- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1024
በቤተክርስቲያንና ‹‹በኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ›› መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ልዩነት በእርቀ ሰላም መፍታቱን አስመልክቶ ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ‹‹ጽርሐ ተዋሕዶ›› አዳራሽ የጋራ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” ሰብሳቢ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንንና የሽማግሌ ቡድኑ ሰብሳቢ ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ መግለጫውን በጋራ የሰጡ ሲሆን በኦሮምያ ክልል ያለችው ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መዳከም ያሳሰባቸው ወገኖች ችግሩን ለመፍታት ሲሉ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነትን›› ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደቆዩ በመግለጫው ተነስቷል፡፡
“የኦሮምያ ቤተ ክህነት” ይዟቸው የተነሳው የአገልግሎት ችግሮች በአብዛኞቹ አባቶች፣ ሊቃውንትና ምእመናን የታመነባቸው ቢሆንም ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነትን›› ማቋቋም መፍትሔ ይሆናል የሚለው አሳብ ግን በቤተ ክርስቲያንና በአደራጅ ኮሚቴው መካከል ከፍተኛ ልዩነት ፈጥሮ እንደቆየ ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ልዩነቱን ለማጥበብና በመካከላቸው ያለውን ችግር ለመፍታት በአደራጅ ኮሚቴውና በሽማግሌዎቹ መካከል ላለፉት ስድስት ወራቶች ውይይቶች ሲካሄዱ እንደነበር በመግለጫው የተመለከተ ሲሆን ለስኬታማነቱም የሽማግሌ ቡድኑ “የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ” አመራሮችን፣ ቋሚ ሲኖዶስንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን እንዳነጋገረ ተገልጿል፡፡
በቀጣይም በኦሮምያ ክልል ያጋጠመውን የአገለግሎት መዳከም ለማሻሻል በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር የሚቋቋም አካል ተጠናክሮ በአንድነት መሥራት የሚችልበትን ሂደት መፍጠር የተሻለ መሆኑ እንደታመነበት በመግለጫው ተነስቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረትም በኦሮምኛ ቋንቋ የሚሰጠውን አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ባለድረሻ አካላት አንድ ሆነው እንዲሠሩም ጥሪ ቀርቧል፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1067
በአሜሪካ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ኅብረት በኦርቶዶክሳዊ አንድነትና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተው ውሳኔ ማሳለፋቸውን ኦርቶዶክስ ኦግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን መንፈሳዊ ፍላጎትን ለማሟላት ሃይማኖታዊ ሥርዓትና አገልግሎት እንዲፈጸም ለማድረግ ኅብረቱ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ውሳኔውም በጋራ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡
የአሜሪካ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ኅብረት ም/ኃላፊ ሜትርፓሊቲያን ዮሴፍ ፳፻፲፫ ዓ.ም ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በትክክለኛ መንፈሳዊ ሕይወትና መስመር የሚገኙበት ማድረግና የኅብረቱ የጋራ እቅድ የሚፈጸምበት ዓመት ይሆናል በማለት እንደተናገሩ ዘገባው አመልክቶ ‹‹ወጣቶች የእኛ የዛሬና የወደፊቶች ናቸው›› ሲሉ አክለው እንደተናገሩም አስረድቷል፡፡
የጳጳሳቱ ኅብረት ባካሄደው ጉባኤ የተመሠረቱ አዳዲስ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበራት ሲኖሩ እነዚህም የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበርና የኦርቶዶክሳውያን በጎ አድራጎት ማኅበር ናቸው፡፡ እነዚህ ማኅበራት በልዩ ልዩ ኦርቶዶክሳዊ የአገልግሎት ዘርፍ በ፳፻፲፫ዓ.ም ወደ ሥራ እንደሚገቡም ከዘገባው ለመርዳት ተችሏል፡፡
ማኅበራቱ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን መንፈሳዊ ሕይወት የመቅረጽ ሥራ የሚያከናውን ሲሆን ያለውን አቅምና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም የሚሠራ ይሆናል ተብሏል፡፡ የጳጳሳት ኅብረቱ በማኅበራቱ ቆይታ ላይ የጊዜ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን ይህም የማኅበራቱን ጥልቀትና ተቀባይነት ለማረጋግጥ ይጠቅማል ሲል ዘገባው አስረድቷል፡፡ ዓመታዊ ኦርቶዶክሳዊ ጉባኤ እንዲሁም የወጣቶች ሠራተኛ ጉባኤ በዚሁ ዓመት እንዲካሄድ መወሰኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1176
የ፳፻፲፫ ዓ.ም ፴፱ኛ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገሪቱ ላይ የመጣውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ እንዲሁም በየጊዜው ሲከሰቱ የነበሩና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ግኑኝነት የሌላቸውን ሁነቶች መነሻ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጥቃት ዒላማ ሆና መቆየቷን አስረድቷል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሀገረ ስብከቶች በምእመናን ሕይወት እና ንብረት ላይ ፣ በአገልጋይ ካህናት እና በቤተ ክርስቲያን የደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት ታሪክ የማይረሳ መሆኑን ገልጿል፡፡
