- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1267
በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት የለሃ ደብር ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና አገልጋዮች ከእስር በዋስ ሊፈቱ እንደሆነ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ገለጡ፡፡
የለሃ ደብር ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለበርካታ ዓመታት በበዓላት ማክበሪያ ይዞታነት ሲጠቀምበት የነበረውን መሬት የመሎ ኮዛ ወረዳ የመንግሥት አካላት “መሬቱ ይፈለጋል” በማለት መንጠቃቸውን ተከትሎ ምእመናን ‹‹የቤተ ክርስቲያኑ ይዞታ ይከበር›› በማለታቸው ብቻ ለእስርና ገንዘብ መቀጮ እንደተዳረጉ ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ይዘው ወደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ቢሮ ድረስ መሄዳቸውን የገለጡት ብፁዕ ነታቸው ከውይይታቸው በኋላ የታሠሩ ምእመናንና አገልጋዮች በዋስ እንዲፈቱና የተወሰደው የቤተ ክርስቲያን ይዞታም እንዲመለስ ርዕሰ መስተዳድሩ መወሰናቸውን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሚያስፈጽሙ እንደነገሯቸው ያስረዱት ብፁዕነታቸው የታሰሩ ምእመናንና አገልጋዮች ሆnu የበዓላት ማክበሪያ ቦታው በቅርቡ መፍትሔ ያገኛሉ ቢባልም መቼ ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ እንዳላኙ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ሀገረ ስብከቱ ተፈጻሚነቱን በቅርበት እንደሚከታተል የጠቆሙት ብፁዕነታቸው “ከዚህ ቀደም ጉዳዩ ጥቅምት !6 ቀን !)0፫ ዓ.ም መፍትሔ እንደሚያገኝ የተነገረን ቢሆንም የወረዳ ቤተ ክህነቱ የፍርድ ሂደቱን ለሀገረ ስብከቱ ባለማሳወቁ ሂደቱ ተጓቷል” ብለዋል፡፡
በየሀገረ ስብከቱ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ብፁዕነታቸው ያነሱ ሲሆን “እኔ የምመራውን ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመመራት የሚፈጠሩ ችግሮችንና ስጋቶችን ከየአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በጋራ ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1325
ያሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት በተለይ በ፳፻፲፪ ዓ.ም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። ለዘመናት የመንግሥት ለውጥ በተደረገ ቁጥር የጥቃት ዒላማ ሆና የኖረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁንም በተመሳሳይ ሰቆቃን አሳልፋለች። ካለፉት ተደጋጋሚ ድርጊቶች በመነሣት ጠላቶቿ የመንግሥትን ለውጥ አለዚያም ትንሽ ግርግርን ተገን አድርገው ሊያጠቋት ሠይፍ ይዘው እንደሚነሡ ታዝበናል። ዛሬም እያስተናገደች ያለችው ይህንኑ ነው። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ምእመናንና ምእመናት፣ ሕጻናትና ወጣቶ፣ አዛውንቱና አረጋውያኑ፣ ካህናትም ሳይቀሩ ብዙዎቹ የወቅቱ የጥቃት ሰለባ ሆነው አልፈዋል። የሰውን ልብ የሚሰብር ግፍ የተፈጸመባቸው፣ ከቤት ከንብረታቸው የተፈናቀሉ፣ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ብዙዎች ናቸው። አብያተ ክርስቲያናቱ ተቃጥለው፣ ካህናቱ ተሰደው ተንገላተው ባቆሟት ሀገር ባይተዋር ሆነው አሳልፈዋል።
በዚያው መጠን በደረሰው ጉዳት እና ጥፋት ልክ ቤተ ክርስቲያን እና ልጆችዋን ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ቁጥር ቀላል አይደለም። በየቦታው የደረሰውን መጠነ ሰፊ ጥፋት በመከታተልና በማጋለጥ፤ ሊደርስ የሚችለውን የጥፋት ዕቅድም አስቀድሞ መረጃ በመስጠት ብዙ ሥራ ሠርተዋል። ለተጎዱት በመድረስ ጉዳታቸውን፣ኀዘናቸውን በመካፈል አለኝታ ሆነዋቸዋል። በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን መከራ ጮኸው ለዓለም አሳውቀዋል። በጊዜው ድምጽ ላልነበራቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ድምጽ ሆነዋል። ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ በግልም በቡድንም የተደረገው ርብርብ የነገን ተሰፋ የሚያጭር ለቤተ ክርስቲያን ኩራት፤ ለምእመናንም አርአያ የሆነ፣ ይበል የሚያስብል ሥራ ነውና ሊመሰገኑ ይገባል።
