ሐመረ ጽድቅ
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ሐመር
    • የማኅበሩ መልእክት
    • ትምህርተ ሃይማኖት
    • እናስተዋውቃችሁ
    • የጥያቄዎቻችሁ መልስ
    • ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት
    • ኪነ ጥበብ
    • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን
    • ከዓለም ማእዘናት
    • ዐውደ ስብከት
    • ዐቢይ ጉዳይ
  • ስምዓ ጽድቅ
    • ርእሰ አንቀጽ
    • አጫጭር ዜናዎች
    • ሪፖርታዥ
    • ቤተ አብርሃም
    • ፍሬ ከናፍር
    • የሕፃናት ዓምድ
    • ትዝብት
    • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ
  • ሙሉ ሕትመቶች
    • ሐመር በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • ሐመር በ ዓ.ም.
      • 1985
      • 1986
      • 1987
      • 1988
      • 1989
      • 1990
      • 1991
      • 1992
      • 1993
      • 1994
      • 1995
      • 1996
      • 1997
      • 1998
      • 1999
      • 2000
      • 2001
      • 2002
      • 2003
      • 2004
    • ሐመር በዓመት
      • 1ኛ ዓመት
      • 2ኛ ዓመት
      • 3ኛ ዓመት
      • 4ኛ ዓመት
      • 5ኛ ዓመት
      • 6ኛ ዓመት
      • 7ኛ ዓመት
      • 8ኛ ዓመት
      • 9ኛ ዓመት
      • 10ኛ ዓመት
      • 11ኛ ዓመት
      • 12ኛ ዓመት
      • 13ኛ ዓመት
      • 14ኛ ዓመት
      • 15ኛ ዓመት
      • 16ኛ ዓመት
      • 17ኛ ዓመት
      • 18ኛ ዓመት
      • 19ኛ ዓመት
      • 20ኛ ዓመት
    • ስምዓ ጽድቅ በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • አዳዲስ ሙሉ ሕትመቶች
      • አዲስ ሐመር
      • አዲስ ስምዐ ጽድቅ
  • ያግኙን

ስምዓ ጽድቅ

ንሰሐ አባቴን የደበቅሁት ምሥጢር፦ ወደ ኋላ መመለስ ፈራሁ ክፍል ሁለት

Details
Written by: በዝግጅት ክፍሉ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 10 March 2021
Hits: 1277
  • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ

የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

፫. ቅዱስ ጴጥሮስ

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በኃጢአቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ግን ንስሓ በመግባቱ ከታረቁት መካከል በዋናነት ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ተጠቃሽ ነው። ይህ ሐዋርያ ሌሎች እንኳ ቢክዱህ እኔ አልክድህም ሲል የነበረ ቢሆንም ከሌሎቹ ተለይቶ የካደ እርሱ ነበር። ሆኖም ግን በፍጥነት ወደራሱ ተመለሰ። የተነገረው ትንቢት ሳይውል ሳያድር እንደተፈጸመበት አወቀ። ፈጥኖ አለቀሰ፤ ንስሓ ገባ፤ እግዚአብሔርም ይቅር አለው። የጥሉ ግድግዳ በንስሓው አማካኝነት በእግዚአብሔር ቸርነት ተናደ። በዚህም ታማኝ አድርጎ የበጎቹ ጠባቂ አደረገው። (ዮሐ.፳፩፥፲፭-፲፰) ስለዚህ ምንም እንኳ ኃጢአተኛው የሠራው ክፉ ሥራና የሚገባው ንስሓ ማለትም በንስሓ የሚያደርገው ጸሎት፣ ልመና፣ ልቅሶ፣ ስግደት፣ ምጽዋት ወዘተ ለበደለው በደል በትክክል ካሳ ከመሆን አንጻር ባይመጣጠንም እግዚአብሔር ግን በባሕርዩ መሐሪ ነውና ንስሓውን ምክንያት አድርጎ ይቅር አለው ታረቀውም።

፬. ማርያም እንተ ዕፍረት 

ማርያም እንተ ዕፍረት ዕድሜ ዘመኗን በኃጢአት ያሳለፈች ሴት ነበረች። ይሁን እንጂ በኃጢአት መኖር ከእግዚአብሔር መለየት አግባብ እንዳልሆነ በተረዳች ጊዜ ፈጥና ወደ ንስሓ ተመለሰች። በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናገኘውም እጅግ ዋጋው የከበረ ሽቶ አቀረበች ጌታችን መድኃኒታችንንም በእንባዋ አጠበችው። የንስሓ ዋጋ የሆነውንም “እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት ቦታ ይህች ሴት ያደረገችው ለእርሷ መታሰቢያ ሆኖ ይነገራል።” በማለት  የማይጠፋ ስም ሰጣት። (ማቴ.፳፮፥፮-፲፫)፤ (ማር.፲፬፥፫-፱)፤ (ዮሐ. ፲፪፥፩-፰)

ከማርያም ዕንተ እፍረት የምንማራቸው በርካታ ቁም ነገሮች አሉን እነሱም ለበጎ ነገር መሽቀዳደምን ይልቁንም ለንስሓ ጊዜ መስጠት እንደሌለብን እንረዳለን። ትርጓሜ ወንጌል እንደሚነግረን ማርያም እንተ ዕፍረት ይህ ቀረሽ የማትባል መልከ መልካም ነበረች። ከዕለታት አንድ ቀን መላ ሰውነቷን በሚያሳይ በቁም መስተዋት ራሷን እየተመለከተች ግን ያን የሚመስል ውበት እንደሚያልፍ እንደሚረግፍ ተገነዘበች። ለዚህ መድኃኒቱ ደግሞ ንስሓ መግባት እንደ ሆነ ተረዳችና ዘመኗን ሙሉ በዝሙት የአጠራቀመችውን ገንዘብ በመያዝ ሥርየትን ለሚያድለው፣ ኃጢአትህ/ሽ ተሥርዮልሃል/ሻል ለሚለው ሊቀ ካህናት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ሽቱ ገዝታ ወደ እርሱ ሄደችና ማድረግ የሚገባትን አደረገች።

ማርያም እንተ ዕፍረት ልቧ በተመለሰ ጊዜ ሳትውል ሳታድር ፈጥና ነው ንስሓን ወደ ሚቀበለው ሊቀ ካህናት የሄደችው። ይህ ብቻ አይደለም በመንገድ ላይም ሆነ ከደረሰች በኋላ በርካታ መሰናክሎች ገጥመዋታል። ከነዚህም መካከል ጥንት ዝሙት ያሠራት የነበረው ሰይጣን ቀድሞ በግብር ከሚያውቋት ወንድ ባንዱ ተመስሎ ከመንገድ ጠብቆ በርካታ የማሰናከያ ቃላትን እየጠቀሰ ሊያሰናክላት ሞክሯል። እሷ ግን አንድ ጊዜ ስለወሰነች እርሱ በሚያመጣው መሰናክል ሳትሸነፍ ለሚያነሣቸው ጥያቄዎች ሁሉ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድል ነሥተዋለች። ስለዚህ እኛም ወደ መልካም ነገር ስንሄድ በየመንገዱ እየጠበቀ ለዚያውም በምናውቀውና በምንወደው አካል እያደረ እንዳያሰናክለን ትጥቃችንን ልናጠብቅ ይገባናል። 