በተለይም በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰው ዘርፈ ብዙ ጥቃት እና ውድመት ፣ በንብረት እና በሕይወት ላይ የደረሰው ጥፋት ከዚህም ባሻገር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ስትጠቀምባቸው የነበረውን የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ንጥቂያ ብሎም በዓላቱ እንዳይከበሩ የተፈጠሩ አሉታዊ ተጽእኖዎች ብዙዎችን ሲያነጋግር የሰነበተ አሁንም ድረስ እያነጋገረ ያለ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በተከታይ ምእመናንዋ ላይ እየተካሄደ ያለው የጥፋት ዘመቻ በአካራሪ ኃይል ፣ በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ሀገርን እንደ ሀገር እንድትቀጥል ትልቁን ድርሻ የያዘችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማጥፋት ዋና ተልእኮዋቸው አድርገው በተነሱ አንዳንድ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት አማካይነት አንዳንዴ በድብቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግልጽ ሲካሄድ መቆየቱ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ፣ ካህናት እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጉዳዩን ከሥር ከሥር እየተከታተሉ ግድያውን፣ የንብረት ውድመቱን ፣ ዝርፊያውን እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋት ዘመቻ ሲቃወሙ ፣ ሲያወግዙ እንዲሁም ሀገሪቱን ለሚመራው የበላይ አካል በመረጃ የተደገፈ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተቃጣ ያለው የጥፋት ዘመቻ ከመቀነስ ይልቅ እየባሰ መምጣቱን ከዳር ሀገር ወደ መሀል መግባቱ እታየ ነው፡፡
ይህ በተቀናጀ መልኩ እየተካሄደ ያለ የጥፋት ተልእኮ በተለይም ወቅት ጠብቆ፣ ምክንያት ፈልጎ፣ አሳቻ ጊዜን ተገን አድርጎ በኦርቶዶክሳውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘመቻ ለመከላከል ፣ ለተጎዱት ለመድረስ ብዙዎች በግልም በማኅበርም ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲረባረቡ ቆይተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜም የተቃውሞ መግለጫ ፣ማሳሰቢያ ፣ ሲሰጥ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
ተጎጅዎችን ምስክር ያደረገ ጥፋት እና የጉዳት ጥልቀት በተለያዩ ጊዜያት ወደ መንግሥት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደርሰዋል፣ በየሀገረ ስብከቱ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት የጥፋት ዘመቻውን ስፋት፣ ከጥፋት ዘመቻው ጀርባ ያሉትን ስውር አንጀንዳዎች እና እቅዶች፣እንዲሁም በዚህ ሁሉ ጥፋቶች ውስጥ መንግሥት ያሳየውን ቸልተኝት ጭምር በግልጽ ተችተዋል፡፡
ይህ እየተጠራቀመ፣ በላይ በላይ እየተደራረበ ፣ የመጣው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም ብሎም የማጥፋት ዘመቻ ከቃል ፣ ከውግዘት ፣ከማሳሰቢያ ፣ ከማስጠንቀቂያ እና ከቃላዊ ተቃውሞ ያለፈ እና መሬት ላይ የወረደ ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ተደራጅተው ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው የሚለው የቅዱስ ፓትርያርኩ የ፴፱ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መክፈቻ መልእክት መዋቅሩን ጠብቆ በተግባር የተገለጠ የተደራጀ ኃይል ኑሮት ከመልእክትነት ያለፈ ቁም ነገር ሊኖረው ይገባል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር ባሉ ተቋማት በተለያየ ጊዜ የወጡ የአቋም መግለጫዎች ፣የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ሊያስከብሩ ይገባል የሚሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያዎች ከወረቀት ባለፈ መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከደረሱት ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ማኅበራት አባቶች እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት የአቋም መግለጫዎች መውጣታቸው ፣የተለያዩ ማሳሰቢያዎች መተላለፋቸው ይታወቃል ሆኖም ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተቃጣ ያለውን ጠንካራ የጥፋት ዱላ መመከት አልተቻለም፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የአቋም መግለጫዎቹ ፣ ማስጠንቀቂያዎቹና ማሳሰቢያዎቹ በተላለፉ ማግስት የጥፋት ዘመቻው በእጥፍ መጨመሩ ነው፡፡
በመሆኑም ሁሉም የሚመለከተው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አካል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ ምእመናኑ ድረስ በ፴፱ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለተላለፉት ውሳኔዎች ተግባራዊነት የበኩሉን አስተዋጸኦ ሊያደርግ ይገባል፡፡ በዚህ ወቅት በኅብረት መቆም ፣ በተለይም የውስጥ ልዩነትን አስወግዶ ባንድ ሐሳብ በመቆም ቤተ ክርስቲያንን በዘላቂነት ከጥቃት የመከላከል ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡
- Details
- Written by: በእንድርያስ ስንታየሁ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1240
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁ? መልካም፤ እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን፡፡
ልጆች የዛሬ ትምህርታችን ስለጸሎት ነው፤ በመጀመሪያም የቃሉን ትርጉም እንመልከት፡፡
ጸሎት ‹‹ጸለየ›› ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ የቃሉ ፍችም ለመነ፣ተማጸነ ማለት ሲሆን ጸሎት ማለት ልመና ወይንም መማጸን ማለት ነው፤ ጸሎት የሚቀርበው ለእግዚአብሔር ወይም ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡
ጸሎት ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ከብዙዎቹም ውስጥ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እንመለከታለን።
1. እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጠቅመናል፤
2. በጸሎት በደላችንን እና ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር እንናዘዛለን (እንናገራለን) ይቅርታውንም እንለምናለን፤
3. ከእግዚአብሔር ዘንድ የፈለግነውንና የጎደለንን ለማግኘትም ያስችለናል፤
4. የእመቤታችንን እና የቅዱሳንን አማላጅነት ለመለመን እንጸልያለን
5. መንፈሳዊ ኃይል እንድናገኝ ያስችለናል፡፡
እንግዲህ ጸሎት ይህን ያህል ጥቅም እንዳሉት ከተረዳን አቡነ ዘበሰማያት (አባታችን ሆይ) በግእዝና በአማርኛ እንጸልያለን፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
አቡነ ዘበሰማያት በግእዝ
፩. አቡነ ዘበሰማያት! ይትቀደስ ስምከ፤ ትምጻእ መንግሥትከ፡፡ ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር
፪. ሲሳየነ ዘለለ ዕለትነ ሀበነ ዮም
፫. ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንህነኒ ንኅድግ ለዘአበሰ ለነ፤
፬. ኢታብኣነ እግዚኦ ውስተ መንሱት፡፡ አላ አድኅነነ፥ ወባልሓነ እምኵሉ እኩይ
፭.እስመ ዚኣከ ይእቲ መንግሥት ኃይል፥ ወስብሐት፤ ለዓለመ ዓለም፡፡
በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ
፩. በሰላመ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ ድንግል በሕሊናኪ፣ ወድንግል በሥጋኪ
፪. እመ እግዚአብሔር ጸባዖት ሰላም ለኪ
፫.ብሩክት አንቲ እምአንስት ወብሩክ፤ ፍሬ ከርሥኪ፤
፬.ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ
፭. ሰአሊ ወጸልዪ ምሕረተ ኀበ ፍቁር ወልድኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ይሥረይ ለነ ኃጣውኢነ።
አባታችን ሆይ በአማርኛ
1. አባታችን ሆይ፥ በሰማይ የምትኖር፥ ስምህ ይቀደስ፥ መንግሥትህ ትምጣ፥ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ፣ እንዲሁም በምድር ይሁን፣
2. የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ፥
3. በደላችንን ይቅር በለን፥ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥
4. አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን፥ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ፥
5. መንግሥት ያንተ ናትና፣ ኃይል፥ ክብር፥ ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን!
በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ
1. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ፥ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን። በሐሳብሽ ድንግል ነሽ፥ በሥጋሽም ድንግል ነሽ።
2. የአሸናፊ የእግዚአብሔር እናት ሆይ ሰላምታ ላንቺ ይገባሻል።
3. ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፥ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡
4. ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ፣ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና።
5. ከተወደደው ልጅሽ ከጌታንችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታን ለምኝልን፤ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ለዘለዓለሙ አሜን!
ልጆች! እስከ ዛሬ ጸሎት ያልጀመራችሁ ካላችሁ ዛሬውኑ ጀምራችሁ ዘወትር ጥዋት ከእንቅልፋችሁ ስትነሡ፣ ምግብ ከመመገባችሁ በፊትና ተመግባችሁ ስትጨርሱ እንዲሁም ከመኝታ በፊት ጸሎት አድርጉ፡፡ ጸሎት የጀመራችሁ ሕፃናት ደግሞ ሳታቋርጡ ዘወትር ጸልዩ! ይህንን ስታደርጉ አምላካችን እግዚአብሔር ይወዳችኋል፤ ከበሽታም ሁሉ ይጠብቃችኋል እሺ!
በመጨረሻም በቤተ ክርስቲያን ስትጸልዩ እንዴት መጸለይ እንዳለባችሁ በሚቀጥለው ትምህርታችን እናቀርብላችኋለን፤ እስኪዚያው መልካሙንና የተወደደውን ነገር ሁሉ እንመኝላችኋለን፤ ደኅና ሰንብቱ!
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1311
ቤተ ክርስቲያንን ለከፋ አደጋ ያጋለጣት የአክራሪዎችና የተቃራኒዎች እንቅስቃሴ መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መክፈቻ ዕለት ባስተላለፉት መልእክት ገለጡ፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ አሠራርም በክፍተት የተሞላ መሆኑ ከተቃራኒና ከአክራሪ አካላት ጥቃት ባልተናነሰ ሁኔታ አገልግሎትን እያስተጓጎለ እንደሆነ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው በቤተ ክርስቲያን የሚታዩ የተለያዩ የአሠራር ጉድለቶች ማለትም የአስተዳደር፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ሊስተካከሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ ያልተስተካከለ አሠራር ምእመናንን እያሳዘነ እንደሆነ ያስታወቁት ቅዱስነታቸው ‹‹ያልተስተካከሉ አሠራሮችንና ሌሎች ችግሮችን ጭምር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል ዕውቀቱ፣ልምዱና ችሎታው ያላቸው ባለሙያዎች ተመድበው በጥናት ላይ የተመሠረተና መሪ እቅድ ያለው አሠራርን መዘርጋት አስፈላጊ ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በሰላሣ ዘጠነኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በተገኘው መረጃ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ከባድ ፈተና ላይ መሆኗን ቅዱስነታቸው አንስተው ሁሉም የጥፋት ድርጊት እንዲቆም ሁነኛ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘውም የተከፈለው ዋጋ ሁሉ ተከፍሎ ያለአንዳች ግጭትና ደም መፍሰስ ሁሉም ነገር ወደ ዕርቅ፣ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ መሠራት አለበት ካሉ በኋላ ሁሉም ነገር የውይይት ጊዜና ትሥግስት ከታከለበት እየዋለ እያደረ መልካም ይሆናል ብለዋል፡፡
