- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1042
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመበረዝ ከካቶሊክ እስከ ፕሮቴስታንት ከተሐድሶ እስከ ቅባትና ጸጋ እንዲሁም ሌሎች ለዘመናት ጥረት ሲደርጉ ቆይተዋል። እነዚህ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ካሉ ሀገራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚደረግላቸው ድጋፍ በከፍተኛ የሰው ኃይልና ገንዘብ ታግዘው ለዘመናት የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ሲሸረሽሩ ምእመናንን ሲያወዛግቡና ሲከፋፍሉ ቆይተዋል። ቤተ ክርስቲያንም ኃይለ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጋ ከቅጥሯ ውጭ ያሉትን ቀሳጥያን ከቅጥሯ ስታርቃቸው በውስጧ የነበሩ የእናት ጡት ነካሾችን ደግሞ በመምከር፣በማስተማር፣ንስሐ በመስጠት በዚህ ሁሉ አልፈው የማይመለሱትን ደግሞ በማውገዝ ከዐውደ ምሕረቷ እንዳይቆሙ ከቅጥሯ እንዳይደርሱ በማድረግ አስተምህሮዋን ከብረዛ ምእመኖቿን ደግሞ ከነጠቃ ስትታደግ ቆይታለች። እነዚህ የበግ ለምድ የለበሱ ነጣቂ ተኩላዎች ለጊዜው የተሳካላቸው ቢመስላቸውም የቤተ ክርስቲያንን አሸናፊነትና መለኮታዊ ኃይል መቋቋም ሳይችሉ ቆይተዋል። የነጣቂ ተኵላዎች ጥረትም ከንቱ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን በቻለችው መጠን ከሐዋርያዊ ጉዞዋ ሳትገታ ለዓለም ብርሃን መሆኗን ቀጥላለች።
- Details
- Written by: በእህተ ሚካኤል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1200
ልጆች! ባለፈው እትማችን በዐቢይ ጾም (በጾመ ሁዳዴ) ውስጥ ከሚገኙ ሳምንታት እና መጠሪያዎቻቸው ውስጥ ‹‹ምኲራብ›› እና ‹‹መጻዕጉ››ን ስያሜያቸውንና ታሪካቸውን ነግረናችሁ ነበር። መቼም እንዳልረሳችሁት ተስፋ እንዳርጋለን። እነሆ በዚህ ዝግጅት ደግሞ ስለ ‹‹ደብረ ዘይት›› እና ስለ ‹‹ገብርኄር›› ይዘንላችሁ ቀርበናል ተከታተሉን።
5. ደብረ ዘይት
ልጆች! አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል ይጠራል። ይህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ወደዚህች ምድር ዳግመኛ ስለመምጣቱ ፣ስለ ዓለም ፍጻሜ እንዲሁም ስለ ትንሣኤ ሙታን ያስተማረበት ነው።
- Details
- Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1247
ሰው የተፈጠረው ሕያውና መልካም የሆነው የአምላኩ የእግዚአብሔር የክብሩ ወራሽ እና የስሙ ቀዳሽ ሆኖ እንዲኖር ነው። በምድርም ላይ ክቡር፣ ትሁት፣ ባለጸጋ፣ ንጉሥ፣ ጠቢብ ሆኖ እንዲመላለስ ፈቅዶለታል። ሰው ግን ክቡርና ሕያው ሆኖ መኖር የሚችለው ፈጣሪው ያዘዘውን የሚፈጽም ለእርሱም በትሕትና የሚገዛ መሆን ሲችል ነበር። ይህንንም ‹‹መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ›› ዘፍ ፪፥፲፯ ብሎ አምላኩ ትእዛዝን ሰጠው። ይህን የመገዛቱ ማሳያ የሆነ ትእዛዝ አክብሮ ቢገኝ ሕያው ሆኖ በሥጋውም በነፍሱም መኖር በተቻለው ነበር። ካልታዘዘ ግን የሞት ሞትን እንደሚሞት ታውቋል። ሰው ግን በሰይጣን ምክር ተነሣሥቶ ይሄህን ትእዛዝ ስለጣሰ፤ ‹‹አትብላ›› ከተባለውም ወስዶ ስለበላ በሥጋም በነፍስም ሞት መጣበት። ከሞት ጋርም መራቆት፣ ሐዘን፣ ትካዜ፣ ሰቆቃ፣ መለየት፣ ውርደት፣ ስደት ደረሰበት።
ቸር የሆነው እግዚአብሔር የሰውን መጸጸት ተመልክቶ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ የድንግል ማርያምን ሥጋ ተዋሕዶ በተገለጸው በአንድ ልጁ ቤዛነት ሰውን ከሞተ ነፍስ አዳነው። ከነፍስ ሞት ታደገን በትንሣኤው በትንሣኤ ዘጉባኤ ለሚሆነው ለሥጋ ትንሣኤያችን ተስፋ ሰጠን።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1433
ምእመናን በሀገራችን ኢትዮጵያ ፍትሕ ርትዕን የሚያሰፍን የፖለቲካ ድርጅት ሊመርጡ እንደሚገባ በኢ/ኦ/ተ/ቤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ አቶ ውብሸት ኦቶሮ አሳሰቡ።
ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በሀገራቸው ፍትሕ ርትዕን የሚያመጣ የፖለቲካ ድርጅት እንዲመርጡ ማኅበረ ቅዱሳን የድርሻውን እንደሚወጣ ያስታወቁት ዋና ጸሐፊው ምርጫ ላይ ባለመሳተፋቸው በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመጣ የሚችለውን ጫና እንዲረዱ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያናችን ከዚህ ቀደም በሀገራችን ፖለቲካ ላይ በበቂ ሁኔታ ባለመወከሏ ላለፉት በርካታ ዓመታት ግፍ ሲፈጸምባት እንደኖረች አክለዋል።
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 2600
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ከረማችሁ? ስሜ ወለተ ሥላሴ ይባላል የምኖረው አዲስ አበባ ሲሆን የምተዳደረው በንግድ ሥራ ነው። በሥራዬ ጸባይ ምክንያት ከብዙ ሰዎች ጋር እገናኛለሁ። በዚህ ግንኙነት ውስጥም በንግዱ ሥራ ከተዋወቅሁት ሰው ጋር የፍቅር ግኑኝነት ጀምሬ ነበር። ይህ ግንኙነት አድጎ ብዙ ጊዜያችንን የምናሳልፈው አንድ ላይ ሆነ፤ በዚህ ብቻም ሳንወሰን ወደ ግበረ ሥጋ ግንኙነት ገብተን በዚያ አጋጣሚ ድንግልናዬን ለማጣት በቃሁ።
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! ከዚያ የፍቅር ጓደኛዬ ጋር ብዙ መዝለቅ ባለመቻላችን ግማሽ መንገድ እንደተጓዝን ተለያየን። በዚህም ምክንያት እጅግ ተጎድቼ ስለነበር ለብዙ ጊዜ የወንድ ጓደኛ ሳልይዝ ቆይቻለሁ። ከጊዜ በኋላ ከሌላ የወንድ ጓደኛ ተዋወቄ ትዳር ለመመሥረት ተስማማን። ካለፈው ጊዜ ትምህርት ስለወሰድኩ ከአሁኑ ጓደኛዬ ጋር ያለኝ ግንኙነት የተቆጠበና ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። በዚህም በወንድ ጓደኛዬ ዘንድ ድንግል እንደሆንኩ ተቆጥሬያለሁ። ስለጋብቻችን ስናወራም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው የምንጋባው ይለኛል። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! ለወንድ ጓደኛዬ የቀደመ ሕይወቴን፣ ድንግል አለመሆኔን መናገር አልቻልኩም፤ ከዚህም በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው የምንጋባው ስላለኝ ኃጢአተኛ ሆኜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት እቆማለሁ የሚለው ያሰጋኛል። ድንግል ያለመሆኔን ሳስብ በሁለት መንገድ ፍርሃቴ ይጨምራል። እጅግ ተቸግሬአለሁና ምን ትመክሩኛላችሁ።
- Details
- Written by: በጋዜጣው ሪፖርተር
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1043
የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሥርዓተ ቀብር ረቡዕ መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።
ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (ዶር) ከአባታቸው ከባላምባራስ ተስፋ ተክሉ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ታህሣ ኃይሉ በግንቦት ወር ፲፱፻፴ ዓ.ም በትግራይ ክልል ብዛታ ወረዳ ፍልፍሎ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደረሰም በተወለዱበት አካባቢ ከአባታቸው ወንድም አባ ገብረ አረጋዊ ፊደል ንባብ የቃል ትምህርት ተምረዋል። በአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ ገዳም ከመምህር ገብረ እግዚአሔር መዝገበ ቅዳሴን፣ ከመሪጌታ ይትባረክ ጸዋትወ ዜማን አጠናቀው የተማሩ ሲሆን በጎጃም ጠቅላይ ግዛት እነማይ አውራጃ መንግሥቶ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከመምህር ደጉ ቅኔን ከነ አገባቡ አጠናቀዋል።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 2573
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ‹‹የቅባት እምነት አራማጅ ነን›› የሚሉ የተደራጁ ኃይሎች እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ከአገልግሎት እያገዱና እያሰናበቱ መሆኑን ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ያቀረቡ አባቶች ገለጡ፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ የነበሩትና አሁን ከአገልገሎት ከታገዱት አገልጋዮች መካከል አንዱ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን ባሕረ ጥበብ አያሌው ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖት፣ የመልካም አስተዳደርና የገንዘብ አጠቃቀም ችግር ያለበት መሆኑን ተቃውመው ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ቅዱስ ሲኖዶስ በመውሰዳቸው ምክንያት ከአገልግሎት እንደታገዱ አስረድተዋል፡፡
Read more: ‹‹የቅባት እምነት አራማጅ ነን›› የሚሉ ኃይሎች አገልጋዮችን ከአገልግሎት ማሰናበታቸው ተገለጠ
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1145
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የተቋቋመው ድጋፍ አሰባሳቢና አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመረዳት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገለጠ፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገው ይህ ዐቢይ ኮሚቴ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለውን እቅድ አውጥቶ የተፈናቃዮችን ችግር ከግምት ውስጥ ያስገባ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ከመግለጫው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዐቢይ ኮሚቴው ጸሓፊና የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መ/ር ዳንኤል ሰይፈሥላሴ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት እንደተናገሩት ዐቢይ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ አንሥቶ በዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ በጥናት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ርዳታ አሰባስቦ ለተጎጂ ወገኖች ከማድረስ ጎን ለጎን ተጎጂ ወገኖችን በቃለ እግዚአብሔር የማጽናት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
ለተጎጂ ወገኖች የሚሰጠው የማጽናኛ ትምህርት ቤተ ክርስቲያን ባሏት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አማካይነት በተለያዩ ቋንቋዎች እንደሆነ ያነሱት የዐቢይ ኮሚቴው ጸሓፊ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አማካይነትም የማጽናኛ ትምህርቱ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሥራ አምስት ሚሊዮን ብር፣ ከቅዱስ ፓትርያርኩ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ ብር፣ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከካናዳና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከአርባ ሺህ ዶላር በላይ የተሰበሰበ መሆኑን ገልጠው ጸሓፊው ተቋማቱ ላበረከቱት አስተዋፅኦም አመስግነዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም የዐቢይ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ይበቃል ሽፈራው በበኩላቸው ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽኑ በማንኛውም ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ በትግራይና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ የተለያዩ ድጋፎችን ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለተፈናቃዮች በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ሁሉተኛውን ዙር ድጋፍ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ከጊዜያዊ ድጋፍ በተጨማሪ ተፈናቃዮች ተጠልለው ያሉበትን ቦታ ምቹ ለማድረግም ከዚህ ቀደም በህንጣሎ፣ ዋጅራት፣ ራያ አዘቦና ጨርጨር አካባቢዎች የውኃና የሽንት ቤት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ በመጀመሪያ ዙር የአንድ ሽህ ሰባት መቶ ሠላሳ አምስት ኩንታል ስንዴ ዱቄት፣ የአንድ መቶ ሰባ ሦስት ኩንታል ምስር ክክ፣ የአሥራ ስምንት ኩንታል ጨው እንዲሁም የአምስት ሽህ ሰባት መቶ ሊትር ዘይት ርዳታ እንዳደረገ ኮሚሽነሩ ገልጠው ይህ ድጋፍ በመቀሌ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች እንደደረሰም አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ከአንድ መቶ ኀምሳ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በሁለቱም ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች እንደሚደርሱ ኮሚሽነሩ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1506
አዲሱ የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ስቱዲዮ አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ተመረቀ፡፡
በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሮ ወለጋና ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ታሪክ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ደረጃውን የጠበቀ ስቱዲዮ እንዳልተገነባ ጠቅሰው የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ስቱዲዮው የቀደሙ ጉባኤ ቤቶችን እንድናስታውሳቸው ተደርጎ መሠራቱ እንዳስገረማቸው የተናገሩት ብፁዕነታቸው ይህም ወንጌል ላይ የተመሠረተችውን የቀናች ሃይማኖት ለማስፋፋትና ለመስበክ አጋዥ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡
ጊዜውን የቀደሙ “ቴክኖሎጂዎችን” ሁሉ በመጠቀም ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ወቅቱ እንደሚጠይቅ ካሉ በኋላ “ስቱዲዮው የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት፣ ትውፊትና የምእመናንን ዘመናዊና ባሕላዊ የአኗኗር ዘይቤ ያንጸባረቀ ሆኖ መገንባቱ ደግሞ በተለየ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በቀላሉ ለማስረዳት ያግዘዋል” ብለዋል፡፡
“ከቴክኖሎጂ” ርቀት የተነሳ ምእመናን በየቤታቸው ሆነው ወንጌልን መስማት የሚችሉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ያሉት ብፁዕነታቸው “ለዚህ ደግሞ ደረጃው ከፍ ብሎ የተሠራ እስቱዲዮ መኖሩ ወንጌል ከምእመናን ቤት ድረስ ለማድረስ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ በበኩላቸው ባዩት ነገር ተደስተው ማኅበሩ የሠራው የቴሌቭዥን ስቱዲዮ ከዚህ በላይ የበለጠ መሥራት እንደሚቻል የተረዱበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የስቱዲዮው የተለያዩ ክፍሎች በጉባኤያት መሰየማቸው ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም በጉባኤያት እንደምታምንና ጉባኤው የክርስቶስ መሆኑን የምንረዳበት ነው ካሉ በኋላ “በዚህ ስቱዲዮ ውስጥ መልካም ዜና የሚሰማበትና የእግዚአብሔር ወልድ ወንጌል የሚሰበክበት ይሆናል” ብለዋል፡፡
እንደነዚህ ያሉ “በቴክኖሎጂ” የጎለበቱ ሥራዎች ሊሠሩና ሊጎለብቱ እንደሚገባ ያስረዱት ብፁዕነታቸው “ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ለማይችሉ ምእመናን መንፈሳዊ መርሐ ግብራትን ቤታቸው ድረስ እንዲከታተሉ ለማድረግ እንደነዚህ ዓይነት ደረጃቸውን የጠበቁ ስቱዲዮ መገንባታቸው የወንጌል ተደራሽነትን ያግዛል” ብለዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ሲሳይ ባሰሙት የመግቢያ ንግግር እንዳስታወቁት የተገነባው ስቱዲዮ የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት ለመሥጠት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስበከተ ወንጌልን በተገቢው መንገድ ለማስፋፋት ሚዲያ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው “የሚዲያ አጠቃቀማችን ለማዘመን የስቱዲዮ ግንባታ ወሳኝ ነው” ብለዋል፡፡
ስቱዲዮውን ለመገንባት ብዙ ውጣ ውረዶች እንደታለፉ ያስገነዘቡት ምክትል ሰብሳቢው ፈተናዎች ሁሉ ታልፈውና የተለያዩ አካላት እገዛ ተጨምሮበት ይህ ዘመናዊ ስቱዲዮ እውን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳንና የቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተናበው እንዲሠሩም ም/ሰብሳቢው ጠይቀዋል፡፡
በተለይም ምእመናን በፈተና በሚወድቁበት ጊዜ የቴሌቭዥን መርሐ ግብራት አስፈላጊ እንደሆነ ያነሱት ም/ሰብሳቢው የበለጠ ሃይማኖታዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ ብቁ የሆኑ የሰው ኃይል ማፍራት እንሚያስፈልግ ያስገነዘቡት ም/ሰብሳቢው ይህንንም ለማድረግ የመንፈሳዊ ጋዜጠኝነት ሙያን ሊያግዙ የሚችሉና ሥልጠናዎችን የሚሰጡ መንፈሳዊ ተቋማት ሊኖሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ለስቱዲዮው መጠናቀቅ ከአሳብ ጀምሮ ድጋፍና እገዛ ላደረጉ ብፁአን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናንና እንዲሁም አሠሪ ኮሚቴውን ላደረጉት አስተዋጽኦ ም/ሰብሳቢው ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1580
ኢትዮጵያ ሀገራችን ልዩ ልዩ መልክ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት ታላቅ ሀገር ስትሆን ከ፹ በላይ ቋንቋዎችም ይነገሩባታል። ከነገድ እና ከወገን የሚበዙት የሚኖሩባት ሁሉንም አቅፋ የያዘች እጀ ሰፊ ሀገር ናት። የረጅም ዘመን ታሪኳም የሚያሳየው ሕዝቦቿ ተፋቅረው እና ተከባብረው እንደ አንድ ልብ አሳቢ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው መኖራቸውን ነው። ለዚህም በተለያየ ጊዜ ሊወራት የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል መክታ ከሀገር ያስወጣችበት ታሪክ ቋሚ ምስክር ነው። ሕዝቧ እንደዛሬ የዘር ቋጠሮ ሳይፈታ ፤ በወንዝ እና በድንበር ሳይወሰን ከአራቱም አቅጣጫ በመትመም የጣሊያንን ሠራዊት ድል አድርጎ በዓለም ላይ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ ኃይል እና ብርታት ሆኖ ነበር።
የዚህ ሁሉ ማጥበቂያው ድር እና ማግ ሀገራችን ከጥንት ክርስትናን መቀበሏ እና የክርስቲያን ሀገር መሆኗ፣ ሕዝቡም ሆነ ነገሠታቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ሆነው መገኘታቸው ነው። ቃለ ወንጌልን በተግባር ሲፈጽሙ ለመኖራቸው ሌላው ምስክር ዘጠኙን ቅዱሳን መቀበላቸው፣ ከመካ መዲና የተሰደዱ ሙስሊሞችን ማስጠጋታቸው ነው። ሀገር በሰላም እና በአንድነት ተጠብቆ እንዲኖር፤ ሕዝቦቿ በፍቅር ተጋብተው እና ተጋምደው እንዲኖሩ ያደረጋቸው ብሎም ኢትዮጵያዊነት እንዲጠነክር በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የክርስትናው አስተምህሮ ነው።
ዛሬ ከዘመን ብዛት ይህ የመከባበር እና አብሮ የመኖር ውል ጠፍቶ፣ በጠንካራ ዓለት ላይ የተመሠረተው አንድነታችን ተሸርሽሮ ዥንጉርጉርነቱና መለያየቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሳይቀር አጥልቶ እናያለን። በክርስቶስ ደም አንድ የሆኑ ክርስቲያኖች በዘር ተለያይተው እና ጎራ ለይተው ሲፋለሙ ማየት ቀስ በቀስ እየተለመደ መጥቷል። ከራስ አልፎ ሌሎችን የተቀበለ ክርስቲያናዊ ሰብእናችን ጠፍቷል፤ ሁሉን አንድ አደርጎ የሚያየው ዓይነችን ተንሸዋሯል። ሁሉም በየቤቱ በክርስቶስ ስለዳነው የሰው ልጅ ሳይሆን ስለጎጥ እና ስለዘር ሲያወራ ይውላል። ጾታና ዕድሜ ሳይለይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከምእመን እስከ መነኲሴ በዘረኝነት አዙሪት ውስጥ ገብቶ ሲባዝን ይውላል። ግዴለም ወደሌሎች ማየት እና መጠቆም አያስፈልገንም ሁላችንም ከእነዚህ እንደ አንዱ ሆነናል፤ ግን እስከ መቼ?
