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው እነዚህን ቦታዎች አስመልሶ ይዞታቸውን በማረጋገጥ ማልማት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ከዚህ ቀደም በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥትና በግለሰቦች እጅ ተይዘው ከነበሩ ሕንጻዎች የተወሰኑትን ማስመለስ ቢቻልም ሌሎች ያልተመለሱ በርካታ ሕንጻዎችና ሌሎች ይዞታዎች እንዳሉ አስታውቀው ይዞታዎቹን ለማስመለስም ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ልጆቿ አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ለቤተ ክርስቲያን የተመለሱ ይዞታዎችን ለማልማትና ለማስመለስ በሂት ላይ ያሉትንም በፍጥነት እንደሚለሱ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ኃላፊው አስረድተው የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ ባለሙያዎች ሁሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላለፈዋል።
በዚህ ወቅት እየለሙ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች በሙሉ የልማት ሥራዎቻቸው በሙያቸው በተመሰከረላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች እየተመሩ መሆናቸውን ያስታወቁት ኃላፊው ይህም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጥበበኛ እጆች እንዳሏቸውና ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የመምራት አቅም እንዳላቸው ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያን በልማት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ኃላፊው ገልጠው በተሻለ ሁኔታ የልማት ተጠቃሚ እንድትሆን ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።