- Details
- Written by: የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1207
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
-ብፁዕ አቡነ ያሬድ
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
-ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
-ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
-የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የየመመሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
-የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ልዩ ልዩ ኃላፊዎች፣ የገደማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
- በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት የመጣችሁ ሥራ አስኪያጆች፣
-በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፍ ተወክላችሁ በዚህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ የተገኛችሁ ክቡራንና በአጠቃላይ፤
-ሁሉንም ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን መከራውንና ፈተናውን አስችሎ በዚህ ታላቅ ጉባኤ ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
‹‹ወይኩን ቅኑተ ሐቈክው ወኅተው መኃትቂክሙ፤ ወገባችሁ የታጠቀ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን፡፡›› (ሉቃ.12፡35)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረውና ያስተማረው ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ትምህርቱ ለጊዜው አጠገቡ ለነበሩት ሐዋርያት የተነገረ ቢሆንም ፍጻሜው እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሡ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንደሆነም እናውቃለን፡፡ ከነሱ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በየደረጃው በኃላፊነት የምንገኝ ደቀ መዛሙርትም ቃሉ በቀትታ እንመሚመለከተን አንዘነጋውም፡፡
በመሆኑም ከዚህ እውነታ ተነሥተን፣ ጌታችን ‹‹ወገባችሁ የታጠቀ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን›› ሲል እኛን ያዘዘበትና ያስተማረበት ምክንያት ምን ይሆን? የሚለውን ጥያቄ አንሥተን ማየት ከሁላችንም ይጠባቃል፤ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የትጥቅ ነገር የሚነሣው ተቃራኒ ኃይል ራስን ወይም ወገንን ለማጥቃት እንደተዘጋጀ ሲታወቅ ነው፤ መብራትን ማብራት የሚያስፈልገው ጨለማ መኖሩ ሲታወቅ ነው፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አፅራር ምንጊዜም የማይተኙ መሆናቸውን በአምላክነቱ ኃይል የሚያውቅ እግዚአብሔር አምላካችን ሁሌ ወገባችንን ታጥቀን መንጋውን እንድንጠብቅ አዞናል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብርሃናዊት፣ ሰማያዊትና ዘለላለማዊት ብትሆንም ለጊዜው ያለችው ጠላት በብዛት ባለበትና በጨላማው ዓለም ውስጥ ነውና በጠላት እንዳትጠቃ በጨለማውም እንዳትዋጥ ሁልጊዜ መብራት እንድናበራላት ታዘናል፤ ይህ የእኛ የክርስቲኖች ቀዋሚና መደበኛ ሥራችን ነው፡፡
-ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
-ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ካለው መከራ አንጻር ከምንም ጊዜ በላይ ታጥቀን ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠልና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ በአንድነት የምንቆምበት ነው፤
ለሦስት ሺሕ ዘመናት ሀገርን የገነባችና የጠበቀች ሁሉንም በእኩልነት ያስተናገደች በማንም ላይ ግፍን ያልፈጸመች ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ከገጸ ምድር እናጥፋሽ የሚሉ በምሥራቅም በምዕራብም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል፤ ፍትሕም ይገኝ ይሆናል እያልን በተስፋ ብንጠባበቅም ሲሆን አናይም፤ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገሩ እየተባባሰ፣ ክርስቲያን ልጆቻችንም ለተደጋጋሚ ጥቃት እየተዳረጉ በክርስቲያንነታቸውብቻ የግፍ ግፍ እየተፈጻመባቸው ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ጊዜያት ባደረገችው ጥሪ ከልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎችና ከሕዝብ ክርስቲያኑ ለተጎዱ ምእመናን የተወሰኑ ድጋፍ ለማድረግ ቢሞከርም ከችግሩ ስፋት የተነሣ የሚያረካ አልሆነም፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
አበው ሲናገሩ ‹‹ከራስ በላይ ነፋስ›› እንደሚሉት ቤተ ክርስቲያናችን እየገጠማት ያለውን ችግር ለመቋቋም ልጆችዋን አስተባብራና አደራጅታ ራስዋን በራስዋ ወደመጠበቅ አማራጭ ካልተሻገረች ዕጣ ፈንታዋ እጅግ አስጊ እየሆነ መጥቶአል፤ ክርስቲያን ልጆቻችን ተሸማቅቀው፣ ነጻነታቸው ተገፎ፣ በሀገራቸውና በወገናቸው መካከል የመኖርና ሃይማኖታቸውን የመከተል መብት አጥተው ባለቡት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቅን ነው ማለት አይቻልም፡፡
ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያንን የመጠበቅና የማጽናናት ኃላፊነት ከሁሉ በፊት በቅደስ ሲኖዶስ ጫንቃ ላይ ያረፈ እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚዘንበውን መከራ ለመግታት ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉባኤ ተገቢውን መፍትሔ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው አባላት፤
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው ሁከት፣ ለዘመናት ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የአንበጣ መንጋና ልዩ ልዩ መቅሠፍት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ አንድ ላይ ሆነን በመቆም ሕዝበ ክርስቲያን በመጠበቅ ፈንታ ሌላ ተቀጥላና የቤተ ክርስቲያንን ዓቅም በመከፋፈል ለማዳከም በውስጣችን የሚደረጉ ሤራዎችም ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ጥንካሬ ከባድ ዕንቅፋቶች እየሆኑ መምጣታቸው ሌላ የጥፋት ገጽታ ሆኖ እየታየ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እንደዚህ ያለው ድርጊት ለዘመናት ቤተ ክርስቲያናችንን ሲፈታተኑ የነበሩ የውጭ ኃይሎች በረቀቀ ስልትና በእጅ አዙር ቤተ ክርስቲያናችንን ሊያፈራርሱ የጠነሰሱት ተልእኮ እንጂ ላይ ላዩ አጥባቂ የኦርቶዶክስ ተከታይ መሳይ ውስጡ ግን ኦርቶዶክስን በመከፋፈል ማዳከምና ማፍረስ የሆነ ድርጊት የንጹሐን ኦርቶዶክሳዊያን ተግባር ይሆናል ብለን አናምንም፤ ይህንን ደባ ሁላችንም ልናጤነው ይገባል፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የተፈጸመው ሕገ ወጥና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነ የኤጲስ ቆጳሳት ሢመት ይገኝበታል፡፡ እንደዚህ ያለ ድርጊት የሁለት ሺሕ ዘመን ሐዋርያዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባላት በቤተ ክርስቲያናችን ቀርቶ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ተደርጎ የማያውቅ ድፍረትና ስሕተት ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ድርጊት መነሻ የሆኑት ምክንያቶችና የምክንያቶ ሰለባ የሆኑ፣ እንደዚሁም ሳይላኩና ሥልጣኑ ሳይኖራቸው ዳግም ጥምቀትን ዳግም ክህነተን በማወጅ ለዚህ አደጋ መከሠት ምክንያት የሆኑ ሁሉ በማያዳግም ሁኔታ ይህ ጉባኤ የማስቆሚያ መፍትሔ እንዲያበጅላቸው በዚህ አጋጣሚ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ዛሬ በብዙ መልኩ እንግልት ላይ ወድቀው ማየት የተለመደ ሆኗል፤ ብዙ ወጣት ልጆች ለእንጀራ ፍላጋ ሲሉ ሃይማኖታቸው ወደማይወደድበት ሰብአዊ መብታቸው ወደማይከበርበት፣ የንብረትም ሆነ የሕይወት ዋስትና ወደሌለበት ሀገር በመሰደድ የምድር ሲኦል እየለበለባቸው እንደሆነ እያየን ነው፤ ይህንን እየተመለከትን ተኝተን የምናድር ኢትዮጵያውያን ካለን ክርስቲያንነቱም ሰብአዊነቱንም ዘንግተዋል የሚያሰኝ ነው፤ ስለሆነም ልጆቻችን በባዕድ ሀገር ራቁታቸው እንደቅጠል እየረገፉ ከማየት የበለጠ (የከፋ) አንገትን የሚያስደፋ ውርደት ስለሌለ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቅዋማት፣ የኢፌድሪ መንግሥትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገበውን ሁሉ በማድረግ ልጆች ወደ ሀገራቸውና ወደ ቤተሰቦቻቸው በአስቸኳይ እንዲመለሱ ያደርጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ድንጽዋን ከፍ አድርጋ ማሰማት አለባት፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
የሰው ልጆች በተፈጥሮ ምግብና መጠጥ ልብስና መጠለያ እንደሚሻ ሁሉ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የእኩልነት፣ የመብትና የፍትሕ ፍላጎቱም የላቀ ነው፤ እነዚህ ፍላጎቶቹን ባጣ ጊዜ ያላስፈላጊ ሁከትና ግጭት ይፈጠራሉ፤ በዓለማችንም በሀገራችን የሚታዩ አለመግባባቶች ይብዛም ይነስ ከዚህ የሚመነጩ ከመሆን አያልፍም፤ እነዚህ ነገሮች በተቻለ መጠን ካልተከበሩ ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆን እያየን ነው፤ በመሆኑም በሀገራችን ያለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ያልሆነ መልክ እንዳይዝ መንግሥታችንና የሀገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወንድማማቾች እንደመሆናቸው መጠን ምንም ልዩነት ሳይኖር በክብ ጠረጴዛ ሆነው በመመካከር ችግሮችን ሁሉ እንዲፈቱ እንጂ ወደ አስፈላጊ ሁኔታ እንዳይገቡ ቤተ ክርስቲያናችን በገለልተኝነትና በእናትነት መንፈስ ማገዝ አለባት፤ ማስታረቅም ማስተማርም አለባት፤ ሁሉም ነገር በሰላምና በውይይት ብቻ እንጂ ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ የሚደረግ አማራጭ ከጉዳት በቀር ውጤት አናገኝበትም፤ ከዚህ ጎን ለጎንም ፍትሕና ርትዕ እንዲሰፍን፣ ፍትሕ የተነፈጋቸው ወገኖች ካሉ ፍትሕ እንዲያገኙ ቤተ ክርስቲያን በማእከል ሆኖ የመምከር ሥራ መሥራት አለባት፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
ከዚህ በላይ የጠቃቀስናቸው ችግሮች በሀገራችን ሥር እየሰደዱ የመጡበት ምክንያት በርከት ያለ ቢሆንም የድህነት ጉዳይ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ አያጠራጥርም፤ ወጣት ልጆቻችን ሥራማ ዳቦ ባጡ ቁጥር ሌላውን አማራጭ በመከተል ሲታክቱ እነሆ በጣም በርካታ የሆኑ ዓመታት ተቈጠሩ፤ ስያሜውና አቀራረቡ ቢለያይም ከሕገ ንጉሣዊ ሥርዓት ምክተም ምግሥት ጀምሮ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፀረ ድህነት የሚል አንድምታ ይዘው የተደረጉ ናቸው፤ ሆኖም ይቀረፋል የተባለው ድህነት ባላመቀረፉ፣ በዚያም ላይ ሌሎች ነገሮች በመካከሉ እየተሰነቀሩ ጉዞአችንን የኋልዮሽ አድርገውታል፡፡