ቤተ ክርስተያን ሄዶ የቅዱስ ወንጌልን ቃል ከመስማት ይልቅ ስለዘረኝነት መስማት የወንጌል ቃል ያህል እየተለመደ ነው። በእግዚአብሔር ስም ተሰብስቦ ሀገርን ስለማይጠቅም፣ ክርስትናን ስለማያንጽ ተራ ጥላቻ እና ወሬ መስማት ከክርስትናው ተርታ የሚያስወጣ ነው። እኔ ክርስቲያን ነኝ ከሚለው ይልቅ እኔ የዚህ ዘር ነኝ፣ እከሌ የዚህ ዘር ነው ብሎ ማውራት እጅግ የሚያሳፍር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚሸቃቅጡት . . . ›› ፪ኛ ቆሮ ፪፥፲፯ እንዳለው በቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ ወንጌልን ከፖለቲካ ጋር ቀላቅሎ መስበክም ሆነ መስማት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል። ለዘመናት የተገነባው ማንነታችን ተሸርሽሮ ክርስትናችንን እየፈተነው ይገኛልና አጥብቀን ልንቃወመው ይገባል።
ሰዎች በደልና ግፍ ሲደርስባቸው፣ ከኖሩበት፣ ሀብትና ንብረት ካፈሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ፣ በጅምላ ሲታረዱና ሲገደሉ እንደ ዓለማዊ ሰው ማውራት ከጀመርን ቆይተናል። በእግዚአብሔር አርአያ ስለተፈጠረው ሰው ሳይሆን የኔ ስለምንለው ዘር ስንብከነከን ፀሐይ ወጥታ ትጠልቃለች። ሆኖም ግን ማዘንና ማልቀስ ያለብን የእኔ ስለምንለው ሰው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ የሚገደን ልንሆን ይገባል።
የሰው ልጆች ሁሉ ከአንድ አዳም ነው የመጡት ብላ በምትሰብከው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያደግን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለሰው ልጅ ማዘንን በዘር መለካት ከጀመርን ሰነባበትን። ይህን ያህል ሰው ተሰደደ ወይም ሞተ የሚለው ሳይሆን የእንትን ብሔር ተገደለ ወይም ተሰደደ የሚለውን አግዝፈን መናገር የሚቀናን እኛው ክርስቲያኖች መሆናችን ያስገምታል። በእኛ ሐሳብ የእኛ ያልሆነ ብሔር ሲሞትና ሲሰደድ ዓይናችንን የምንጨፍን ጆሯችንን የምንደፍን በተቃራኒው የኔ ለምንለው ብሔር ጎራ ለይተን በየማኅበራዊ ሚዲያው ስንሳደብና ስንራገም የምንውል እኛው ነን እኛ የቤቱ ሰዎች። ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ›› ኤፌ ፭፥፲፰ የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ዘንግተነው አለዚያም ተራ ሆኖብን ዘረኝነትን ስናሳድድ ከክርስትና እየራቅን ነውና በጊዜ ልንመለስ ይገባል።
ቤተ ክርስቲያን በክርስትና ጉዞዋ ውስጥ ብዙ ታሪካዊ ሰቆቃዎችን አሳልፋለች፤ ለአብነትም የዘመነ ዮዲት ጉዲት፣ የዘመነ ግራኝ . . . በጥቂቱ ተጠቃሾች ናቸው። በእነዚህ ሰቆቃዎቿም የደረሰባትን መከራ በድል በማጠናቀቅ እዚህ ዘመን ላይ ደርሳለች። እኛ የዘመኑ ክርስቲያኖች ግን ከአባቶቻችን ጋር በምንም የማይገናኘውን ትንሹን ፈተና እንኳ ማለፍ አቅቶናልና ራሳችንን፣ እምነታችንን በደንብ ልንፈትሽ ይገባል። ሀገር ዛሬ ካለችበት እና ከገባችበት አዙሪት እንድትወጣ ሰላምን በመስበክ የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ አንድ የሆንን ክርስቲያኖች ተግተን ልንጸልይ ልንሠራ ይገባል። ለሦስት ሺህ ዘመን ወንጌል የተሰበከልን ክርስቲያኖች እንዲሁም ለዚያን ያህል ዘመን የተገነባ የእምነትና የአብሮነት ባህልን ያዳበርን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬ ከእምነታችን እና ከአስተምህሮአችን ፈቀቅ የሚያደርግ የዘረኝነት ተራራ ከፊታችን ተገትሯል። በእምነታችን ጸንተን እንዳንኖር ፤በመንፈሳዊነትም እንዳንመላለስ የሚያደርገንን በክርስትናችን መንገድ ላይ ያለውን እንቅፋት ልናስወግደው ይገባል። በተለይም ለቤተ ክርስቲያን ቅርብ ነን ለምንል የቤቱ ሰዎች ክርስትናችንን የፈተነውን ይህን ክፉ ዘመን ተሻግረን ምእመናንንና ቤተ ክርስቲያንን ለማሻገር ከእኛ ብዙ ይጠበቃል።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 999
ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመፋለምና የሕይዎት መሥዋትነትን በመክፈል በመሠረቷትና ሀገር አድርገው በቆሟት ሀገራቸው ውስጥ ባይተዋር ሆነው ከመቆየታቸው ባሻገር ሠርተው ለፍተው በሚኖሩባቸው አንዳንድ ሀገራችን አካባቢዎች በአክራሪ ሃይማኖተኞችና በስሑት ትርክት አቀንቃኞች አማካኝነት እየታደኑ መገደል ከጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመንን አስቆጥረዋል። ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ ያለምንም ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላሉ፤ ሀብት ንብረታቸን ይዘረፋል፤ ሆን ተብሎም ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ይገለላሉ፤ እንዲሁም ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለሥደትና ለርኀብ ይዳረጋሉ። በአክራሪ ሃይማኖተኞችና በስሑት ትርክት አቀንቃኞች አማካይነት የሚደርስባቸው ጥቃት መነሻው ደግሞ ከዚህ ቀደም በሀገራችን የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ‹‹በጠላትነትና በጨቋኝነት›› ፈርጆ መነሣቱ ነው። ይህ የፖለቲካ ኃይል ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን የትግል ማእከል አድርጎ ሲያጎሳቁላት፣ ሲከፋፍላት፣ ዶግማና ቀኖናዋንም በመጣስ ሊያጠፋት እልህ አስጨራሽ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።
በመላ ሀገራችን ያሉ የዚህ ፖለቲካ ድርጅት የግብር ልጆች አሁንም ድረስ ቤተ ክርስቲያንን መድፈራቸውን ምእመናንን ማሳደድና መግደላቸውን አላቆሙም። ‹‹የፖለቲካ ለውጥ›› መጥቷል ከተባለበት ጊዜ አንሥቶም በተለይ በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በየጊዜው በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላሉ። ኦርቶዶክሳውያኑ አብዛኛውን ጊዜ በአክራሪ እስላሞች አማካይነት ይገደሉ እንጂ ከጀርባ ሆነው ጥቃቱን የሚደግፉና የሚያስተባብሩ የክልሉ የፖለቲካ አመራሮች እንዳሉ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ ምንጮች ለመረዳት ችለናል። እነዚህ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት በሥልጣን ላይ የነበረው ፀረ ኦርቶዶክስ የፖለቲካ ድርጅት ያወረሳቸውን ኦርቶዶክስ ጠልነት ሐሳብ በተግባር ሲፈጽሙ ቆይተዋል። በመሆኑም ላለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በባሌ፣ በአርሲ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በሌሎች የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ያለ ጥፋታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ታርደው ተገድለዋል፣ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፤ ለረኀብና ለእርዛትም ተዳርገዋል።