ስለ ክርስትናቸው ከቤተ ክርስቲያን ጥፋት በፊት ራሳቸውን አስቀድመው ሰማዕትነትን ስለተቀበሉት ምእመናን ‹‹ክርስትና ማለት ይህ ነው›› ብለው ለቀረነው ክርስቲያኖች ጽናት እንዲሆነን መስክረውልናል። በሕይወት ለቀሩት ነገር ግን በጥቃቱ በአንድ ጀንበር ንብረታቸው ለወደመባቸው ፣ ከነበሩበት ከፍተኛ የኑሮ ማማ ላይ ወርደው የሰው እጅ ተመልካች ለሆኑት ምእመናን ቀድሞ በመድረስ፤ የምግብ፣ የልብስ እና የገንዘብ ዕርዳታን በማድረግ የፈረሰ ቤታቸውን የሠሩ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች ዋጋቸው በምን ይተመናል? የተቃጠለውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ከበፊቱ በተሻለ በመሥራት በፈረሰው በኩል የቆሙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በእምነት እንዴት መቆም እንዳለብን አሳይተውናልና ሊመሰገኑ ይገባል።
የእምነት አርበኛ በሆኑት የቤተ ክርስቲያን ልጆች፤ በኅብረት እና በግል የተደረጉ እርዳታዎች፣ ለመልካም ነገር የተዘረጉ እጆች ባጠቃላይ ሰጪዎችን ብቻ ሳይሆን የተሰጣቸውን ተጎጂዎች በእምነታቸው እንዲጠነክሩ ነገን ተስፋ እንዲያደርጉ ያስቻለ በተግባር የተገለጠ ክርስትናን አሳይተውናል። ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፣ ስለተጎጂዎቹ ልጆችዋ የመንግሥትን ቸልተኝነት ፊት ለፊት ያጋለጡ፣ ጊዜ የሰጠውን አጥፊ ሳይፈሩ በክፉ ቀን ከቤተ ክርስቲያን ጎን የቆሙ ፣ ሳይሳቀቁ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን የጮኹ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች አርዓያዎቻችን ናቸው። በተለይም ነገን እንዴት መኖር እንዳለብን አሳይተውናልና የመንፈስ ጥንካሬያቸውን፣ መንፈሳዊ የዓላማ ጽናታቸውን አርአያ ልናደርገው ይገባል።
የጠላትን ዛቻና ጥፋት ሳይሳቀቁ ያጋለጡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ከምእመኑ እስከ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕልውና ከፊት ቆመው ጮኸዋል። በቃል ብቻ ሳይሆን ጥፋት በደረሰባቸው ቦታዎች ተገኝተው የምእመኑን ኀዘን ተካፍለዋል፣ ያላቸውንም በመስጠት ብርታት እና ጉልበት ሆነዋቸዋል። ስለቤተ ክርስቲያን መሥዋዕትነትን የከፈሉ ምእመናንን፤ ቤተ ክርስቲያን ለዘላለም ታስባቸው ዘንድ ‹‹የቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት ቀን›› ብለው ሰይመውላቸዋል። ዛሬ መልካም ዛፍን ተክለው የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ፍሬዋ እንዲበዛ አድርገዋል። በየቦታው ሲመቱት የሚጠብቅ ክርስቲያንን አንጸዋል፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዴት መኖር እንዳለብን ክርስትናን በተግባር አሳይተውናልና በክብር ሊዘከሩ ይገባል።
ቦታና ጊዜ ሳይገድባቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጆሮአቸውን የሰጡ፣ እጃቸውን የዘረጉ ከውስጥና ከውጭ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶች የነበራቸውን ተሳትፎ በቀላሉ ማየት አይቻልም፤ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ነገር ማለት ነውና። በመከራ ውስጥ ያለፈችውን ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንዋን ለመታደግ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ከሕመሟ እንድትፈወስ፣ ከድካሟ እንድትበረታ፣ በጽናቷ እንድትቀጥል በማድረግ ለቀረው ምእመን የቤት ሥራ ሰጥተዋል።
ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተጋረጠውን መከራ ፊት ለፊት በመናገር ፣ በማስጠንቀቅ እንዲሁም ምእመናኑን በማጽናናት አባቶቻችን ያሳዩት ቁርጠኝነት ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ብርታት ሆኗታል። በቦታው ላይ በመገኘት ለምእመናን ያሳዩት አባታዊ ፍቅር እና ምክር የመልካም እረኝነትን ተግባር የገለጠ ነውና ሳይታሰብ መታለፍ የለበትም። ታላላቅ ጉባኤያትን በማዘጋጀትና በቦታው ላይ በመገኘት ለምእመናኑ አባታዊ ምክር በመስጠት ፣ በመባረክ የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ የተወጡ አባቶቻችን፣ በቃለ ወንጌሉ ፣ በዝማሬ ሲያጽናኑ የነበሩ ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ለቤተ ክርስቲያን ባሳዩት ፍቅር ልክ ሊታሰቡ ይገባል።