ስለሆነም ድህነትን በዕድገት በመቀየር ረገድ ቤተ ክርስቲያን በልማቱ፣ በድህነት ማጥፋቱና በሰላም ማረጋገጡ ዙሪያ በርትታ መሥራት ይጠበቅባታል፤ ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመውም ሕዝቡ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በአንዱ ወጥ አደረጃጀት ተሰብስቦ አረጋዊያንን በመጦር፣ ሕፃናትን በማስተማርናበመንከባከብ፣የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋት፣ ለወጣቱ ትውልድ ሥራ በመፍጠርና የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነ ይታወቃል፤ ከዚህ አንጻር ሰበካ ጉባኤ ከተቋቋመበት ዘመን አንሥቶ የተገኘው ዕድገት የማይናቅ ቢሆንም መጓዝ የሚገባውን ያህል እንዳልገተጓዘ፣ ያለውም ሀብት በአግባቡ እንዳልተያዘ የአደባባይ ምሥጢር ነው፤ ከዚህም ሌላ ሌሎች ደባል ቡድኖች በየአካባባው ሲፈጠሩ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ለምጣኔ ሀብት መባከን ያለው አደጋ ሳይጤን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ፈቃድ እየተሰጠን በየፊናው ያሰማራቸውና ሁሉ በስመ ቤተ ክርስቲያን እየተሰበሰቡና ገንዘብ እየሰበሰቡ በርከት ያለ የምእመናን ሀብት እንደሚባክን መረጃዎች አሉ፤ ይህም የሚከናውነውን በሀገር ውስጥና በውጭ ጭምር ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስና ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን ድርጊት አርሞና አስተካክሎ መልክ ካላስያዘ በቀር ጉዳቱ የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን አንድነትዋንና ህልውናዋንም ጭምር ከባድ አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል፤ በታሪክም ተወቃሽነትን ያስከትላል ስለዚህ እኛ የምንለው አሁንም መፍትሔ እናበጅለት ነው፡፡
በመጨረሻም፤ ይህዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ የጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ የቀረቡትን ዓበይት ጉዳዮች በጥልቀትና በማስተዋል ተመልክቶ ለወሳኙ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ግብአት የሚሆን የውሳኔ ሐሳብ እንዲያስተላልፍ በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክልን፤ ይቀድስልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1609
“በምንከተለው ሃይማኖት ምክንያት እየተገፋንና እየተሳቀቅን መኖርን አንፈቅድም” ሲሉ የምዕራብ ሸዋ፣ ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ተናገሩ፡፡
ብፁዕነታቸው ይህንን የተናገሩት በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ አስቦ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል በአክራሪዎች በግፍ የተገደሉ ሰማዕታትን ለማሰብ በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ነው፡፡
ብፁዕነታቸው በወቅቱ ክርስትናና መከራ ተለያይተው እንደማያውቁ አስረድተው “በተለይ በሃይማኖታችን ምክንያት መጠቃታችንና መገለላችን አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡ “ነገር ግን ማዕተቤን፣ ክሬን አልበጥስም ብሎ መሞት ግን ክብር ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አያይዘውም በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው የተቀነባበረ ጥቃት የማይቆምና የሰላምን ዋጋ የማያውቁ እጃቸውን በደም የታጠቡ ባለሥልጣናትንና አክራሪ ኃይሎችን መንግሥት አደብ ማስገዛት የማይችል ከሆነ ውሎ ሲያድር ዋጋ እንደሚያስከፍለው ገልጸዋል፡፡
የምዕራብ አሩሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ በበኩላቸው አንድነታችንን በማጠናከር በኦርቶዶክሳዊነታችን የሚደርስብንን መከራና ሥቃይ ልናስቆም ይገባናል ካሉ በኋላ ሲደርስብን የነበረው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት በመንግሥት መዋቅር በተሰገሰጉ ጫካ ያልገቡ ሽብርተኞች አማካይነት ሲደገፉና ስምሪት ሲሰጥበት የነበረ ነው ብለዋል፡፡
ብፅዕነታቸው አያይዘውም በኦርቶዶክሳውያን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል በአክራሪዎች ሲፈጸም ቆመው ያዩ የነበሩ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር በመኖራቸው መንግሥትም ይህንን ተገንዘቦ መዋቅሩን እንዲያጸዳ ጠይቀዋል፡፡
“በሃይማኖታችን ምክንያት ጥቃት እየደረሰብንና እየተሳቀቅን በራሳችን ሀገር መኖር የለብንም” ያሉት ብፁዕነታቸው መንግሥት የደኅንነት ዋስትና ሊያረጋግጥልን ይገባል ብለዋል፡፡ ምእመናን እየሞቱ ያሉት በሃይማኖታቸው ምክንያት መሆኑን በመገንዘብ የእነርሱን ጽናትና ትዕግሥት መላበስ እንደሚያስፈልግ ለሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1202
የአርመንያው ፓትርያርክ በኢየሩሳሌም ኖሩህን ማኖልያን ለእስራኤሉ ፕሬዜዳንት ሚስተር ሪውቩን ሪቪሊን በጻፉላቸው ደብዳቤ የአርመን ግዛት በሆነችው ኖጎሮን ካራባክህ የአዘርባጃን መንግሥት እስራኤል ሠራሽ በሆኑ የጦር መሣሪያዎች ታግዞ ንጹሓን ዜጎችን እያጠቃ መሆኑን ማስታወቃቸውን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
በአዘርባጃንና በአርመን ጦር ሠራዊት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ንጹሓን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ጥቃት እየተጋለጡ እንደሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ በደብዳቤው አንሥተው የአዘርባጃን ሠራዊት በወሰደው የኃይል ርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎችና ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ለከፋተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ብለዋል፡፡