ሰሞኑንም በዚሁ ክልል በሆሮ ጉድሮ ወለጋ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ ዴቢስ ቀበሌ ላይ ይንቀሳቀስ የነበረ “ታጣቂ ኃይል” በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ኦርቶዶክሳውን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተደብድበው፣ በስለትም ታርደው ተገድለዋል። ከአካባቢው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ጥቃቱን በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ላይ የፈጸመው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን ነው። ይህ “ታጣቂ ቡድን” በቤተ መቅደስ ውስጥ በጸሎት ላይ የነበሩ ካህናትና ምእመናንን ጨምሮ በየቤታቸው የነበሩ ንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን ጭምር በስለት አርዶ በመሣሪያ ደብድቦ እንደገደላቸው ታውቋል።
የሆሮ ጉድሮ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ጽዮን ቀሲስ ተፈራ ቢሻሙ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ‹‹በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን በፈጸመው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት ቢያንስ ሃያ ዘጠኝ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ተገድለዋል›› ብለዋል። ካህናትና መምህራንን ጨምሮ እየተመረጡ የተገደሉት በሙሉ ኦርቶዶክሳውያን ብቻ መሆናቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ “ከዚህ በፊት በአካባቢው የፀጥታ ሥጋት እንዳለብን ለወረዳውና ለዞን አመራሮች አሳውቀናል” ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹በአካባቢው ያሉት የመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› ዓይነት በመሆናቸው ለታጠቁ ኃይሎች ድጋፍ ከማድረግና ስንቅና ትጥቅ ከማቅረብ ውጭ የንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን ደኅንነት ለመጠበቅ ያደረጉት ጥረት የለም” ሲሉም አክለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የተወሰነ የፀጥታ ኃይል ገብቶ የማረጋጋት ሥራ እየሠራ እንደሆነ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ‹‹ጥቃት ያደረሰው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን ጥቃት ካደረሰበት አካባቢ ላይ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ጫካ ውስጥ መሽጎ ይገኛል›› ብለዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የመሸገው ይህ ታጣቂ ቡድን በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዳይኖርና ሕዝበ ክርስቲያኑ ሥጋት ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል፤ በቋሚነት ታጣቂ ኃይሉን ከአካባቢው ማጽዳት እስካልተቻለ ድረስ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት እንደማይቻል አክለው አስረድተዋል።
በሆሮ ጉድሮ ወለጋ ሀገረ ስብከት የአቢ ደንጎሮ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት መልአከ ገነት ቀሲስ ደመቀ ታደሰ በበኩላቸው በወረዳቸው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን ሃይማኖት ተኮር ጥቃት እንደፈጸመ ተናግረው በጥቃቱም በርካታ ካህናት፣ ዲያቆናት መምህራንና ምእመናን እንደተገደሉ አረጋግጠዋል። ታጣቂ ኃይሉ መጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጸሎት ላይ የነበሩ አገልጋዮች ካህናትንና ምእመናንን ከገደለ በኋላ በየመንደሩ እየዞረ የቀሩትን ኦርቶዶክሳውያን እንደገደለ ኃላፊው አስረድተው አስከሬናቸው የተገኘ ፲፱ ሰዎች ብቻ ተቀብረዋል›› ሲሉ ተናግረዋል። የሟቾች ቁጥር እስከአሁን ድረስ ፲፱ ይባል እንጂ ፳፪ እና ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል ኃላፊው ተናግረው ከተገደሉት በተጨማሪም በርካቶች ታፍነው እንደተወሰዱ አስረድተዋል። የምእመናን ሀብት ንብረት እንደተዘረፈና ቤታቸው እንደወደመም ገልጠዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ቅዳሜ ከቀኑ ሰባት ጀምሮ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውንና ታፍነው የተወሰዱባቸውን ሕፃናት ከነ ነፍሳቸው በአቅራቢያ በሚገኝ ወንዝ ላይ እንደጣሏቸው አስረድተዋል። በወቅቱ ግማሽ የሚሆነው የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ገቢያ በመሄዱ ቀሪዎቹ አቅም ኖሯቸው ታጣቂ ኃይሉን መመከት እንዳልቻሉ ያነሡት ኃላፊው የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ አስረድተዋል። አስክሬናቸው እስከአሁን ድረስ ያልተገኘ እንዳለም አክለው ተናግረዋል።
በወረዳው ሥር ፵፮ አጥቢያዎች የሚገኙ ሲሆን በአካባቢው የሚኖረው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መሆናቸው ታውቆ ጥቃቱ እንደተፈጸመ ያስረዱት ኃላፊው ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ የተረፉ ምእመናን ተሰብስበው ራሳቸውን ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም ‹‹የኦነግ ሸኔ›› ታጣቂ ኃይል ትጥቅ ከሕዝበ ክርስቲያኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለከፋ የጸጥታ ችግርና ለሕይወት መጥፋት እንደተዳረጉ ተናግረዋል። የአካባቢው የመንግሥት ታጣቂ ኃይልም ‹‹የኦነግ ሸኔ›› ታጣቂ ኃይል ደጋፊና መረጃ አቀባይ በመሆኑ ለእነርሱ ችግራቸውን ማስረዳትም ሆነ እገዛ መጠየቅ የማይታሰብ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።