በፈረሰው በኩል በመቆም ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ እንዳይቋረጥ ባጠቃላይ ምእመንዋ እንዳይበተንና፣ እንዳይጠፋ ባለበት ጸንቶ እንዲቆም የታገሉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። በተለይም የጥቃቱ ሰለባ የነበሩቱ ስአንዲትዋ ቤተ ክርስቲያን ተላልፎ መሰጠት እየሞቱ መኖር እየጠፉ መብዛትን አስተምረውናል። በሁሉም መንገድ ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ጋር አብረው መከራውን የተቀበሉ፣ የቁርጥ ቀን ልጆች ታላቅ መልእክት አስተላልፈውልናል።
- Details
- Written by: ዲ/ን አሻግሬ አምጤ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1126
ቤተ ክርስቲያን የሰላም በር ብትሆንም በየጊዜው በልዩ ልዩ ምክንያት በተከሠተ ጦርነት ስትለበለብ ኖራለች። ጦርነት አውዳሚ መሆኑን ተረድታ ክፉዎች በጥፋት ቀጥለው ዘለዓለማዊ ቤታቸውን እንዳያጡ ትጸልያለች። ጸሎቷም በዓለም ላይ አማናዊው ሰላም ይሰፍን ዘንድ ነው። ጦርነት በተከሠተ ጊዜ ግን ተዋጊዎች በአንድ በኩል ከለላ ለማግኘት በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ብለው ለማስጠቃት ቤተ ክርስቲያንን ይጠጓታል።
ከውጭ ወራሪ ጋር የሚደረግ ጦርነት ከሆነ ቤተ ክርስቲያን እንደ አገር ለትውልድ ሥነ ልቡና መገንቢያ ተደርጋ ስለምትታሰብ በጦርነት ስትለበለብ ኖራለች። በመጀመሪያው ወረራው ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሽንፈትን ተከናንቦ የፈረጠጠው ፋሽስት ኢጣሊያ ለሁለተኛው ጊዜ አገራችንን ለመውረር ሲያስብ ለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ምክንያቱን አጥንቶ ቤተክርስቲያን መሆኗን ደረሰበት። ከጥናቱ በመነሣትም ቤተክርስቲያንን አንዷ የጥቃት ዒላማ እንድትሆን አድርጐ ክርስቲያኖችንና አብያተ ክርስቲያንን አወደመ። የአንድ እናት ልጆች በአንድ በኩል አገርን ለመታደግ በሌላ በኩል ደግሞ ለማፍረስ ከመጣው ፋሽስት ጋር በመወገን ኢትዮጵያን አወደሙ። የጦርነት ፍጻሜው እንዲህ ነው።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1113
የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ካራኪን ዳግማዊ በአርመንያና በአዘርባጃን መካከል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ምእመናንን መጎብኘታቸው ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነብቧል።
ከወራቶች በፊት በነበረው ጦርነት ምክንያት በርካታ አርመንያውያን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች አካባቢያቸውን ለቀው በአርመንያ ባሉ አህጉረ ስብከት በሚገኙ አጥቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ። ቅዱስ ፓትርያርኩም ክርስቲያኖች ተጠልለው ከሚገኙበት ቦታ በአንዱ ተገኝተው ያጽናኑ ሲሆን ተገቢው ጥበቃና ክብክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑንን ማረጋገጥ እንደቻሉ ዘገባው አመልክቷል።
የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለተፈናቃዮች የምግብ፣ የልብስና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን እያደረገች ሲሆን ተጨማሪ ርዳታ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ካለ ደግሞ ‹‹የእችሚአዳጊን ጓደኞች›› በሚለው አድራሻ በኩል ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።
- Details
- Written by: መጽሐፈ ሲራክ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1114
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ስምዐ ጽድቅ፦ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት መምጣቱ መልካም ነገር ሆኖ ሳለ ምናልባት በውጪው ሀገር ለክርስትናው መስፋፋት መከፋፈሉን እንደ በጎ ልናየው እንችል ይሆን?
መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ፦ በምንም አይነት መለያየትን እንደ መልካም ነገር ልናየው አንችልም። በተለይ የቤተ ክርስቲያን ሲሆን ደግሞ መለያየት ክፉ ነው ብዙ ጠባሳ ጥሎ ንፁሐንንም አቁስሎ ያልፋል። በነበረው መከፋፈል የተነሳ በዓለም ላይ መሥራት የሚገባንን መንፈሳዊ ሥራ ሳንሠራ ቀርተናል፤ አገልግሎቱንም ጎድተናል፤ ሕዝቡን ለመናፍቃን ገብረናል፤ ብዙ ነገር አበላሽተናል።
የወላጆች መከፋፈል ለልጆች፤ የመሪዎችም መከፋፈል ለተመሪዎች ምን ያህል ችግር መሆኑ ይታወቃል። እንግዲህ ይህንን ስናስብ መለያየትን ልንጠየፈው ያስፈልጋል። ይኽ ደግሞ አጋጥሞን አልፏል፤ በታሪክ አጋጣሚ ይህንን አስተናግደናል፤ የምንወደውን ትተን የምንጠላውን ሆነናል፤ በወቅቱ በፓለቲካም ይሁን በቅዱስ ሲኖዶስ በዘርም ይሁን በሥልጣን ተበታትነን ሳለን ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ስላገኘን ይህንን ነገር እግዚአብሔር ለበጎ አድርጎት ይሆን? ብለን እንጠይቃለን ሰዎች ነንና እንዲህም እናስባለን ደግሞ እንመለስና እንዴት በእግዚአብሔር ፊት መለያየትን ለበጎ እንላለን? የሚል ሐሳብም ይመጣል።
በሀገራችን ጥንት ቤተ ክርስቲያን ይቋቋም የነበረው ያለው ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን ሲርቃቸው፣ ወንዝ እየሞላ ሲያስቸግራቸው፣ ሕፃን ታቅፈው ለማስጠመቅ፣ ሰው ሞቶባቸው ለቀብር ሲርቃቸው፣ በአካባቢያቸው ደብር እንዲኖራቸው በሚል ቅን ሐሳብ በስምምነት ነው እንጂ ተጣልቶና ተኳርፎ ተለያይቶ የሚሆን አይደለም በውጪ ሀገር ግን ሁሉም ባይሆኑም አንዳንድ ቦታ ያሉት የመለያየት ውጤቶች ናቸው።
አሁን የጥንቱ አንድነት ተመልሷል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ ሆኗል፣ ቀደም ሲልም ልዩነቱ የጀመረው ከላይ ነበር አሁንም ከላይ ተስተካክሏል በተፈጠረው ልዩነት ስናዝን የነበርነው ካህናትና ምእመናንንም አሁን አንድ በመሆናችን ደስተኞች ነን።
Read more: “በውጪው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች ሳይሆን ተስፋፋች እላለሁ” -መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ክፍል ሁለት
- Details
- Written by: እህተ ሚካኤል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1080
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ባለፈው እትማችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ እትማችን ደግሞ ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ ትከታተሉ ዘንድ ግብዣችን ነው። የተወደደዳችሁ አንባብያን በመጀመሪያው ክፍል ‹‹ቀሲስ መልአኩ›› ተብሎ የተጻፈው የእንግዳችን ስም ‹‹ቀሲስ ንጋቱ›› መሆኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።
ስምዐ ጽድቅ፦ ሞተ የተባለው እና የተመዘገበው የጥቃቱ ሰለባ የሆነ ሰው ነው?
መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ አዎን ለምሳሌ አለማያ ላይ አንዲት እናት ሙተዋል። ቤተ ሰቦቻቸውም ጭንቅላታቸውን ተፈነካክተው እጃቸው ሁሉ ተሰባብሯል። እናትየው ባልቴት ናቸው፤ በጣም ተደብድበው ስለነበር ሆስፒታል ሲደርሱ ሞቱ። እንግዲህ በእርሳቸው ስም ፴ ሺህ ብር ቡክ ተከፍቶአል፤ ቡኩ በልጃቸው ወይም በቤተሰቡ ስም መሆን ነበረበት፤ የእርሳቸው ካሳ ለልጆች መሰጠት ነበረበት። ያው እንደሚታወቀው በሞተ ሰው ስም ሲደረግ ደግሞ ውርስ እና ተያያዥ ነገሮች ሲባሉ ብዙ ጊዜ ይፈጃል። በእርግጥ ይህ ስለተስተካከለ ችግር የለውም።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 489
በናጎሮን ካራባክህ ከአራስፅካህ ለተፈናቀሉ የአርመንያ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች “ችልድረንስ ፈንድ ፎር አርመንያ” የተባለ ግብረሠናይ ድርጅት ዓለም አቀፍ የርዳታ ጥሪ ማቅረቡን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
ለአርመናውያን ፪፻፳ ዓ.ም አስቸጋሪና እጅግ ፈታኝ ወቅት እንደነበረ ያነሣው ግብረሠናይ ድርጅቱ ፈተናው ለአራስፅካህ አርመናውያን ብቻ ሳይሆን የመላው አርመናውያን ችግር ነው ብሏል፡፡ አያይዞም “ከቅርብ ወራት በፊት በአዘርባጃንና በአርመንያ መካከል በተደረገው ጦርነት አርመናውያን ዘመዶቻቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ ቤቶቻቸውን፣ አካሎቻቸውን አጥተዋል” ሲል ድርጅቱ አስታውቆ “በርካታ ሕፃናት ወላጅ አልባ ከመሆናቸው በተጨማሪ አያሌ ቤተሰብም በድንገት ተበትኗል” ሲል ገልጧል፡፡
በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ሁሉም አርመናውያን የገንዘብና የሥነ ልቡና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ድርጅቱ አስርድቷል፡፡ በተለይ በጦርነቱ የተጎዱ አርመናውያን ሕፃናትንና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ብሔራዊ ግዴታ መሆኑንም አስተውቋል፡፡
ድርጅቱ በተለይ ካናዳ የሚኖሩ አርመናውያን በጦርነቱ ቤተሰቦቻቸው ለሞቱባቸው፣ ለቆሰሉባቸውና ለጠፉባቸው አፋጣኝ ርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡ እግዚአብሔር አርመናውያንን እንዲጠብቅና በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን እንደሚጸልይም ገልጧል፡፡
- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1371