የአዘርባጃን ጦር ሰራዊት በንጹሓን ላይ የወሰደው የኃይል ርምጃ እስራኤል ሠራሽ የሆኑ አውሮፕላኖችንና ድሮኖችን ተጠቅሞ መሆኑን በእስራኤል ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በድንገት ሲነገር መስማት ያሳዝናል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረው፤ የአዘርባጃን መንግሥት የተጠቀማቸው ጦር መሣሪያዎች ሁሉ ከእስራኤል የተላኩና በናጎሮ ካራባክ የሚገኙ ንጹሐንን ለሞትና ለአካል ጉዳት እየዳረጋቸው ነው ሲሉ ፓትርያርኩ ለፕሬዝደንቱ በጻፉት ደብዳቤ ቅሬታ አቅርበዋል፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘውም እስራኤል ሰላም ወዳድ ሀገር መሆኗ ቢታወቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፀረ ሰላም ከሆነችው አዘርባጃን ጎን መቆሟ ጦርነቱ በአዘርባጃን የበላይነት እንዲጠናቀቅ ከመፈለግ ውጭ በሀገሪቱ መካከል ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ፍላጎት ያላት አይመስለኝም ብለዋል፡፡
እስራኤል ለአዘርባጃን መንግሥት የምታደርገውን የመሣሪያ ድጋፍ ከዚህ በኋላ እንድታቆም ቅዱስ ፓትርያርኩ ጠይቀው እስራኤል የሰላምን ዋጋ ከማንም በላይ ጠንቅቃ የምታውቅና ስቃይን በቅጡ የምትረዳ ሀገር ናት ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ለአርመንያ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት ለሆነው የአዘርባጃን መንግሥት የሚደረገው የመሣሪያ ድጋፍ በናጎሮ ኮራባክ በሚኖሩ ንጹሐን ላይ ሞት ማወጅ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ያስረዱት ቅዱስ ፓትርያርኩ የእስራኤሉ ፕሬዝደን ጉዳዩን በደንብ በማጤን ለቅሬታው አስቸኳይ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኦርንታል ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት አባል ስትሆን በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በርሳሲድ ገዥ ንጉስ ተሪዳተስ ሦስተኛ አማካይነት ክርስቲያናዊ መንግስትን የመሠረተች ብቸኛዋ ሀገር ናት እንዲሁም ኖጎሮን ካራባክህ የተባለችው ሀገር ደግሞ በአዘርባጃን ግዛት የምትገኝና በአብዛኛው የአርመንያ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የሚኖሩባት እራስ ገዝ ሀገር መሆኑኗ ይታወሳል፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 2144
ኤስኤኤቲ በተሰኘው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የተመለከተ ውይይት መካሄዱን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
የፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሚስተር ጆርጅ አሌክሳንደር በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም አማካይነት ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁፅ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል፣ ለሩሲያ ሕዝብና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ የተካሄደ ውይይት መሆኑን ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዘህ ቀደም በዋና ጸሐፊው በኩል የቀረበላትን ጥሪ በአዎንታ የተመለከተችው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እተፈጸመ ያለ የታቀደ ጥቃት›› በሚል ርዕስ ተጋባዥ ኢትዮጵያውያን እንግዶች፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የሩሲያ ቤተክርስቲያን ጋዜጠኞችና የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ተጠሪ በተገኙበት በኤስኤኤቲ በተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያዋ ላይ ውይይት እንዲካሄድ ማድረጓን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ጉዳይ እየተከታተሉ ለፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ድርጅት ሪፖርት ለሚያደርጉት ዲያቆን ሰሎሞን ክብርያና አቶ ምንተስኖት ደስታ በውይይቱ ምስጋና እንደቀረበላቸው ዘገባው አስረድቷል፡፡
ፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ የተባለው ድርጅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያንን ሰቆቃ ለሩሲያ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ያቀረበ ብቸኛው ድርጅት እንዳደረገው ዘገባው አስታውቆ “ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት የወንጀሎችን እየተከታተለ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቋል” ብሏል፡፡
የፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ጆርጅ አሌክሳንደር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የተመለከቱ ሪፖርቶችን ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እንዳስገቡ ከዘገባው ለመዳት ተችሏል፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1100
ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በባህልም ሆነ በሃይማኖት እንዲሁም በሕግ ራሳቸውን የመከላከል መብት አላቸው፡፡ የትኛውም ምእመን ራሱንም ሆነ በእምነት የሚመስሉትን የመጠበቅ ኃላፊትነት አለበት፡፡ ሌላውን ማጥቃት ሳይሆን ሌላው ሊያጠቃ ሲል ቀድሞ መከላከል ችላ የማይባል ተግባር መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሰዓት ኦርቶዶክሳውያን ራሳቸውን ለመላከል ሳይችሉ ቀርተው ወይም አቅሙ ስለሌላቸው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ስለማይፈቅድ ነው፡፡ ክፉን በበጎ እንጂ ክፉን በክፉ መልስ የሚል አስተምህሮ ቤተክርስቲያን የላትምና፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች በተደጋጋሚ በኦርቶዶክሳውያንና በንብረታቸው ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ጥቃት መድርሱ ምንን ያሳያል ይላሉ?