አንዳንዴ በአካባቢው ችግር እንዳለ መረጃ ደርሷቸው የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች በቦታው ተገኝተው ማጣራት ሲፈልጉ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ችግር እንደሌለ ነግረዋቸው እንደሸኛቸው ያረጋገጡት ኃላፊው “ይህም በመሆኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ ለከፋ የፀጥታ ችግር ከመጋለጡ ባሻገር ሕይወታቸውን ሙሉ በሥጋት እንዲያሳልፉ አድርገዋቸዋል” ብለዋል። ባለሥልጣናቱም ለታጣቂ ኃይሉ ሽፋንና የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት ከማድረግ ውጭ ለንጹሓን የአካባቢው ኗሪ ምንም ዓይነት የሕግ ከለላ አያደርጉላቸውም ሲሉም ተናግረዋል። ታጣቂ ቡድኑ ካህናትንና ምእመናንን እየመረጠ የገደለ ሲሆን “ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ካቃጠልን ድጋሜ ሊሠሩ ይችላሉ፣ ካህናትና መምህራንን ቀድመን ካጠቃን ግን የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ያበቃል›› በሚል እሳቤ ተነሳስቶ ጥቃት ሲፈጽም እንደነበረም ኃላፊው ተናግረዋል። ጉዳዩን ከወረዳ እስከ ዞን ላሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና በሥራ አስኪያጁ በኩል እንዳስረዱ ኃላፊው አክለው ገልጠዋል።
የአቢ ደንጎሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ብሪሳ ኃይሌ ጉዳዩን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በወረዳቸው የሚንቀሳቀሰው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረው “በአካባቢው በቂ ጥበቃ አሰማርተን ንጹሓንን ስንጠብቅ የነበረ ቢሆንም ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ግን ጥቃቱ ተፈጽሟል” ብለዋል። ዕለቱ የገበያ ቀን በመሆኑም በጥበቃ ላይ የነበሩ አንዳንድ የአካባቢው የፀጥታ ኃይላት ወደሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ የተፈጸመ ጥቃት እንደሆነም ኃላፊው አስረድተው። “ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ ከወረዳቸው ርቀው ጫካ አካባቢ በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንደሆነ የገለጡት አስተዳዳሪው ይህም ከርቀቱ አንጻር ደኅንነታቸውን የመጠበቁን ሥራ አክብዶብናል” ብለዋል። በወቅቱ ጥቃቱን ያደረሰው ታጣቂ ቡድንም የጥቃቱ ሰለባዎች መረጃ እንዳያወጡ በሚል ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን እየነጠቀ እንደገደላቸው አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ አንድ ቦታ ላይ ሆኖ መዋጋት የማይችልና አሳቻ ሰዓት ጠብቆ ሕዝብን ጨፍጭፎ የሚሠወር ኃይል ነው ያሉት አስተዳዳሪው “ይህም ንጹሓንን ከጥቃት ለመከላከል ፈታኝ አድርጎታል” ብለዋል። ዘላቂ ሰላም በአካባቢው ማስፈን የሚቻለው የአካባቢውን ኅብረተሰብ በዘላቂነት ማደራጀት እንደሆነ አስተዳዳሪው ጠቅሰው “የአካባቢው ኅብረተሰብ ታጥቆ ራሱን እንዲከላከል የማድረግ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፤ ለወደፊቱም አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ አስረድተዋል። “በአሁኑ ወቅት በቂ የሚባል የፀጥታ ኃይል በአካባቢው ላይ በመሠማራቱ አካባቢው የተረጋጋ ሆኗል” ብለዋል”። ጥቃት የተፈጸመባቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን አስተዳዳሪው አስረድተው የሟቾች ቁጥርም ሃያ ሁለት ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል።
ጥቃቱን ሸሽተው ከተሰደዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገን ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበትን ነገር እያመቻቸን እንገኛለን ያሉት አስተዳደሪው የተሰደዱት ወደ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ ውይይቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በቀጣይም ዘላቂ ሰላም በሚመጣበት ዙሪያ አቅጣጫ በጋራ እናስቀምጣለን ሲሉ ተናግረዋል። በታጣቂዎች ታፈነው ከተወሰዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሦስት ያህሉን ማስመለስ እንደቻሉም አስተዳዳሪው ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል።
በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ቀርበው በስልክ አስተያየታቸውን የሰጡት የአካባቢው ኗሪ ታጣቂ ቡድኑ ጥቃቱን የጸፈመው የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ቅዳሜ ዕለት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ እንደሆነ ተናግረው ታጣቂ ቡድን በአካባቢው በሚገኘው መንደር እየዞረ ያገኘውን ሰው ወደ ኋላ በገመድ እያሰረ እንዳረዳቸው አስረድተዋል። በጥቃቱ አረጋውያን ጨምሮ ሕፃናት የታረዱ ሲሆን በተለይ ፲፱ የሚሆኑትን በኋላቸው አስሮ አርቆ በመውሰድ አርዶ እንደገደላቸው ያዩ መሆኑን ለቴለቭዥን ጣቢያው በስልክ ተናግረል።
“ኦነግ ሸኔ” የተባለው ታጣቂ ቡድን በተለየ ሁኔታ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን እያጠቃ መሆኑን ያስረዱት ግለሰቡ የወረዳው የፀጥታ ኃይልም ለታጠቂ ቡድኑ እገዛ እንደሚያደርግለት ተናግረዋል። የአካባቢው ኅብረተሰብ በዚህ ወቅት ወደ መኖሪያ ቀዬው እንዳልተመለሰና ምግብ ለመብላት ብቻ ወደ አካባቢያቸው ዘልቀው ከሰዓት በኋላ ደግሞ ወደ ጫካ ተመልሰው እንደሚሄዱ አያይዘው አስረድተዋል። እስካሁን ድረስም ወደ አካባቢያቸው መመለስ ባለመቻላቸው ሀብት ንብረታቸው በታጣቂ ቡድኑና በተባባሪዎቹ እየተዘረፈባቸው እንደሆነ ግለሰቡ አስረድተዋል።
- Details
- Written by: መጽሐፈ ሲራክ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1308