ሌላው ከደቀ መዛሙርቱ የመጣው ፈተና ነበር። አዛኝ ለድሆች በጎ አሳቢ በመምሰል ይህ ተሸጦ ለድሆች በተሰጠ በተገባ ነበር በማለት ያደረገችውን ሥራ እንደጥፋት ቆጥረውት ነበር። ክርስቶስ ግን መልካም አደረገች ለምን ታሰናክሏታላችሁ በማለት ሥራዋን አደነቀላት። እንዲያውም ይህ የእሷ ሥራ በአራቱም ወንጌላውያን ሲነገር እንደሚኖር በመግለጽ አስረዳቸው። ዛሬም እኛ ለንስሓ መፋጠን እንጂ መዘግየት እንደሌለብን፣ እኛ ለንስሓ በተፋጠን ቍጥር እግዚአብሔር አምላካችን ንስሓችንን በቶሎ እንደሚቀበለንና የሚመጡ መሰናክሎችን ሁሉ የምናልፍበትን ኃይል እንደሚሰጠን ያስረዳናል።

ምሕረትን ለሚያድለው፣ ኃጢአትህ/ሽ ተሠርዮልሃል/ሻል ለሚለው ሊቀ ካህናት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ሽቱ ገዝታ ወደ እሱ ሄደችና ማድረግ የሚገባትን አደረገች።

ውድ እኅታችን ወለተ ገብርኤል ዛሬ ላይ ሁነሽ ይህን ጉዳይ መደበቅሽ የኅሊና ዕረፍት እንደነሣሽ የተደረገበት ምክንያት በዕድሜ የመብሰልሽ ጉዳይ ነው። ሰው በዕድሜ እየበሰለ በሄደ ቁጥር ትላንት ይጓዝበት የነበረው የጨለማ መንገድ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ይሠራቸው የነበሩ ስሕተቶች በጉልህ እየታዩት ራሱን እንዲወቅስ፣ መሳሳቱንም እንዲያይ፣ እግዚአብሔር ኅሊናን ያህል ዳኛ መስጠቱ በዚህ ይታወቃል። የኅሊና ዳኝነት ከባድ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ “በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ፤ ከሥራቸው የተነሣ ይታወቃል፤ ሕሊናቸው ይመሰክርባቸዋል፤ ይፈርድባቸዋልም” (ሮሜ ፪፣፲፭) በማለት እንደተናገረው ኅሊና በራሱ ስለሚጠይቅ ተፈጥሯዊ ጉዳይ መሆኑንም ልብ ማለት ያስፈልጋል። 

አንቺም የኅሊና ዳኝነቱ ደርሶሽ መፍትሔ ፍለጋ ጥያቄሽን አቅርበሽልናል።  ወለተ ገብርኤል በቅድሚያ መረዳት የሚገባሽ ዝሙትን መፈጸም ከዐሥርቱ ትዕዛዛት አንዱን መሻር እንደሆነ መገንዘብ ይገባሻል። እግዚአብሔር አምላክ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕግን ሰጠው። በተሰጠው ሕግ ለወቅቱ እስራኤል ዘሥጋ (ያዕቆባውያን) ይተዳደሩበት ዘንድ ሲሆን ለፍጻሜው ደግሞ ለእስራኤል ዘነፍስ (ለክርስቲያኖች) የተሰጠ ሕግ ነው። ከዐሥርቱ ሕግጋት አንዱም ‹‹አታመንዝር›› የሚል ነው (ዘፀ. ፳፥፲፬።) አንቺ ግን በወጣትነትሽ ወቅት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን ሕግ ተላልፈሽ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ተራክቦ መፈጸምሽን ነግረሽናል። 

ወለተ ገብርኤል ዝሙት ታላቅ ኃጢአት መሆኑን በሰብአ ትካት በኖኅ ዘመን ሰዎች ላይ ያስከተለውን መዓት ምን እንደሆነ ታላቁ መጽሐፍ ይመሰክራል። 

በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከዝሙት ይርቁ ዘንድ ‹‹ሥጋ ግን ለእግዚአብሔር ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም ጌታም ለሥጋ ነው። ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆኑ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር እንደሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሏልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው  የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋል ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።›› በማለት አስተምሯቸዋል። ፩ቆሮ.፮፥፳—፳፫። 

ክርስቲያን በዋጋ የተገዛ መሆኑን ሲዘነጋ ለኃጢአት ይዳረጋል። ክርስቲያኖችን ጌታችን በወርቅ ደሙ እንደዋጀን ሐዋርያው ሲገልጽ “በዋጋ ተገዝታችኋል” አለ። ከዚህም በተጓዳኝ ዝሙትን ስንፈጽም በእኛ ያደረውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘን ስለሆነ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በሥጋው እግዚአብርን ማክበር ደግሞ ካልቻለና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በኃጢአት ከወደቀም ፈጥኖ ንስሓ መግባት ይጠበቅበታል። 

ወለተ ገብርኤል እንደሚታወቀው ኃጢአት የሥጋም የነፍስም በሽታ ነው። ለዚህ በሽታ ደግሞ እግዚአብሔር የሰጠን መድኃኒት ንስሓ ነው። የንስሓ ሁሉ መጀመሪያ ደግሞ የኅሊና ወቀሳ ነው። ይህም ማለት ኃጢአተኝነትን ማመንና ኃጢአትን ማውገዝና መጥላት ነው። ይህም ተነሳሒው በኅሊናው በአንቺ እንደሆነው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር መናዘዝ ነው። ‹‹ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ በደሌንም አልሸፈንሁም ለእግዚአብሔር መተላለፌን እናገራለሁ›› (መዝ. ፴፩፥፭ ) እንዲል። 

ይህ ዓይነቱ የኅሊና ጸፀት ብቻ በራሱ በቂ አለመሆኑን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለምጽ በሽታ የተያዘውን ሰው ከለምጹ ከፈወሰው በኋላ ‹‹ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ›› (ማቴ.፰፥፬) ብሎታል።  አንድ ኃጢአተኛ ራሱን ለካህን ማሳየት ለምን ያስፈልጋል? የሚል ሰው ካለም መልሱ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ስለሆነ ነው። ‹‹ካህኑ ሁሉን የሚችል የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና  ከንፈሮቹ ዕውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፤ ሕጉንም በልቡ ይመረምር ዘንድ ሚል.፪፥፯ ተብሏልና ነው። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዲስ ኪዳን ለወቅቱ ለቅዱሳን ሐዋርያት ለፍጻሜው በእርሱ እግር ተተክተው ለሚያገለግሉ ሥልጣነ ክህነት ላላቸው ካህናት የሰጠው ሥልጣን እንዲህ የሚል ነው። ‹‹እውነት እላችኋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።›› (ማቴ.፲፰፥፲፰)

ይህ ሥልጣን በዘመናት፣ ኃያላን የማይሽሩት አምላካዊ ጸጋ ነው። እኅታችን ወለተ ገብርኤል እስቲ አንቺ አንድ ጥያቄ መልሽልን እንጠይቅሽ። አያድርገው እንጂ አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር በሥጋሽ ታመሽ ትላንት የጤና ባለሙያ ጋር ሄደሽ ሕመምሽን ተናግረሽ መድኃኒት ታዝዞልሽ ነገር ግን የታዘዘልሽን መድኃኒት በአግባቡ ባለመውሰድሽ ሕመሙ ቢጸናብሽ ተመልሰሽ ጤና ባለሙያው ዘንድ መሄድሽ ይቀራል? አይቀርም። ምክንያቱም ፈውስ ስለምትፈልጊ ተመልሰሽ ሄደሽ ተናግረሽ የሚታዘዝልሽን መድኃኒት ወስደሽ እንደምትጠቀሚበት ሁሉ ያለ ምንም ዕፍረትና ይሉኝታ የነፍስ አባቴ ዳግመኛ ስነግራቸው ምን ይሉኛል ሳትይና ሳትሳቀቂ ጉዳዩን በዝርዝር አስረድተሻቸው ያንጊዜ ያልተናገርኩት ዕፍረት ይዞኝ ነው። አሁን ግን ኅሊናዬን ኃጢአቱ እረፍት ስለነሳኝ ነው ብለሽ ተናዘሽ የሚሰጥሽን ቀኖና በተግባር ፈጽሚው። 

ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ ‹‹እንድትጸድቅ መጀመሪያ ኃጢአትህን ተናገር›› ኢሳ.፵፫፥፳፮ ብሏልና። ከተለያዩ ወንዶች ጋር በዝሙት ኃጢአት መውደቅሽን መግለጽ ያለብሽ ለነፍስ አባትሽ ብቻ እንጂ ለትዳር አጋርሽ ለልጆችሽ አባት አለመሆኑንም ማወቅ ይገባሻል። ምክንያቱም አንደኛ የቀደመ በደልሽን የሚያስተሠርይልሽ ኃጢአትሽን ለካህኑ መንገርሽ እንጂ ለባለቤትሽ መንገረሽ አይደለም ባለቤትሽ ወደ ኋላ ተመልሰሽ የተደረገውን ድርጊት ስትነግሪው ጎልማሳ በሚስቱ ቀናዒ ነው ስለሚባል ሊከፋውና ሊጠላሽ ይችል ይሆናልና። ስለዚህም አሁን ማድረግ የሚገባሽ ከላይ እንደገለጽንልሸ የተደረገውን ድርጊት ኅሊናሸን ዕረፍት የነሳሽን ጉዳይ ለነፍስ አባትሽ ነግረሽ ንስሐ ግቢበት አይከብድም። በተጓዳኝ ደግሞ በመጽሐፍ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይልን ታደርጋለች›› (ያዕ.፭፥፲፮) ተብሏልና መብዓ ማለትም (ዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብ) ወደ ገዳማት ከስመ ክርስትናሽ ጋር በመላክ  በጸሎት እንዲያስቡሽ አስደርጊ። 

በተቀረው በዘመንሽ ሁሉ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በፈጸምሽው ኃጢአት እየተጸጸትሽ መኖር አንዱ የክርስትና ሕይወት መሆኑን ብታውቂም እግዚአብሔር ደግሞ መሐሪ መሆኑን ሳትዘነጊው አምነሽ ኅሊናሽን በፀፀት ከመጉዳት ተጠበቂ። ቸሩ አምላክ በደልሽን ሁሉ ይቅር ብሎሽ ትዳርሽን ባርኮ እንዲቀድስሽ የእርሱ መልካም ፈቃድ ይሁን አሜን።    

 

መንግሥት ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለቅርሶችና ምእመናን የሕግ ከለላ እንዲሠጥ ተጠየቀ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 10 March 2021
Hits: 1037
  • አጫጭር ዜናዎች
መንግሥት ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለቅርሶችና ምእመናን የሕግ ከለላ እንዲሠጥ ተጠየቀ

መንግሥት ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለቅርሶችና ምእመናን የሕግ ከለላ እንዲሠጥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጠየቁ።

ቅዱስነታቸው ይህንን የጠየቁት የዐቢይ ጾም መግባቱን አስመልክቶ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው። 

በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች በተከሠተው ችግር ምክንያት ብዙ ኢትዮጵያውያን ለርኀብ፣ ለእርዛትና መፈናቀል መዳረጋቸውን ያነሡት ቅዱስነታቸው ችግሩ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ያሳሰበ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል። 

ይህም ሆነው በሀገራችን በተከሠቱ ችግሮች ምክንያት በውስጣችን ፍቅርና ሰላም በመጥፋቱ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ችግሮቹ መፍትሔ እንዲያገኙ ሁሉም ወገን ያላሠለሰ ጥረት እንዲያደርግ መክረዋል። አብዝተን ልንሠራው ከሚገባው ነገር

ሁሉ ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነት፣ ይቅርባነት፣ መተጋገዝ፣ መራራትና ካለው ላይ አካፍሎ ለሌላው መሥጠት ሊሆን እንደሚገባም ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። 

ከዚህ በኋላ በሀገራችን የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይደፈሩ፣ ንዋየ ቅድሳትና 

ቅርሶች እንዳይዘረፉ መንግሥት ድርጊቱን በማስቆም ለሁሉም የሕግ ከልላ እንዲያደርግላቸው ቅዱስነታቸው አሳስበው የሃይማኖት ተቋማት፣ ማኅበረሰቡና በጎ አድራጊዎችም በችግር ላይ  ያሉ ወገኖችን በመደግፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

“የአንገት ማዕተቤን አላወልቅም” ያለው ወጣት ከሥራ ገበታው ተሰናበተ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1081
  • አጫጭር ዜናዎች

ኗሪነቱን ስዊድን ያደረገው የሃያ ስምንት ዓመቱ ጆርጅ ታኑዋሪ ‹‹የአንገት ማዕተቤን አላወልቅም›› በማለቱ ከሥራ ገበታው ተሰናበተ።  የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ የሆነው ጆርጅ ተቀጥሮ ከሚሠራበት ድርጅት የአንገት ማዕተቡን እንዲያወልቅ ተጠይቆ በመቃወሙ ምክንያት ከሥራ ገበታው እንደተሰናበተ ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነብቧል።    

ወጣቱን ቀጥሮ የሚያሠራው “ኢንግራም ማይክሮ” የተባለው ድርጅት “አንገት ላይ መስቀል ማድረግ ለደኅንነት አደገኛ ነው” ብሎ በማመኑ ወጣቱ መስቀሉን እንዲያወልቅ ቢጠይቀውም ወጣቱ በመቃወሙ ከሥራ ገበታው እንዳሰናበተው ከዘግባው ለመርዳት ተችሏል። በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይ ጓደኞቹ ጀለቢያና ሂጃብ አድርገው እየሰሩ እርሱ ማዕተብ እንዳያደርግ መከልከሉ ሃይማኖታዊ መድሎ እንደተፈጸመበት መሆኑን ማስረዳቱን በዘገባው ተገልጧል።    

የኩባንያው ባለሥልጣናት በበኩላቸው መስቀልም ሆነ ጌጣጌጥ ማድረግ እንደማይፈቀድ ለወጣቱ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል። ጆርጅ በበኩሉ በድርጅቱ ተቀጥረው  ያሉ ሠራተኞች ጌጣጌጦችንና የእስልምና አልባሳትን ለብሰው ሲሰሩ ማየቱን ገልጾ ‹‹በድርጅቱ ተቀጥረው ያሉ ሌሎች ብዙዎች ሂጃብ ለብሰው እንደሚሠሩት ሁሉ እርሱም የአንገት መስቀል በአንገቱ ላይ አድርጎ የመስራት መብት እንዳለው ለኩባንያው ባለሥልጣናት ማስረዳቱን ዘገባው አመላክቷል።    

ባለፉት ዓመታት በምእራብ አውሮፓ ሀገራት በክርስቲያኖች ላይ በርካታ የሃይማኖት መድሎዎች መደረጋቸውን አስመልክቶ ሪፖርት መደረጉን ዘገባው አመልክቷል።   

 

ዓላማውን የሳተው የዐውደ ምሕረት ስብከታችን

Details
Written by: በጋዜጣው ሪፖርተር
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1314
  • ርዕሰ አንቀጽ