ቀሲስ ሙሉቀን፡- ከዚህ ቀደም እስላማዊው አክራሪ ቡድን የፈጸማቸው ተከታታይ ጥቃቶች በዋናነት አብያተ ክርስቲያናትንና ምእመናንን ዒላማ ያደረገ ነበር፡፡ በዚህኛው ጥቃት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ ላይ መንግሥት ትኩረት አድርጎ መከላከያ ሠራዊትን በማሰማራት አብያተ ክርስቲያናትን መጠበቅ ሲጀምር እስላማዊው አክራሪ ቡድን ደግሞ ታክቲክ ቀይሮ ምእመናንን፤ ቤታቸውንና ሀብት ንብረታቸውን ማጥቃት ጀመረ፡፡ የድርጊቱ ዋና ዓላማ ምእመናን መኖሪያ ቤት ሲያጡና የዕለት ጉርስ ሲርቃቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ወይም ተቸግረው እንዲሰልሙ ማድረግ ነው፡፡ ምእመናን ከሌሉ ደግሞ በየአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ከሕንፃነት የዘለለ ሚና አይኖራቸውም፡፡ ከሰሞኑ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተከሰሠተው ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋም ምእመናን እንደተለመደው ቤተ ክርስቲያናቸውን በመጠበቅ ላይ እያሉ እስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን የምእመናኑን ቤትና ንብረት ይዘርፍና ያቃጥል ነበር፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1110
የኦሮሚያ ፖሊስም ሕይወት ከማዳን ይልቅ በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ላይ ቀጥታ ጥይት በመተኮስ ለአክራሪው ቡድን ከለላ ሰጥቷል፤ የመሣሪያና የስንቅ ትጥቅ ድጋፍም አድርጓል፡፡ ሕግን እንዲያስከብር ጥሪ ሲደረግለት “ትዕዛዝ አልተሰጠኝም” በማለት የሰው ሕይወት ሲጠፋ በታዛቢነት ተመልክቷል፡፡ እነዚያ ግፍ የተፈጸመባቸው ምእመናን በአሁኑ ሰዓት በሕይወት የተረፉት በሕክምና ቦታ፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አንዳንድ ምእመናን እንደሚናገሩት ከሆነ የተፈጸመው ጥቃት የተቀናጀና በግልፅ የመንግሥት የፀጥታ አካላትም ተሳትፎ ያደረጉበት ነበር፡፡ በአክራሪ ኃይሉ የተፈጸመው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ሃይማኖት ተኮር ሲሆን በኦርቶዶክሳውያኑ ላይ ሆን ተብሎ ታቅዶና ታስቦ የተፈጸመ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች እንዳሉ በዝርዝር ተናግረዋል፡፡
የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የፀጥታ ኃይሎችና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ባሉበት መፈጸሙ ደግሞ ጥቃቱ ቀደሞ የታቀደ እንደሆነ አመላካች ነው በማለት ምዕመናኑ ያክላሉ፡፡ የደረሰው ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት መከላከልም ሆነ መቀነስ ይቻል እንደነበር የገለጡት ምእመናኑ ነገር ግን የመንግሥት መዋቅሩ የተሳተፈበት በመሆኑ በሕይወታችንና በንብረታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብናል ይላሉ፡፡ አንዳንድ የ ፀጥታ ኃይሎች ሁሉም ነገር ከወደመ በኋላ ለይስሙላ ጥፋቱን ለመከላከል ጥረት እያደርጉ እንደነበረ የተናገሩም አልጠፉም፡፡
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1289
ለ፫፻፴ ዓመታት ያህል በአይሁድ ክፋት እና ጭካኔ ተቀብሮ ተራራ የሚያህል ቆሻሻ የተደፋበት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክበቡር መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት ከተቀበረበት ወጥቶ በከበረው ስፍራ እንዲቀመጥ ከተደረገ እነሆ ፳፻ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ አይሁድ ሙት ያስነሣ ፣ ድውይ ይፈውስ የነበረውን ክቡር መስቀል ከኢየሩሳሌም የቆሻሻ መጣያ ወስደው ሲቀብሩ ፈዋሽነቱ እንዳይነገር ፣ አዳኝነቱ እንዳይመሰከር፣ ታሪኩ ተቀብሮ እንዲቀር አስበው እና አልመው ነበር፡፡ መስቀሉን በጊዜው ቆፍረው ማውጣት ያልቻሉ በአካባቢው የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ለይተው ቢያውቁም በ፸ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ ከሀገር በመሰደዳቸው ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቀው ሰው አልነበረም፡፡ የአይሁድ አላማም ይህ ነበረ ነገረ ድኅነቱ እንዲረሳ ከሰው ልብ እንዲወጣ ማድረግ፡፡ ለዚያም ነው ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ስትመጣ ኪርያኮስ የተባለ በዕድሜ የገፋ የጥንቱን የሚያውቅ ሰው ያስፈለጋት፡፡