ይድረስ ምሥጢሬን ላካፍላችሁ አዘጋጆች፤ እንደምን ሰነበታችሁ? እኔ እግአብሔር ይመስገን ደኅና ነኝ፤ ስሜ ወለተ መድኅን ይባላል ዛሬ ለዓመታት ሲያስጨንቀኝ እና ሲያሰቃየኝ የነበረ ችግሬን ሳካፍላችሁ መፍትሔ የያዘ ምላሽ ትሰጡኛላችሁ ብዬ በማመን ነው።
በወጣትነት ዕድሜ ላይ ነው የምገኘው፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ተግባቢና ተጫዋች የምትባል ዓይነት ሴት ነበርኩ። በትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ብዙ ጓደኞች ነበሩኝ፤ ብቸኛ የሆንኩበትንም ወቅት አላስታውስም። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ይህ ችግር አላጋጠመኝም። ወደ ሥራ ዓለም ገብቼ ከተለያዩ ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር ስጀምር በተለያዩ አጋጣሚ የቀርብኳቸው ሰዎች ኑሮአቸው ከጥቅም ጋር የተያያዘ መሆኑን ተረዳሁ፤ ያ ብቻም አይደለም፤ ሰዎች ሠርተው እና ለፍተው ከማግኘት ይልቅ በአቋራጭ ለመክበር እንደሚጥሩ ሳይ በመጀመሪያ ላይ ተቸግሬ ነበር፤ ሥራዬ ላይም እክል ሆኖብኝ ነበር፤ ገንዘብን ለማግኘት እና ሀብትን ለማካበት ሲሉም በሥልጣናቸው ጭምር ተጠቅመው ሠርቶ ማደር የሚፈልገውንና የሚጥረውን ሰው የሚበድሉ፤ ለሌሎች ከማዘን ይልቅ የሰዎችን ኑሮ ከሚበጠብጡ ሰዎች ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ ለመሥራት እጅጉን ተቸግሬ ነበር።
ከትምህርት ጓደኞቼ ጋር በሥራ ቦታችን መለያየት የተነሣ በመራራቄ ከሥራ ቦታም ሆነ በተለያዩ ሥፍራዎች ጓደኛ ማግኘት አልቻልኩም። ጥሩ ሰዎች ናቸው ብዬ የቀረብኳቸው እና ለጓደኝነት ይሆኑኛል ብዬ ያሰብኳቸው ሴቶች እውነተኛ ሆነው ስላላገኘኋቸው ምንም ዓይነት ማኅበራዊ ሕይወትን ከእነርሱ ጋር ማሳለፍ ተሳነኝ። ጓደኛ ማጣቴም እጅጉን ጎድቶኛል። በሥራ ወይም በግል ሕይወቴ ላይ የተለያዩ ዓይነት ስሜትን የሚጎዳ ንግግር እንዲሁም አስተያየት በመስጠት እና በመዝለፍ እኔን ለመጉዳት የሚጥሩ ሰዎችም እንዲሁ ሕይወቴን አስቸጋሪ አድርገውብኝ ነበር። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራ እና የግል ሕይወቴን የሚያስተጓጉሉ ድርጊትም ከመፈጸም ወደ ኋላ አይሉም፤ ይህ ሁኔታ አልፎም ለትዳር ያለኝን አመለካከት እስከ ማበላሸትም የደረሰበት ጊዜ ነበር። በዚህም የተነሣ በፍቅር ሕይወቴ በመጎዳቴ ትዳር ለመመሥረት ፍላጎት እስከማጣት ደርሻለሁ። በመሆኑም ከዚህ ሁሉ ችግር በኋላ ሰዎችን ርቄ ብቻዬን ለመኖር ወሰንኩ። ቤተሰቦቼም ከእኔ ጋር ስለማይኖሩ በብቸኝነት ኑሮዬን እየገፋሁ ነው። የዕረፍት ቀኔንም ሆነ ትርፍ ጊዜ በማገኝበት ወቀትም ብቻዬን አሳልፋለሁ። ነገር ግን ማንም ቢሆን ሰው ያስፈልገዋልና ብቸኝነት እየጎዳኝ ነው። ስለዚህ ምን ትመክሩኛላችሁ?