ሠርክ ቃለ እግዚአብሔርን የምንሰማባቸው የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቶች እንደሰባክያኑ መልካቸው የተለያየ ነው።  ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ቃለ እግዚአብሔርን ሰምተው ሊታነፁበት፣ ወደ ንስሓ ሊመለሱበት ፣ ባጠቃላይ የጽድቅ ሥራ ሊሠሩበት ነው።  ዛሬ ዛሬ በየዐውደ ምሕረቶቻችን የምንሰማቸው አንዳንድ ስብከቶች ዓላማቸውን የሳቱ፣ በግለሰብ ፍላጎት እና ሓሳብ ላይ የተመሠረቱ ሆነዋል።  በተከበረው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ወንጌል መሰበክ ሲገባው ስለኳስ ጨዋታ፣ ስለሰባኪው የግል ዝንባሌና ምኞት፣ስለ ዘረኝነት ፣ ስለ ወቅቱ የሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት እንዲሁም ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያተኮረ መልእክት ማስተላለፍ የተለመደ ሆኗል።  ከላይ ባነሳናቸው ሐሳቦች ዙሪያ ትኩረት የሚያደርጉ ምእመናንን ፍጹም የማያንፁ፣ በዓለማዊ ቋንቋና ሐሳብ የተሞሉ ፍጹም ግለሰባዊ ስብከቶች ከየዐውደ ምሕረቱ ሲሰሙ ሃይ የሚላቸውና ስሕተት ነው ባይ የላቸውም።  

በአበይት በዓላት፣ በሠርክ ጉባኤና፣ በቅዳሴ ሰዓት የሚሰጡ ስብከቶችን ለመስማት የሚታደሙ ምእመናንም እንዲህ ዓይነት ከዓላማው የተፋታ ስብከት ሲሰሙ ለምን አይሉም።  ነገሩን በውል ተረድተው ልክ አለመሆኑን ቢያውቁም በአብዛኛው ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አይተው እንዳላዩ ወይም በይሉኝታና በፍርሃት ተይዘው እግዚአብሔርንም እንደመዳፈር ቆጥረውት ዝም ይላሉ።  ግን እስከመቼ? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በመንግሥተ ሰማያት፣ በዘር ፣ በእርሾ እየመሰለ ማስተማሩን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።  

ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሊቃውንት በተቀመጡበት ዐውደ ምሕረት በእነርሱ ፊት ወጥቶ የሚሰብከው ሰባኪ ከምእመኑ ጋር የማይገናኝ የምእመኑን ዕድሜ፣ የትምህርትና የኑሮ  ደረጃዎች ፣ጾታንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ያላገናዘበ ትምህርት ሲሰጥ ዝም ሊባል አይገባም።  ምእመኑም የእግዚአብሔር ቤት ነው ብሎ አክብሮ የሚነገረውን ሰምቶ መሄዱ እንደተማረ ተቆጥሮ መታለፍ የለበትም።  ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ስብከቶችን በክርስትናው ባልተለወጡ ምእመናን ሕይወት እያየነው ስለሆነ ነው።  በተከበረው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥቶ ከምእመናን ልብ የማይደርስ ስብከት ሲሰጥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዝም ሊሉ አይገባም።  የጉባኤው ተካፋይ ምእመንም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች ሲያይ ዝም ከማለት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አለዚያም ወደ ስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ቀርቦ እንዲስተካከል ማድረግ ይጠበቅበታል።  

አንዳንዱ ሰባኪ እንደ ተከበረው የእግዚአብሔር ቤት ዐደባባይ ሳይሆን እንደራሱ ቤት በሚቆጥረው መድረክ ላይ የመጽሐፍ ቅዱሱን ቃል ሳይሆን የራሱን ሐሳብ ብቻ ተናግሮ  ይወርዳል።  ምእመኑ ዘንድ ስለሚደርሰው የእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን እርሱ በዚያች ሰዓት ስለሚያስተላልፈው ሐሳብ ብቻ ተጨንቆና ተጠቦ በመምጣት ያንኑ አስተላልፎ ሲወርድ ልክ አይደለህም ሊባል ይገባል።  እንዲህ ዓይነቱ ሰባኪ ሲያጠፋ ስላልተነገረው ብቻ ራሱን ትክክል አድርጎ በየሄደበት ዐውደ ምሕረት ከምእመናን ሕይወት ያልተገናኘ ስብከት ሲሰብክ ይኖራል።  በተሳሳተበት ቀንና ቦታ ስላልተነገረውም ከመንገድ የወጣ ትምህርቱ ሥር እየሰደደ ይሄድና ለመመለስ ይቸግራል።  ‹‹ ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ አባቶች ገና ከመነሻው ያልተነገረ ጥፋት በአድራጊው ዘንድ እንደ ትክክል ይቆጠራልና ሰባኪውም ሆነ ምእመኑን ወደ ፍጹም ስሕተት  ሳይገቡ እርምት ሊሰጥ ይገባል። 

የዐውደ ምሕረቱ አስተባባሪ ወይም ፕሮግራም መሪ ‹‹እከሌ የተባሉት መምህር አሁን ያስተምሩናል›› ብሎ ለወንጌል ትምህርት የተፈቀደለትን መድረክ ተጠቅሞ እግዚአብሔርን ሳይሆን ራሱን የሚያስተዋውቀውን፣ቃለ ወንጌልን ሳይሆን ይዞት የመጣውን መጽሐፍ ወይም ሲዲ አስተዋውቆና በረከት የሚገኘው ከመጽሐፉና ከሲዲው ነው በማለት የወንጌሉን ቃል ወደ ጎን ሲተው ሃይ ባይ የሚገሥፅ ያስፈልጋል።  ዐውደ ምሕረቱ ለቃለ ወንጌሉ ነው በማለት ከስሕተቱ እንዲታረም ማድረግ ካልተቻለ ‹‹ቤቴን የንግድ ቤት አደረጋችሁት . . . ›› እንዳለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐውደ ምሕረቱ ወደ ንግድ ማዕከልነት ሳይለወጥ በጊዜ መላ ሊበጅለት ይገባል።   

ትናንት ያየውን ዜናና ዓለማዊ ፊልም ለስብከቱ ማዳመቂያ አድርጎ መድረክ ላይ የሚወጣውም ሰባኪ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለመገብየት የመጣውን ምእመን ስላየው ዜናና ፊልም ዳግም እየነገረ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ስለሚያዋርደው ሰባኪ አንድ ነገር ሊባል ይገባል።  በዐውደ ምሕረቱ ያልተለመደ ፌዝና ስላቅ እያስተላለፈ ምእመኑን ‹‹ይሄ ነው ትክክለኛው›› እንዲሉ መንገድ የሚጠርገውን ሰባኪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዐውደ ምሕረቷ ዘወር ልታደርገው ይገባታል።  የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ቢሆኑ እንዲህ ዓይነት ቀልድና ፌዝ ከቃሉ ጋር ተቀላቅለው ሲነገሩ፤ ዓለምን ከነኮተቷ ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ሊያስገቡ ሲሞክሩ ‹‹ይህ የአባቶቻችን ትምህርት አይደለም›› በማለት ለቤተ ክርስቲያናቸው ክብር ሊቆረቆሩ ይገባል።  

ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት ፣ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ለማሳደግ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ውስጥ ለተሰበሰበ ምእመን የተነሣበትን ርእሰ ጉዳይ ትቶ ከርእሱ ወጥቶ ወይም የሆነው ያልሆነውን ሲዘባርቅ የዕለቱንም በዓል አስመልክቶ አንድም ሳያስተምር የጉባኤውን ሰዓት የሚጨርስ ራሱን እንዲያስተካክል መንገር ከቤተ ክርስቲያን አባቶችም ሆነ ከምእመናን ይጠበቃል።  ጊዜውን ተጠቅሞ ለምእመኑ ማስተላለፍ ያለበትን መንፈሳዊ መልእክት ሳያስተልልፍ ፤ ምእመኑን መጀመሪያ ላይ የሰማው ርዕሰ ጉዳይ እስኪጠፋበት እና አንድም ፍሬ ነገር የማያገኝበትን እንቶ ፈንቶ ሲያወራ ቆይቶ ከመድረክ ላይ የሚወርደውን ሰባኪ ተብዬ ‹‹ ቃለ ሕይወት ያሰማልን›› ማለት ሳይሆን ከሕስተቱ ተምሮ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አቅጣጫ መስጠት ተገቢ ነው።   

ታላላቅ በዓላት በሚከበሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ላይ ምእመኑን ‹‹ ዕልል በሉ፤ አጨብጭቡ›› ከማለት ያለፈ ስለ ዕለቱ አንድም ነገር ሳይናገሩ ከመድረኩ ለሚወርዱ ሰባኪዎቻችን አስቀድሞ ርእስ እና አቅጣጫ መስጠት ተገቢም ነው።  የዕለቱን ክብረ በዓል ምንነት ለምእመናን ከማስተማር ይልቅ ገንዘብ ስለመለመን ብቻ አውርተው የሚወርዱ ሰባኪዎቻችን በምእመኑ አንደበት ሳይቀር ‹‹ ምን እነሱ ብር መለመን ብቻ ነው›› እስከመባል ደርሰዋልና ቤተ ክርስቲያን ይህን ልታስብበት ይገባል።   

የቤተ ክርስቲያን አምባሳደር ሆነው በቆሙበት መድረክ ላይ የወንጌልን ቃል ሳይሆን ዘረኝነትን የሚዘሩ፤ ዘለዓለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ከማስተላለፍ ይልቅ ሰሞነኛ የፖለቲካ ትኩሳት ማቀንቀን የሚቀናቸው ሰባክያንን ‹‹ቦታው እዚህ አይደለም›› በማለት ወደ ትክክለኛው መሥመር እንዲገቡ ማድረግ ከቤተ ክርስቲያን ልጆች ይጠበቃል።  ሞልቶ ከተረፈው የእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ከዓለም በቃረሙት ቃላትና ምሳሌ ወደ ዐውደ ምሕረት አምጥተው ምእመናንን የሚያደነቁሩ ሰባክያን ልክ አይደለም ሊባሉ ይገባል።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአለባበስ ሥርዓት በመጣስ ያልተፈቀደላቸውንና የማይገባቸውን የቤተ ክርስቲያን ልብስ በመልበስ ወደ መድረክ ብቅ የሚሉ ሰባኪዎቻችንን ቤተ ክርስቲያን ችላ ልትላቸው አይገባም።  

ዐውደ ምሕረቱን ተጠቅመው የእግዚአብሔርን ቃል የሚሸቃቅጡትን፤ ‹‹ በነፃ የተሰጣችሁን በነፃ ስጡ ›› የሚለውን ቃል ዘንግተው ኪሳቸውን ለመሙላት ብቻ የምእመኑን ኪስ የሚያራግፉትን (ዋጋ ተምነው ይህን ያህል ሊከፈለኝ ይገባል በማለት በድርድር ዐውደ ምሕረት ላይ የሚቆሙ) ሰባክያን ቤተ ክርስቲያን ለይታ ልታወጣቸው ይገባል።  በዚያው ልክ ለቤተ ክርስቲያን ክብር የቆሙ ጨዋ የወንጌል ሰባክያንን (ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ደሃ አይደለችምና) ወደ መድረክ ልታመጣ ፣ ልትጋብዝ፣ እንዲያስተምሩ ልታደርግም ይገባል።  ባጠቃላይ ምእመኑ ጥሎት የመጣውን ዓለም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ በድፍረት የሚያስተዋውቁ የወንጌል ነጋዴዎች ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ምእመኑን እየጎዱ ነውና ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቷን  በትኩረት ልታየው ይገባል።

ቤተ ክርስቲያንን ያከበረች ከተማ…

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1040
  • ሪፖርታዥ
ቤተ ክርስቲያንን ያከበረች ከተማ…

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ፈተና ያልተለያት እንደሆነች በዘመናት ውስጥ ከተጻፉ የታሪክ ድርሳናት  መረዳት ይቻላል። ቤተ ክርስቲያን በፀረ ክርስቲያን ኃይሎች መፈተኗ አላጠፋትም፤ ምእመናንንም ከአምልኮተ እግዚአብሔር አላራቃቸውም።   ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እያሰፋች ለዓለም ብርሃን መሆኗን ቀጥላለች።    ከዘመናዊ ትምህርት ዘርፉ ከሚገኝ ዕውቀት በበለጠ የቋንቋ፣ የሥነ ጥበብ፣ የኪነ ሕንፃና የፍልስፍና ምንጭ ሆና መቀጠሏ ዓለም ያወቀው ገሃድ ነው።  ይሁን እንጂ ኃያልነቷንና ታሪካዊነቷን የተረዱና ያልተረዱ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን ከሚያልሙ ፀረ ክርስቲያን ኃይሎች መገኛ ሀገራት መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ናት።    

Read more: ቤተ ክርስቲያንን ያከበረች ከተማ…

“የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የልጆቿን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው” -ብፁዕ አቡነ አብርሃም (የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ክፍል አንድ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1003
  • ፍሬ ከናፍር
“የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የልጆቿን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው”             -ብፁዕ አቡነ አብርሃም (የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)             ክፍል አንድ

በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዊ ብሔረሰብ አስተዳድር ቻግኒ ከተማ ዙሪያ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠልለው ይገኛሉ።    የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማጽናናት፣ ለመባረክ እንዲሁም ከሀገረ ስብከቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ርዳታ ለማስረከብ በቦታው በተገኙበት ወቅት ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባባ።    

ስምዐ ጽድቅ፡-  በፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል ቻግኒ ከተማ ዙሪያ የተጠለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሲያዩ ምን ተሰማዎት? ምንስ ታዘቡ?

ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- ቻግኒ ላይ ያየሁት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝና ልብን የሚሰብር ክስተት ነው። ከፖለቲካ የራቁና ሠርቶ አርሶ ከመብላት ውጭ ምንም የማያውቁ ዜጎችን ከሞቀ ቤታቸው እያስወጡ በጭካኔ መግደልና ማሳደድ በእውነት ሰብአዊነትን ያላከበረ ተግባር ነው። ምንም የማያውቁ ሕፃናት፣ ለዘመናት ሀገራቸውን በተለያየ መስክ ያገለገሉ የዕድሜ ባለጸጐች ሴቶችንና እናቶችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መግደልና ማፈናቀል የወንድነት መለኪያ መስፈርት ሊሆን አይገባም።  ከሞት ጥላ አምልጠው በቻግኒ ከተማ አቅራቢያ ተጠልለው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቀን ፀሐይ የማታ ብርድ እየተፈራረቀባቸው ማየት ደግሞ ከምንም በላይ ልብን ያቆስላል።     

     

Read more: “የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የልጆቿን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው” -ብፁዕ አቡነ አብርሃም (የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)...