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የብዙ ሊቃውንት አባቶች መፍለቂያ ምንጭ ናት። ሰማዕታትን፣ ደናግላኑን ሐዋርያትን፣ ጳጳሳትን፣ መነኮሳትን፣ ያፈራች የቅዱሳን እናት ናት። ብዙዎቹ በተሰጣቸው ዘመን ወደዚህ ዓለም መጥተው በቅድስና በንጽሕና ኖረው፣ አስተምረው፣ጸልየው፣ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለቤተ ክርስቲያን ክብር ቆመው እና አገልግለው በስተመጨረሻም ዘመን ገቷቸው አንቀላፍተዋል።
በዘመናቸው ተነስተው እንደ ተወርዋሪ ኮከብ አብርተው፣ መልካም ገድልን በመጋደል እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሩጫቸውን ጨርሰው በገነት ወደ ቅዱሳን ማኅበር ከተቀላቀሉት መሀከል ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ አንዱ ናቸው። እኛም የብፁዕነታቸውን የሕይወት ታሪክ፣ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን፣ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውን ባጠቃላይ እስካረፉበት መጋቢት ፲፮ ቀን ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ያለውን ዜና ሕይወታቸውን በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል መልካም ንባብ፦
ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በቀድሞ ስማቸው አባ ጸጋዬ ቢሆነኝ በዚያን ጊዜ አጠራር በደቡብ ጎንደር አስተዳደር በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ ልዩ ስሙ ቆማ ፋሲለደስ ተብሎ በሚታወቀው ታላቅ ገዳም ከአባታቸው ከቀኝ ጌታ ቢሆነኝ ዋሴ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ውዴ መሸሻ በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ተወለዱ።
ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በመካነ ልደታቸው በቆማ ፋሲለደስ ፊደል፤ ዳዊትና ጸዋትወ ዜማ ከታወቁት ከታላቁ የቆሜ ድጓ ምሥክር ከነበሩት ከመምህር ሐዲስ ተምረዋል። በጥር ፲፱፻፴፭ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም ከግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ ማዕረገ ዲቁናን ተቀበሉ።
ብፁዕነታቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ፈለግ በመከተል መንፈሳዊ ዕውቀታቸውን ለማስፋፋት በነበራቸው ጽኑዕ ፍላጎት ከትውልድ ቦታቸው ወጥተው በልዩ ልዩ ክፍላተ ሀገራት በመዘዋወር ከአያሌ ኢትዮጵያውያን መምህራን የቤተ ክርስቲያችንን ከፍተኛ ትምህርት በመቅሰም መንፈሳዊ ዕውቀትን ገብይተዋል።
በዚሁ መሠረት ከደቡብ ጎንደር ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሄደው በሞጣ አውራጃ ድቦ ኪዳነ ምሕረት ቅኔ እስከነአገባቡ ተምረዋል። ወደ ደቡብ ጎንደር በመመለስም በጋይንት አውራጃ በስማዳ ወረዳ ደብረ ዕንቍ ከመምህር ጌጡ ተሰማ ተጨማሪ የቅኔ ትምህርታቸውን አስፋፍተዋል።
ቀጥሎም ወደ ደቡብ ወሎ በመሄድ በአማራ ሳይንት ወረዳ፤ በሮ ሚካኤል ከነበሩት ከአለቃ ከበደ የቅኔ ትምህርትን ከነአገባቡ በመማር አጠናቀው በመምህርነት ተመርቀዋል። በመጻሕፍት ትርጓሜ ረገድም በዚያው በቦረና ሣይንት አውራጃ በመካነ ሰላም ከአለቃ ታመነ አግደው ትርጓሜ ነገሥትን፣ በደሴ አውራጃ በደሴ መድኃኔ ዓለም ከአባ ገብረ ማርያም ገብረ ሐና ዳዊትን፣ የውዳሴና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜን ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ሐጎስ የትምህርተ ኅቡአት ፣ የኪዳንና የፍትሐ ነገሥት ትርጓሜን ተምረዋል። ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በደቡብ ወሎ በትምህርት ላይ ነበሩበት ጊዜም በ፲፱፻፵ ዓ.ም በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ ሕገ ምንኩስናን ተቀብለዋል። መስከረም ፳፩ ቀን ፲፱፻፵፬ ዓ.ም በግሼን ማርያም ማዕረገ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል የጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።
ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በታዕካ ነገሥት በዓታ መታሰቢያ ቤት የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርታቸውን ቀጥለው ሐዲሳትን ከመምህር ገብረ ሕይወትና ከመምህር ሥምረተ አብ ቀጸላ፣ ብሉያትን ከመምህር ጌራ፣ አቡሻህርን ደግሞ ከመምህር ገብረ ሕይወትና ከመምህር ኪዳነ ማርያም ተምረው ተመርቀዋል።
ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ከፍ ብሎ በዝርዝር እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ባህል እውነተኛ ምንጮች ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መምህራን ነገረ መለኮትን አጥንተው ካስመሰከሩ በኋላ በመምህርነት ተመርቀዋል።
ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በተለያዩ ሊቃውንት የቤተ ክርስተያንን ዕውቀት ከቀሰሙ በኋላ በ፲፱፻፶፮ ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ በሐዲሳት ትርጓሜ መምህርነት ተመድበው እስከ ፲፱፻፸፩ ዓ.ም ድረስ ለዐሥራ አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ በማስተማር ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የካቴድራሉ ቄሰ ገበዝ በመሆን መንፈሳዊ ፍቅርን በተሞላ ሰብእና ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል።
በተጨማሪም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ተመድበው ብዙ ወጣቶችን አፍርተዋል። ቀደም ሲል ማኅበረ እስጢፋኖስ ሲባል የነበረው የካህናት ማኅበር እንዲሁም ማኅበረ ሥላሴ እየተባለ ይጠራ በነበረው የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር ዘወትር ቅዳሜና እሑድ በመገኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ነገረ መለኮትን በማስተማር ከፍ ያለ አገልግሎት ሰጥተዋል። በተለይም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በሚያደርጉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሁሉ በመሳተፍ በማኅበሩ ውስጥ እየተመረጡና እያስተማሩ ለማኅበሩ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አበርክተዋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በነበራት ሰፊ እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያንዋ ለምትጠብቀው አገልግሎት አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲመረጡ በተወሰነው መሠረት ጥር ፭ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ.ም ከተመረጡት ፲፫ ኤጲስ ቆጶሳት መካከል ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ አንዱ ሆነው በመመረጥ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ማዕረገ ጵጵስናን ተቀብለዋል።