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1722
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ከአባታቸው ከመምህር ቀሲስ ገብረ ሕይወት ወልደ ሐዋርያት እና ከእናታቸው ወይዘሮ ብርነሽ ቸኮል በቀድሞ የወሎ ክፍለ ሀገር ዋግ ሕምራ አውራጃ ተወለዱ።
ብፁዕነታቸው በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ተዘዋውረው የቤተክርስቲያንን ትምህርት ጠንቅቀው ተምረዋል። ወደ ተለያዩ ውጭ ሀገራት በመሄድም የተለያዩ ትምህርቶችን ተምረው ያተጠናቀቁ ሲሆን በሩሲያ ሞስኮብ የቀድሞው ፒተርስበርግ በኋላ ሌኒንግራድ ዩኒቨርስቲ በሃይማኖተ አበው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። የማስተርስ ዲግሪያቸውንም እንዲሁ በነገረ ክርስቶስ ትምህርት ያገኙ ሲሆን ዶክተሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በነገረ ሥጋዌ አግኝተዋል።
ቀጥሎም ወደ ሰሜን አሜሪካ በመሔድ በፕሪስተን ዩኒቨርስቲ በማስተር ኦፍ ቲዎሎጂ ዲግሪ ተቀብለዋል። ብፁዕነታቸው በምንኵስና የቅድስና ሕይወት ጉዞ የጀመሩትና ለታላቁ ማዕረግ እንዲደርሱ የእግዚአብሔር ጥሪ የደረሳቸው በ፲፱፻፷፩ ዓ.ም ሲሆን በዚህ ዓመት ወደ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳም በመሔድ መንኰሰዋል። በመቀጠልም መስከረም ፮ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ዘመነ ፕትርክና ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅስና እና ቁምስናን ተቀብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራዶኦ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቀጥሎም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የካህናት አስተዳደር መምሪያና መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ ጥር ፬ ቀን ፲፱፻፸፪ ዓ/ም በቅዱስ
ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ዶር አባ ኢያሱ ይባሉ የነበሩት ብፁዕ አባ ገብርኤል ተብለው የመንፈሳዊ ኮሌጅ ኤጲስ ቆጶስ (ዲን)፤ የድሬዳዋ እና አካባቢው ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሾሙ። በድሬዳዋ ሀገረ ሰብከትም ለአንድ ዓመት ያህል ከአገለገሉ በኋላ በ ፲፱፻፸፫ ዓ/ም የኤርትራ ክፍለ ሀገር ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለተከታታይ ሦስት ዓመታት አገልግለዋል።
ብፁዕነታቸው በአጠቃላይ ቤተክርስቲያንን በተለያዩ የአገልገሎት ዘርፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በትጋት ያገለግሉ ሲሆን። ከ፳፻፫ ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሲዳማ፣ ጌድኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞን ሀገረ ስብከት ተልከው እስከ ጥቅምት ፳፻፲፫ ዓ.ም ከላይ በተጠቀሱት። አህጉረ ሰብክት ተዛውረው በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ይገኙ ነበር።
ብፁዕነታቸው በጸበልና በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ኅዳር ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም ከቀኑ ፭ ሰዓት በተወለዱ በ፹ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም ቅዱስ ፓትርያሪኩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊዎች እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ኅዳር ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም ከጠዋቱ በ፬ በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
- Details
- Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1064
አንድ ምሽት በምሥራቅ የኦሮሚያ አካባቢ ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከቶች ስላሉ ክርስቲያኖች መከራና የስጋት ሕይወት እያሰብኩ ሳለ አንድ ሐሳብ መጣልኝ፤ በእነዚህ ሀገረ ስብከቶች ለአደጋ የተጋለጡ ስንት አብያተ ክርስቲያናት ይኖሩ ይሆን? ማን ማን ይባሉ ይሆን? ምን ያህልስ ምእመናንና ካህናት ይኖሩ ይሆን? አልኩ።
ወዲያውኑ ስልኬን ከፍቼ የኢንተርኔቱን የመረጃ መስጫ መረብ ተቀላቀልኩ። በተለመደው መንገድ በጎግል ልፈልግ ብዬ የሀገረ ስብከት ስምና የቤተ ክርስቲያን ቃላት ዓይነት እያማረጥኩ አሰሳዬን ቀጠልኩ። ነገር ግን አልፎ አልፎ መከራ ስለደረሰባቸው አንዳንድ አጥቢያዎች በግርድፉ ከሚጠቅሱ የዜና ዘገባዎች ውጪ መሠረታዊ መረጃ የያዘ ገጽ ድርም ሆነ የጥናት ጽሑፍ ማግኘት አልቻልኩም። ሀገረ ስብከቶቹ ራሳቸውን የሚገልጹበት፣ አጥቢያዎች ስለአሉበት ሁኔታ የሚነግሩበት አንድም የማኅበራዊ ሚዲያ ሽፋን የለም። ለምን? ከዚያ አልፌ በጠቅላይ ቤተ ክህንት ደረጃ እነዚህን መሠረታዊ መረጃዎች በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርግ ገጸ ድር ወይም ጥናት ላገኝ አልቻልኩም።
ወዳጆቼ! የተቀነሰብንን፣ ያጣነውን፣ የተቸገርንበትን ነገር መጠኑን የምናውቀው የነበረንን በውል ስናውቅ ነው።
- Details
- Written by: ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 3075
የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? አሜን፤ የአባቶቻችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!