አባ ገላስዮስ

Details
Written by: እህተ ሚካኤል
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1075
  • የሕፃናት ዓምድ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከረማችሁ? አሜን የአባቶቻችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! 

ልጆች ትምህርታችሁን በንቃት እየተከታተላችሁ ነው? እያጠናችሁስ ነው? በርቱ ትምህርታችሁን በተገቢው መንገድ በመከታትል በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋል!

ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው አባ ገላስዮስ ስለሚባል ቅዱስ አባት ታሪክ ነው፤ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!                                                                      

ልጆች አባ ገላስዮስ እግዚአብሔርን ከሚያመልኩና ከሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያን ወላጆች የተገኘ ቅዱስ አባት ነው።    ቤተ ሰቦቹም ልጃቸው ገላስዮስን ከሕፃንነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩት በምግባርና በሃይማኖት ኮትኩተው አሳደጉት።    በኋላም ገላስዮስ የዲቁና ማእረግ ተቀበለ።   

ቅዱስ ገላስዮስም ከትንሽነቱ ጀምሮ ይህንን ዓለም በመናቅ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር የሚተጋ መነኩሴ ሆነ።    በምንኩስና ሆኖ በጾም በጸሎት እየተጋደለ መኖር ጀመረ።    እግዚአብሔር አምላክም የቅዱስ ገላስዮስን ትጋት ተመልክቶ በአስቄጥስ ገዳም ባሉ መነኮሳት ላይ ቅስና ተሾመ።    በአስቄጥስ ገዳም ሆኖ በታላቅ ተጋድሎ የገዳሙን ማኅበረ መነኮሳት እያገለገለ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ለአባ ጳኩሚስ እንደተገለጠ ለአባ ገላስዮስም ተገለጠለት።   

በገዳሙ ያሉ መነኮሳትንም ሰብስቦ እግዚአብሔርን መፍራትንና የምንኩስናን ሕግ እንዲያስተምራቸው አዘዘው። በገዳሙ የሚገኙ መነኮሳትን በመሰብሰብም መንፈሳዊ የሆነ የአንድነት ማኅበራዊ የኑሮን ሥርዓት ሠራላቸው።  አባ ገላስዮስም በመነኮሳቱ መካከል ሲኖር እጅግ ትሑት ከመሆኑ የተነሳ እንደ መምህራቸው ሳይሆን ከእነርሱ እንደሚያንስ እንደ አገልጋያቸው ይሆን ነበር።   

አባ ገላስዮስ በአስቄጥስ ገዳም መነኮሳቱን በፍጾም የዋህነት፣ ቸርነትና በመታዘዝ ያገለግላቸው ነበር።    በዚያም ሳለ የብሉይ ኪዳን እና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በአንድነት ሰብስቦ አንድ ታላቅ መጽሐፍ ጻፈ። ይህን ታላቅ መጽሐፍ ለማጻፍም ፲፰ የወርቅ ዲናር አወጣ።    ያንንም ታላቅ መጽሐፍ መነኮሳቱ ለማንበብ በሚፈልጉ ጊዜ እንዲያገኙት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአትሮንስ ላይ አኖረላቸው።   

አንድ ሰውም ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋዊ አባ ገላስዮስን ሊጎበኝ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጣ። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሲዘልቅም ማንም አልነበረም፤ ነገር ግን ያንን ታላቅ መጽሐፍ በአትሮንስ ላይ ተቀምጦ አየና ሊወስደው ፈለገ። ጨለማ በሆነ ጊዜም ተመልሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጣና ማንም ሰው ሳያየው መጽሐፉን ሰርቆ ወጣ ሊሸጠውም ወደ ከተማ ይዦት ሄደ።    አንድ ሰውም መጽሐፉን ሊገዛው ፈልጎ ‹‹የመጽሐፉ ዋጋ ምን ያህል ነው? አለው።   

ሌባውም ‹‹ ፲፯ የወርቅ ዲናር ስጠኝና ውስደው›› አለው።   

ገዢውም ‹‹ያልከውን ፲፯ የወርቅ ዲናር እሰጥሃለሁ ነገር ግን ለወዳጄ ወስጄ እስካሳየው ድረስ ጥቂት ታገሰኝ›› አለው።    ሌባውም በዚህ ስለተስማማ ገዚው መጽሐፉን ወደ አባ ገላስዮስ ዘንድ ይዞ በመሄድ ‹‹ አባቴ ሆይ! ይህ መጽሐፍ ተመልከትልኝ፤ መልካም ከሆነ እገዛዋለሁ›› አለው።   

አባ ገላስዮስም መጽሐፉን ሊገዛ የመጣውን ሰው ‹‹ መጽሐፉን ሊሸጥልህ ያለው ሰው ምን ያህል ገንዘብ ጠየቀህ?›› አለው።   

ገዥውም ‹‹ ፲፯ የወርቅ ዲናር ጠየቀኝ›› በማለት ነገረው።   

አባ ገላስዮስም ‹‹መጽሐፉ መልካም ነው ዋጋው ቀላል ነው ግዛው›› አለው።    

ገዥውም ወደ ሌባው ተመልሶ እና አባ ገላስዮስ የነገረውን ደብቆ ‹‹ ለአባ ገላስዮስ አሳየሁት እርሱም ዋጋው በዝቷል አለኝ ›› አለው።    

ሌባውም ‹‹ያ ሽማግሌ ሌላ የተናገረህ ነገር የለም? ››  በማለት ገዢውን ጠየቀው።   

ገዢውም ‹‹አዎን ሌላ ምንም ነገር አልተናገረኝም›› አለው።   

በዚህ ጊዜ ያ መጻተኛ ሌባ ‹‹ ይህን መጽሐፍ በፍጹም አልሸጠውም›› ብሎ ወደ አባ ገላስዮስ ሄደ።    ከእግሩ በታች ወድቆም ‹‹ ሰይጣን አስቶኛልና ይቅር በለኝ ፤ መጽሐፍህንም ውሰድ›› ብሎ ለመነው።    

የከበረ አባ ገላስዮስ ግን ‹‹ እኔ መጽሐፉን መውሰድ አልሻም ሽጠህ የወርቁን ዲናር ለምትፈልገው ተግባር አውለው›› አለው።    ሌባውም በፊቱ እያለቀሰ እና እየሰገደ ብዙ ለመነው፤ ከብዙ ድካም በኋላ አባ ገላስዮስ መጽሐፉን ተቀበለው።    ይህንንም ምሥጢር ከሁለቱ በስተቀር ማንም አያውቅም ነበር።    

ልጆች የአባ ገላስዮስን ደግነት አያችሁ? መጽሐፉን ሊገዛው የነበረው ሰው ይዞለት ሲመጣ ‹‹የኔ ነው፤ ተሰርቆ ነው›› ብሎ አላጋለጠውም ይህን ማድረጉ ሌባው የአባ ገላስዮስን መጽሐፍ በመስረቁ ተጸጽቶ እንደመለሰለት አስተውሉ።    

ልጆች! ከዚህ በኋላ ለአባ ገላስዮስ ትንቢት የመናገር ሀብት ተሰጠው፡፤ ብዙ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ያደርግ ነበር።    በአንዲት ዕለትም የገዳሙ ወጥ ቤት የሚሠራው ሰው ለገዳሙ መነኮሳት ዓሳ ወጥ ሰርቶ አንዱን ልጅ በመጥራት ‹‹ እስክመለስ ድረስ ጠብቅ›› ብሎት ወደ ሥራው ሄደ።    እንዲጠብቅ የታዘዘው ልጅ ግን ለገዳሙ መነኮሳት ከተቀመጠው ዓሳ በላ።     ወጥ ቤት ሠራተኛውም ተመልሶ ሲመጣ ወጡ ተበልቶ በማግኘቱ ልጁን ‹‹ አረጋውያን አባቶች ሳይባርኩት እንዴት ደፍረህ ትበላለህ? አለው።    የቁጣ መንፈስም በልቡ አደረና ልጁን ረግጦ ገደለው፤ ልጁ ፈጽሞ እንደሞተ አይቶ እጅግ ደነገጠ።    