ማዕረገ ጵጵስናን እንደተቀበሉ በቀድሞው የኤሊባቦር ክፍለ ሀገር ኤጲስ ቆጶስ ሆነው በመሾም በሀገረ ስብከቱ የተለያዩ መንፈሳዊ ተግባራትን አከናውነዋል። ከነዚህ መንፈሳዊ ተግባራት መካከልም ፦ በዚሁ በተመደቡበት ኤሊባቦር ልዩ ስሙ ዳበና በተባለው ሥፍራ ፻፳ ኪሎ ሜትር መንገድ በእግራቸው በመጓዝ እና በማስተማር ለካህናት ማሰልጠኛ መጠናከር አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ብፁዕነታቸው በዚሁ ሀገረ ስብከት በነበራቸው መንፈሳዊ አገልግሎት ሰበካ ጉባኤ አደራጅተዋል፣ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን አቋቁመዋል፣ የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት በማቋቋም እናት እና አባት ለሌላቸው ልጆች ምግብ፣ መጠለያ እና ትምህርት እንዲያገኙ አድርገዋል። የመቱ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ለሀገረ ስብከቱ በሚመጥን መልኩ በካቴድራል ደረጃ ከፍ አድርገው አሠርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሰንበት ትምህርት ቤትን በማቋቋምና በማደራጀት ብዙ ወጣቶች የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሆነው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ አድርገዋል።
ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በጥር ወር ፲፱፻፸፮ ዓ.ም የኤርትራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ተዛውረው ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። በተለይም ለቤተ ክርስቲያን እድገትና የካህናትን ኑሮ ለማሻሻል በወጣው ቃለ አዋዲ መሠረት ለምእመናን ጥቅሙን በማስረዳትና የነበረውን ችግር በማስወገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበካ ጉባኤ አስጀምረዋል።
ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከቱ የካህናት በጀት እንዲከፈት በማድረግ በየወረዳው ሊቃነ ካህናትን መድበዋል። በተጨማሪም ለካህናትና ለመምህራን ለቢሮ ሠራተኞች ደሞዝ እንዲሻሻል በከፍተኛ ጥረት አዲስ በጀት አስከፍተዋል። የአስመራ አብያተ ክርስቲያናትን በማስተባበርም በሰበካ ጉባኤ ገቢ ላይ ገንዘብ እንዲዋጣና ከሀገረ ስብከቱም ወጭ በማድረግ ለሠልጣኝ ካህናት ለትራንስፖርትና ለመምህራን አበል በመክፈል ራስ አገዝ የካህናት ማሠልጠኛ ከፍተው ካህናቱ በየሦስት ወሩ እንዲሠለጥኑ አድርገዋል። በሀገረ ስብከቱ ብዙ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፣ብዙ ዘመን የቆዩትም በአዲስ መልኩ እንዲሠሩ አድርገዋል።
ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት እስከተዛወሩበት የጥቅምት ወር ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኤርትራ ክፍለ ሀገር በድርቅና በሰላም መታጣት ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች የምታከናውነውን የርዳታ ሥራ ሲመሩና ሲያስተባብሩ ቆይተዋል።
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ተመድበው በሀገረ ስብከቱ ሥራ በጀመሩ በአራት ወራት ውስጥ ብዙ የትሩፋት ሥራዎችን አከናውነዋል። በጎንደር ከተማ አዘዞ ሚካኤል የሚገኘውን የካህናት ማሠልጠኛ በቦታው ድረስ እየተገኙ በማስተማር ከማበረታታቸውም በላይ ማሠልጠኛውን በገንዘብ ይደግፉ ነበር።
የጉባኤ ቤቶች ተጠናክረው እንዲስፋፉ በነበራቸው ጽኑዕ ዓላማ መሠረት በጎንደር ከተማ ውስጥ ለተለያዩ ጉባኤ ቤቶች ከግል ገንዘባቸው ልግስና አድርገዋል። ለድሆች፣ ለጦም አዳሪዎች ከግል ገንዘባቸው ችሮታ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በየአውራጃው እየተዘዋወሩ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠገኑ ሐሳብና መመሪያ ሰጥተዋል። በተለይም የቆማ ፋሲለደስ ገዳም እንዲታደስና ቆርቆሮ እንዲለብስ አስፈላጊውን ገንዘብና ቁሳቁስ እንዲያገኝ ከፍተኛ የማስተባበር ተግባር ፈጽመዋል።
በጎንደር ደብረ ታቦርና በወረታ ያሉትን የሕፃናት ማሳደጊያዎች ተዘዋውረው በመጎብኘት ለሕፃናት ትምህርትና ምክር በመስጠት የሕፃናት ማሳደጊያዎቹም የበለጠ እንዲስፋፉ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በደብረ ታቦር የሚገኙትን የችግኝ ጣቢያዎች ተዘዋውረው በመጎብኘት ብዙ የድጋፍ ሥራን ሠርተዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝናብ እጥረት ችግር የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት በሌቦ አውራጃ በአዲስ ዘመን እና በእብናት ያቋቋመቻቸውን ሦስት የርዳታ ጣቢያዎች በመጎብኘት እና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴውን በመከታተል ለተጎጂ ወገኖች ርዳታ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል።
ብፁዕነታቸው በሕይወተ ሥጋ በነበሩባቸው ዓመታት ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነት ሲያገለግሉ የቆዩ ፤ለብዙዎች አርአያ የሆኑ መንፈሳዊ አባት ነበሩ። ሀብተ ክህነት፣ሀብተ ትሕትና፣ ሀብተ ጾም፣ ሀብተ ጸሎት፣ ሀብተ ፍቅር እንዳላቸው በብዙዎች ዘንድ የሚነገርላቸው ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ባደረባቸው ሕመመም ምክንያት በተወለዱ በ፷፩ ዓመታቸው መጋቢት ፲፮ ቀን ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሥጋ አርፈዋል። ብፁዕነታቸው ከዚህ ዓለም በሥጋ ቢለዩም በመንፈስ ሕያው ሆነው ይኖራሉ።
በረከታቸው ይደርብን