ልጆች! ዛሬ የብዙ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን መንፈሳዊ አባት ስለሆኑት ጻድቁ አባታችን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ የቅዱሳንን ታሪክ በማንበብ ለቅዱሳን ከተሰጠው ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆን ይቻላልና በጥሞና ታነቡ ዘንድ እንጋብዛችኋለን!
የአቡነ ኢየሱስ ሞዐ አባታቸው ዘክርስቶስ እናታቸው ደግሞ እግዚእ ክብራ ይባላሉ። በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። አቡነ ኢየሱስ ሞዓ በጐንደር ክፍለ ሀገር ዳኅና ገብርኤል በሚባል ቦታ ግንቦት ፳፮ በ፲፪፻፲ ዓ.ም ተወለዱ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በአባታቸው ቤት እና በአካባቢያቸው ጥበብን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን እና መልካም ተግባርን ሁሉ እየፈጸሙ አደጉ። በቅድስና በንጽሕና ሆነው በቤተሰቦቻቸው ቤት እስከ ሠላሳ ዓመት ኖሩ።
አንድ ቀን ስሙ ገብርኤል የተባለ የእግዚአብሔር መልአክ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ በሌሊት ታያቸው። ሦስት ጊዜም ጠራቸውና ‹‹ከአባትህ ቤት ውጣ፤ ወደ ታላቁ አባት ወደ አባ ዮሐኒ መኖሪያ ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ሂድ፤ ደግ አገልጋይ ትሆናለህም›› አላቸው። ቃሉንም ተቀበሉትና በሠላሳ ዓመታቸው በ፲፪፻፵ ዓ.ም. ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገብተው ከአባ ዮሐኒ ጋር ሰባት ዓመት ኖሩ።
- Details
- Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1635
ይሄ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚባል ጉድ የስንቱን ጠባይ፣ፍላጎትና ገበና ገለጠው?! ሰው እንዴት ከልብሱ አልፎ ገላውን፣ ከገላው አልፎ ነፍሱን አራቁቶ ያሳያል?! ጎበዞች ሆይ! ማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ክብራቸው በነውራቸው እንዲሆን የመፍቀድ ልምምዳቸው ማሳያ አደባባይ እየሆነ መምጣቱን እንደ እኔ አስተውላችሁ ይሆን! ሞራል፣ ሥነ ምግባር፣ ሕግ በይፋ ሲሰባበሩ የሚታይብት የፍልሚያ ሜዳ አይታያችሁም?
ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሳየን የሁሉንም ገመና ሆኗል፤ የሴቱን ብቻ አይደለም፤ የወንዱንም ነው፤ የደቂቁን ብቻ አይደለም የልሂቁንም ነው፤ የኢ-አማኒውን ብቻ አይደለም የምእመኑንም ነው፤ ያልተማረውን ብቻ አይደለም የተማረውንም ነው፡፡ እረ ስንቱን!
በየቤቱ ቤተሰብ የቻለው ጉድ አሁን የሁሉም ሕዝብ ሆኖ ማኅበረሰብ እንዲሸከመው ሆኗል፡፡ አሁን በቤተሰብህ ብቻ ሳይሆን በጎረቤትህ አመል ትታወካለህ፡፡
ይሄ ጉድ ሄዶ ሄዶ ከቤተክርስቲያን ቄሱን፣ ዲያቆኑን፤ ከገዳም መነኮሳቱን መንካቱ ደግሞ ‹‹የቤቴው ጉድ›› እንድል አስገድዶኛል፡፡ የዛሬም ትዝብቴ ከብዙ ኃላፊነት ተሰምቷቸው የእግዚአብሔርን አደራ ጠብቀው ቀን ከሌት ስለሕዝባቸው በመንፈስ ሲጋደሉ ከሚኖሩ ካህናት ተርታ ወጥተው ‹‹አክቲቪስት›› ስለሆኑ ጥቂት ካህናት ነው፡፡ ሌት ከቀን በማኅበራዊ ሚዲያ ዕድሎቻቸው መልካሙን ዜና ከሚያወሩና ከሚነግሩን ብርቱ አገልጋይ መምህራን ይልቅ ጥቂት ‹‹አክቲቪስት›› ስለተባሉ አገልጋዮች ነው፡፡