ታላቅ ፍርሃትም ፈራና ወደ አባ ገላስዮስ ሄዶ የሆነውን ሁሉ ነገረው።    አባ ገላስዮስም ወጥ ቤት ሠራተኛውን ‹‹የልጁን ሬሣ ወስደህ ከቤተ መቅደሱ ፊት አስተኛው›› በማለት አዘዘው።    ወጥ ቤት ሠራተኛውም አባ ገላስዮስ እንዳዘዘው አደረገ።    ማታም በሆነ ጊዜ አረጋውያን መነኵሳት በቤተ ክርስቲያን ጸሎት አድርገው ወጡ።    አረጋዊ አባ ገላስዮስም ከእነርሱ ጋር በወጣ ጊዜ የሞተው ልጅ ተነሥቶ ከኋላው ተከተለው ይህንን ማንም አላወቀም ነበር።    

እርሱም የገደለውን ባለወጥ ለማንም እንዳይናገር አዘዘው።    የተመሰገነ አባ ገላስዮስም ያማረ ትሩፋቱንና ተጋድሎውን ፈጽሞ ፤ እግዚአብሔርን አገልግሎ ፤ይህንንም በጎ ተግባር መታሰቢያ ትቶ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሰላም ዐረፈ።   

ልጆች ከታሪኩ ብዙ መንፈሳዊ እውቀት እንደቀሰማችሁ ተስፋ እናደርጋለን።    በሚቀጥለው ትምህርታችን እስክንገናኝ በትምህርታችሁ ጎብዛችሁ እንድታጠኑ ደግሞም በጸሎትና በጾም እንድትበረቱ እንመክራችኋለን፤ ደኅና ሰንብቱ! 

ልጆች! የአባ ገላስዮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን አሜን!

ምንጭ ፦ ስንክሳር የካቲት ፲፪

 

‹‹ምን አለበት››

Details
Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1180
  • ትዝብት

ክርስትና ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ይጠራል፤ የጠራቸውን ደግሞ አስተምሮ አጥምቆ ይመርጣል፤ የመረጣቸውን ደግሞ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አሳድጎ ያጸድቃል።     

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአንድ ክርስቲያን ጉዞው ቤተ ክርስቲያን በሠራችው ሥርዓት ውስጥ ነው።    ያለሥርዓት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠትም ይሁን መቀበል አይቻልም። በመሆኑም ያለሥርዓት መመላለስ ለቤተ ክርስቲያን አለመታዘዝ ነው። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የክርስቶስ አካል ስለሆነች ለክርስቶስ አለመታዘዝ ይሆናል።    መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን።›› ፩ኛ ቆሮ ፲፬፥፵ ይላል።   

ለአንዳንዶች ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አላስፈላጊ፣ ተደራቢ፣ ትርፍ ነገር ይመስላቸዋል።  ለኦርቶዶክሳውያን ግን አግባብ በሆነ መንገድ እግዚአብሔርን ለማምለክ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።    በመሆኑም ቅዳሴው፣ ጥምቀቱ፣ በዓላቱ፣ ጾሙ፣ ትምህርቱ /ስብከቱ/ ወዘተ በሥርዓት የሚከናወን ነው።   

Read more: ‹‹ምን አለበት››

ንሰሐ አባቴን የደበቅሁት ምሥጢር፦ ወደ ኋላ መመለስ ፈራሁ ክፍል አንድ

Details
Written by: በዝግጅት ክፍሉ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1366
  • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ

ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ለረጅም ጊዜ በውስጤ ሲመላለስ የቆየ እና ሰላም የነሳኝን ጥያቄ ልጠይቅ ወደድኩ የኅሊና ዕረፍት የሚሰጥ መልስ ትሰጡኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።  ስሜ ወለተ ገብርኤል ይባላል ዕድሜዬ በአርባዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች እናት ነኝ።  ትዳር ከመመሥረቴ በፊት ከተለያዩ ወንዶች ጋር ተራክቦ እፈጽም ነበር።  የአሁኑን የትዳር አጋሬን ሳገባ ይህንን አልነገርኩትም ነበር።  በጊዜው ከሱ በፊት ከነበረኝ የወንድ ጓደኛዬ ጋር በአጋጣሚ በተፈጠረ ክሥተት ስህተት ላይ መውደቄን ብቻ ነግሬው ነው ያለፍኩት። ለንስሐ አባቴም በወቅቱ ያለፈ ሕይወቴን እና የሠሁትን ኃጢአት በሙሉ ዘርዝሬ አልነገርኳቸውም።  ለአሁኑ ባለቤቴ የነገርኩትን ብቻ ነግሬ ሌሎቹን ‹‹ያለፈ ታሪክ ነው›› በሚል ምክንያት ሸፋፍኜ ነው ያለፍኩት።  በዕድሜ እየበሰልኩ ስመጣ እና ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ውስጤ ይደነግጣል፤ በኅሊናዬም ኃጢአተኛ እንደሆንኩ እያስታወሰኝ በየዕለቱ ይወቅሰኛል።  ከዚህም የተነሣ መልካም ለሆነው ባለቤቴ፣ ለልጆቼ፣ ለንስሐ አባቴ በተለይም ለእግዚአብሔር ታማኝ እንዳልሆንኩ ይሰማኛል። 

ውድ የስምዐ ጽድቅ አዘጋጆች! ያለፈውን ኃጢአቴን እያሰብኩ በየዕለቱ ፀፀት ቢሰማኝም በጊዜው የደበቅሁትን ምሥጢር ግን አውጥቼ መናገር ፈራሁ።  ለመሆኑ ያለፈ በደሌን ዛሬ ላይ አለመናዘዜ ኃጢአት ይሆን? ፀፀቴን መሸከም ባለመቻሌ ለባለቤቴ እና ለንስሐ አባቴ መንገር እፈልግና ወደ ኋላ መመለስ ፈራሁ።  ምን ላድርግ ምንስ ትመክሩኛላችሁ እባካችሁ ዘርዘር አድርጋችሁ አስረዱኝ።  

Read more: ንሰሐ አባቴን የደበቅሁት ምሥጢር፦ ወደ ኋላ መመለስ ፈራሁ ክፍል አንድ

የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋትና የማጠናከር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተገለጠ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1262
  • አጫጭር ዜናዎች
የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋትና የማጠናከር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተገለጠ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋትና የማጠናከር ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ ዲ/ን አንድነት ብርሃኑ ገለጡ።   

በአብነት ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ መርሐ ግብር ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሌላቸው አካባቢዎች ተለይተው አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የሚቋቋሙ ሲሆን በማጠናከሪያ መርሐ ግብር ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማሻሻልና የመደገፍ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ም/ኃላፊው ገልጸዋል።   

ማኅበረ ቅዱሳን ሃያ አምስት አህጉረ ስብከት ለይቶ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የገለጡት ኃላፊው “በዚህ ዓመት ብቻ በአራት አህጉረ ስብከት የአብነት ት/ቤቶችን ለመሥራት እቅድ ይዟል” ብለዋል። እቅድ ከተያዘላቸው አራት አህጉረ ስብከት መካከል አፋር፣ ሶማሌ፣ አርሲና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት እንደሚገኙበት ያስታወቁት ኃላፊው የሶማሌ ሀገረ ስብከት የአብነት ትምህርት ቤት በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ሲሆን በዚህ ወርም የግንባታ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል።    ሌሎች ተመሳሳይ የአብነት ትምህርት ቤቶች ግንባታም በሂደት ሥራቸው እንደሚጀመር አስረድተዋል።   

አዲስ በሚቋቋሙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአካባቢያቸውን ባህልና ቋንቋ ጠንቅቀው የሚያውቁ ወጣቶች ተመልምለው እንደሚገቡ ያስረዱት ኃላፊው በሚኖራቸው የሁለት ዓመት ቆይታም የቤተ መቅደስና የዐውደ ምህረት አገልግሎትን እንደሚቀስሙ ተናግረዋል።   

ኃላፊው አያይዘውም ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ት/ቤቶችን ከማቋቋምና ከማጠናከር ባሻገር ጊዜያዊ የገንዘብ ድጋፍም እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።    አጠቃላይ ለተማሪዎችና ለመምህራን የሚደረገው ወርኅዊ የገንዘብ ድጋፍ በዓመት እስከ አምስት ሚሊዮን እንደሚደረስም አስረድተዋል።   

ባልታወቀ ምክንያት ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የሳት ቃጠሎ አደጋ የደረሰበት የጨጎዴ ሃና የቅኔ ማስመሥከሪያ ጉባኤ ቤት በአዲስ መልክ እየተሠራ መሆኑን ም/ ኃላፊው ተናግረዋል።   የቅኔ ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤት ፕሮጀክት የተጀመረው ፳፻፪ ዓ.ም ሲሆን ለፕሮጀክቱ የዋለውን ፳ ሺህ ካሬ መሬት የሰጠው የምዕራብ ጎጃም ዞን የቋሪት ወረዳት መንግሥት ነው።   

ፕሮጀክቱ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመምህራን መኖሪያ፣ የተማሪዎች መፀዳጃ ቤትና የምግብ ማብሰያ ያካተተ ሲሆን ሲጠናቀቅም በርካታ ነባርና አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ ም/ኃላፊው ገልጸዋል።    ፕሮጀክቱ ከ፵፭ በመቶ በላይ የደረሰ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን የበጀት እጥረት እንደገጠመው አስረድተው የተፈለገው ያህል በጀት የሚገኝ ከሆነ ግን በቅርቡ መጠናቀቅ እንደሚችል አስታውቀዋል።   

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጭ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን ከዚህ ቀደም ወጭ የተደረገው  ገንዘብ ከምእመናን ድጋፍ የተገኘ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው “አዳዲስ የሚቋቋሙና ነባር የአብነት ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን በገቢ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።   

‹‹የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ ነው ያኖረኝ›› መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ ብሩ ክፍል አንድ

Details
Written by: መጽሐፈ ሲራክ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 23 February 2021
Hits: 1134
  • ቤተ አብርሃም
‹‹የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ ነው ያኖረኝ››                                          መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ ብሩ                                                                                 ክፍል አንድ

የተወደዳችሁ አንባብያን በዛሬው የቤተ አብርሃም ዐምድ ዝግጅታችን የምናቀርብላችሁ በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካተድራል የሐዲስ ኪዳን መምህር የሆኑትን መጋቤ ሐዲስ አባ አእምሮ ብሩን ነው።  በ ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ወደ ካቴድራሉ ሲመጡ በሐዲስ ኪዳን መምህርነት ተመድበው  ለተወሰነ ጊዜ አገልግለዋል።  ብዙም ተማሪዎች በቦታው ላይ ባለመገኘታቸው በአሁን ሰዓት በስብከተ ወንጌል እና በተጓዳኝ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የማይክሮ ሊንክ ግቢ ጉባኤዎችን እንዲሁም በአጥቢያው ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥት እና የግል መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር መበሆን ያስተምራሉ፣ የአጥቢያውን ሕፃናት ጠዋትና ማታ ከፊደል ጀምሮ እያስተማሩ ይገኛሉ።    አባታችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ያላቸውን የአገልግሎትና የሕይወት ተሞክሮ እንዲያካፍሉን እንግዳ አድርገናቸዋል ተከታተሏቸው፦ 

 

Read more: ‹‹የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ ነው ያኖረኝ›› መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ ብሩ ክፍል አንድ

በሙዚቃ ድግስ የታጀቡ የቤተ ክርስቲያን በዓላት ከየት ወዴት?

Details
Written by: በዝግጅት ክፍሉ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 09 February 2021
Hits: 1315
  • ርዕሰ አንቀጽ

መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው የክርስትና ሃይማኖትና አስተምህሮ የሆኑት፤ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ የሆኑትንና  በምእመኑ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቁ በዓላት በዓለማዊ ኮተት እንዲታጀቡ መደረግ ከጀመሩ ሰንብተዋል።  በቤተ ክርስቲያናችን እና በምእመናን ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው የዘመን መለወጫ፣ ገና፣ ጥምቀት እና የትንሣኤ በዓላት ቀደም ሲል የገበያ ማሻሻጫ አሁን አሁን ደግሞ የዘፈን እና የመዝናኛ ማጀቢያ እንዲሆኑ የተፈረደባቸው ይመስላል።  

ቀደም ባሉት ዓመታት የዘመን መለወጫ፣ የገና፣ የጥምቀትም ሆኑ የትንሣኤ በዓላት ሲደርሱ በዓላቱን በማስታከክ  በመስቀል የአደባባይ ኤግዚብሽን ማዕከል ይደረግ የነበረው ዝግጅት ገበያ ብቻ እንደነበር ይታወቃል።  በተለይ ገዢና ሻጭ የሚገናኝበት፤ ከወትሮው በተለየ መልኩ ሌላ ጊዜ እና ቦታ ውድ የሆኑ ነገሮች በርካሽ የሚገኙበት  በየቦታው እንደልብ የማይገኙ የምግብ ዓይነቶች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች በአንድ ቦታ ለተጠቃሚው የሚቀርቡበትም ነበሩ።  ከላይ እንደተጠቀሰው ገበያው የሚካሄደው በበዓላቱ ስም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።  

Read more: በሙዚቃ ድግስ የታጀቡ የቤተ ክርስቲያን በዓላት ከየት ወዴት?

Page 9 of 19

  • 4
  • 5
  • 6
  • 7
  • 8
  • 9
  • 10
  • 11
  • 12
  • 13

የቅጅ መብት © ማኅበረ ቅዱሳን 2012 ዓ.ም.

ዋናው ማዕከል | Afaan Oromoo | English |አሜሪካ ማዕከል | አውሮፓ ማዕከል | ካናዳ ማዕከል | ትሩፋት
MK Facebook MK Telegram MK Youtube
አጫጭር ዜናዎች የሕፃናት ዓምድ ትዝብት ሪፖርታዥ ቤተ አብርሃም ፍሬ ከናፍር ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ርዕሰ አንቀጽ Oct ኪነ ጥበብ June ዐውደ ስብከት sept እናስተዋውቃችሁ ትምህርተ ሃይማኖት Nov Mar Apr ዐቢይ ጉዳይ ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት የነገዋ ቤተ ክርስቲያን የጥያቄያዎቻችሁ መልስ July የማኅበሩ መልእክት Jan Aug May 1997 13 ከዓለም ማእዘናት